Learning materials for your health  Learn

ከማኅፀን ውጪ የሚከሠት እርግዝና  (Ectopic Pregnancy)

  • May 9, 2023
  • የጤና እክሎች

ከማኅፀን ውጪ የሚከሠት እርግዝና  (Ectopic Pregnancy)

 ከማኅፀን ውጪ እርግዝና  የሚከሠተው፤  ከማኅፀኑ ውስጠኛው ግድግዳ በውጭ በኩል ሌላ የሴት መራቢያ አካሎች ወይም የሆድ ክፍል ውስጥ ትክለተ ፅንስ ሲካሄድ ነው። ዘጠና ስምንት በመቶ የሚሆኑት ከማኅፀን ውጭ የሚፈጠሩ እርግዝናዎች  በእንቁላል መተላለፊያ ቱቦ (fallopian tube) ውስጥ ይከሠታሉ።  አልፎ አልፎ በማደግ ላይ ያለው ፅንስ  በማኅፀን በር ጫፍ (cervix)፣ በእንቁልጢ (ovary) ወይም በሆድ እና በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሊከሠት ይችላል ፡፡

መንታ እርግዝና በሚኖርበት ወቅት፤  አንዱ  ፅንስ በትክክል  በማኅፀን ውስጠኛው ግድግዳ ላይ ትክለት ሲያካሂድ፣ ሌላኛው ደግሞ ከማኅፀን ውጪ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ያልተለመደ ክሥተት ቢሆንም የመሃንነት ሕክምና በሚወስዱ ሴቶች ላይ የመከሠት ዕድሉ ሰፋ ያለ ነው፡፡

ከማኅፀን ውጪ የሚከሠት  እርግዝና አደጋው ምንድንነው?

በአጠቃላይ ከማኅፀን ግድግዳ ውጪ  የሚተከሉ ሽሎች  ሲያጋጥሙ፤ ለፅንሱ ደም የሚያቀርበው የእንግዴ ልጅ ጤናማ ስለማይሆን  በሥርዓት ማደግ አይችሉም፡፡ በተጨማሪም  በማደግ ላይ ያለው ፅንስ የተተከለበት አካል  ላይ በሚያሳድረው  ግፊት ምክንያት ወደ መበጠስ ወይም መፈንዳት ሊያመራ ይችላል።

ይህም በሚሆንበት ጊዜ እስከ ሞት የሚያደርስ ከፍተኛ ውስጣዊ የደም መፍሰስ  ያስከትላል፡፡

ከማኅፀን ውጪ ለሚከሠት  እርግዝና አጋላጭ ምክንያቶችን፣ ምልክቶችን እና የሕክምና አማራጮችን ማወቅ፤  ለሕይወት አስጊ የሆኑ በሽታ ከመፈጠሩ በፊት ጥንቃቄ እንዲወሰድ እና ሕክምና እንዲደረግ ይረዳል፡፡

ከማኅፀን ውጪ ለሚፈጠር እርግዝና  አጋላጭ  ምክንያቶች

  • የእንቁላል መተላለፊያ ቱቦዎች መጎዳት፤ በኢንፌክሽኖች፣ በቀዶ ጥገና፣በእጢዎች ወይም አብሮ በሚወለድ እክል ምክንያት፤

  • ተፈጥሮአዊ የማኅፀን አቀማመጥ መዛባት (T-shaped, bicornuate uterus)

  • ከዚህ በፊት ከማኅፀን ውጪ እርግዝና ተፈጥሮ ከነበረ፤

  • የአባለዘር በሽታ የነበረባቸው እናቶች፤

  • ከአንድ በላይ የወሲብ አጋር ያላቸው ሴቶች፤

  • ሲጋራ ማጨስ

  • ዕድሜ መግፋት

  • ለመካንነት የሚሰጡ መድኃኒቶች እና ሕክምናዎችን የሚወስዱ ሴቶች፤

  • በማኅፀን ውስጥ የሚቀመጥ የእርግዝና መከላከያ (IUD) የሚጠቀሙ ሴቶች  የማርገዝ ዕድላቸው እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ሆኖም እርግዝና በሚፈጠርበት ጊዜ ግን ከማኅፀን ውጪ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ 

  • በማኅፀን  ውስጥ እያሉ ለ ዲኢታይልስቲልቢስትሮል (diethylstilbestrol) (ተፈጥሮአዊ የአልሆነ ሰው ሠራሽ /ሲንቴቲክ/ ለሴቶች የሚታዘዝ ኢስትሮጅን ሆርሞን ነው፡፡ ፅንስ ማስወረድን፣ አለጊዜው የሚከሠት ምጥ፣ ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ውስብስብ የእርግዝና ችግሮችን ለመከላከል የሚታዘዝ ነው፡፡) ለዚህ ተጋላጭነት የነበራቸው እናቶች  በእንቁላል መተላለፊያ ቱቦዎቻቸው ላይ እክል የመኖሩ ዕድል ክፍተኛ ነው፡፡

 ከማኅፀን ውጪ የሚከሠት እርግዝና ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የዚህ በሽታ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ እናትየዋ እርጉዝ መሆኗን ሳታውቅ ሊከሠቱ ይችላሉ። 

  • የሆድ ሕመም

  • የወር አበባ አለማየት

  • ከማኅፀን መጠነኛ ደም መፍሰስ

  • የእርግዝና ምልክቶች (እንደ ማቅለሽለሽ፣ የጡት ሕመም ወይም ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት)

ሆኖም ከ 50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች የእንቁላል መተላለፊያ ቱቦ እስኪበጠስ ድረስ ከመጠነኛ የሆድ ሕመም የዘለለ ምልክት አያሳዩም፡፡ የቱቦውን መበጠስ ተከትሎ  ከባድ የሆድ ሕመም፣ የትከሻ አካባቢ ሕመም እና በማኅፀን ደም መፍሰስ ይኖራል፡፡ ይህም በመጀመሪያ ማዞር እና ጭልም ማለት፤ በመቀጠልም የደም ግፊት መቀነስ እና ራስን መሳትን ያስከትላል።

ከማኅፀን ውጪ የሚከሠት እርግዝና ለሕይወት አስጊ ስለሆነ በአስቸኳይ የሕክምና ርዳታ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡

ከማኅፀን ውጪ ለሚከሠት እርግዝና ምርመራው ምንድነው?

ከማኅፀን ውጪ የሚከሠት እርግዝናን ለመመርመር የሚያገለግሉ ምርመራዎች  አልትራሳውንድ እና የእርግዝና (hCG) ሆርሞንን የሚለካ የደም ምርመራን ያካትታሉ፡፡

ከማኅፀን ውጪ ለሚከሠት እርግዝና ሕክምናው ምንድነው?

ከማኅፀን ውጪ እርግዝና እንዳለ በምርመራ እንደተረጋገጠ ወዲያውኑ ሕክምናው ይጀመራል፡፡ ይህም የመድኃኒት ወይም የቀዶ ጥገና ሕክምና ሊሆን ይችላል፡፡

1.  የመድኃኒት ሕክምና - አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከማኅፀን ውጪ እርግዝና ያጋጠማቸው እናቶች የፅንሱን ዕድገት በሚያስቆም ሜቶትሪክሴት (methotrexate) በሚባል መድኃኒት ሊታከሙ ይችላሉ፡፡ በመርፌ መልክ የሚሰጥ መድኃኒት ሲሆን፤ የሆድ ሕመም እና ቁርጠት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህንንም ለማከም ፓራሲታሞል (paracetamol) መጠቀም በቂ ነው፡፡ NSAIDs(ibuprofen፣ aspirin) ከሜቶትሪክሴት ጋር ባላቸው መስተጋብር ምክንያት መጠቀም የተከለከል ነው።

በትክክለኛው ሁኔታ ጥቅም ላይ ሲውል እና ተገቢው ክትትል ሲደረግ በሜቶትሪክሴት የሚደረግ ሕክምና እስከ 95 በመቶ ስኬታማ ነው ፡፡

2.     የቀዶ ጥገና ሕክምና - ቀዶ ጥገና ሕክምና ለማድረግ ከሚያስገድዱ ሁኔታዎች ውስጥ የተወሰኑት የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡

  • በማደግ ላይ ያለው ፅንስ ትክለት ባካሄደበት አካል ላይ የመፈንዳት ወይም የመበጠስ ጉዳት ሲያስከትል፤

  • በጠና የታመሙ ሴቶች ላይ፤

  • የመድኃኒት ሕክምና ለማድረግ የማይፈቅዱ ሁኔታዎች ወይም ተያያዠ በሽታዎች ከአሉ፤

  • በመድኃኒት ሕክምና ወቅት ተገቢውን ክትትል ማድረግ የማትችል ሴት፤


 

የቀዶ ጥገና ሕክምናው እንዴት ይከናወናል?

የቀዶ ጥገና ሕክምናው የሆድ ዕቃን በመክፈት ወይም የተወሰኑ ቀዳዳዎችን በመፍጠር ካሜራ የተገጠመለት ቀጭን ቱቦ በመጠቀም ሊከናወን ይችላል፡፡ የሆድ ዕቃን በመክፈት ከሚደረገው ቀዶ ጥገና ጋር ሲነጻጸር ሁለተኛው  የቀዶ ጥገና መንገድ ሕመም ለመቀነስ እና በፍጥነት ለማገገም ያስችላል ፡፡

በቀዶ ጥገና ወቅት የእንቁላል መተላለፊያ ቱቦ መውጣት አለበት? 

አንዳንድ ጊዜ በቀዶ ጥገና ወቅት ከማኅፀን ውጪ የተፈጠረውን  እርግዝናን ማስወገድ እና ቱቦውን መጠገን ይቻላል፡፡

በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ  የእንቁላል መተላለፊያ ቱቦን ማስወገድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ይህም የማይቆም የደም መፍሰስ ከአለ፣ በዚያው ቱቦ ውስጥ ተደጋጋሚ እርግዝና ከተፈጠረ፣ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ቱቦ ከሆነ፣ ፅንሱ ከመጠን በላይ በቱቦ ውስጥ ከአደገ  እንዲሁም ልጅ መውለድን ባጠናቀቁ ሴቶች ላይ ይከናወናል፡፡

በቀጣይ የማርገዝ ዕድል ምን ያሀል ነው?

ከዚህ በፊት ከማኅፀን ውጪ እርግዝና ከተፈጠረ በኋላ በቀጣይ በትክክል በማኅፀን ውስጥ እርግዝና የመፈጠር ዕድሉ ከ 38 እስከ 89 በመቶ ሲሆን፤ ደጋሚ ከማኅፀን ውጪ እርግዝና የመፈጠር ዕድሉ ደግሞ ወደ 15 በመቶ ነው።


 

Share the post

scroll top