Learning materials for your health  Learn

ትኩረት የማጣት እና የአለመረጋጋት ችግር

 • June 10, 2022
 • የጤና እክሎች

ትኩረት የማጣት እና የአለመረጋጋት ችግር

(Attention Deficit Hyperactivity Disorder/ ADHD)

ትኩረት የማጣት እና የአለመረጋጋት ችግር (Attention Deficit hyperactivity / ADHD) የሚባለው ከተለመደው የሕፃናት ችኩልነት እና አለመረጋጋት በላቀ መልኩ የመንቀዥቀዥ እና ችኩልነትን የሚያስከትል የአእምሮ ጤና መታወክ ነው ፡፡ 

የ ኤ ዲ ኤች ዲ በሽታ የአለባቸው ሰዎች ትኩረታቸውን በአንድ ሥራ ላይ በማድረግ ረዘም ለአለ ጊዜ ለመቆየት ይቸገራሉ፡፡ አንድ ነገር ጀምረው አፍታም ሳይቆዩ ሌላ ነገር ሐሳባቸውን ይሰርቀዋል። 

ይህ ሕመም አብዛኛውን ጊዜ ከ ሦስት እስከ ስድስት ዓመት በአሉ ልጆች ላይ የሚከሠት የሥነ ልቦና ችግር ነው፡፡ እነዚህ ሕፃናት ከአደጉ በኋላም ምልክቶቹ በቀን ተቀን ሕይወታቸው ላይ ሊንጸባረቅ ይችላል። ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱ ሕፃናት መካከል ከ5 እስከ 10% የሚሆኑት በዚህ በሽታ ይጠቃሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ወንዶች ከሴቶች ጋር ሲነጻጸር በበሽታው የመጠቃት ዕድላቸው ከ 3 እጥፍ በላይ ከፍ ያለ ነው ።

የሕመሙ መንሥኤ በግልጽ ባይታወቅም ጥናቶች በአእምሮአችን ውስጥ ያሉ ኬሚካል ንጥረ ነገሮች ማነስ አስተዋጽዖ እንደአላቸው ያመለክታሉ። በተጨማሪም በቤተሰብ ውስጥ በዚህ ሕመም የተጠቃ ሰው ከአለ ለሕመሙ የመጋለጥ ዕድልን ከፍ ያደርጋል።

የበሽታው ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?

ሁላችንም እንደምናውቀው ከዐዋቂዎች ይልቅ ሕፃናት የመሯሯጥ እና የመጫወት ተፈጥሮአዊ ጠባይ አላቸው። ማንኛውም ጤናማ ሕፃን ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር ይጫወታል፡፡ እንደ ዐዋቂዎች ትኩረቱን ሰብስቦ ለረጅም ሰዓት በአንድ ቦታ ሥራ ላይ ማሳለፍ ይቸገራል፡፡ ቤት ውስጥም ሆነ ትምህርት ቤት ውስጥ ሊያስቸግር ይችላል። በ ኤ ዲ ኤች ዲ በሽታ የተጠቁ ሕፃናት ላይ ግን ከጤነኛ ሕፃናት በጣም በተለየ መልኩ እነዚህ ምልክቶች ገነው ይታይባቸዋል። 

 • ሐሳባቸውን በትምህርት፣ በቤት ሥራ እንዲሁም በጨዋታ ላይ ሳይቀር ለመሰብሰብ ይቸገራሉ። በዚህ ምክንያት ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ 20 እስከ 50 በመቶ የሚሆኑት በትምህርታቸው ደካማ ይሆናሉ።

 • በቀላሉ ሐሳባቸው ይሰረቃል።

 • ዝንጉ ናቸው።

 • ለደቂቃ ተረጋግተው መቀመጥ አይችሉም።

 • ሌላ ሰው ሲያወራ በመሐል አቋርጠው ሊያወሩ እና ሊረብሹ ይችላሉ።

 • ለጨዋታም ሆነ ለማንኛውም ነገር ተራ መጠበቅ አይወዱም፤ አይችሉም። 

 • ሁሌም ንቁ ናቸው።

 • በቀላሉ ይናደዳሉ፤ ይበሳጫሉ።

 • እያደጉ ሲመጡ ደግሞ ለአደንዣዥ ሱስ የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል። 

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች በትምህርት ቤት፣ ከጓደኞቻቸው ጋራ ሲጫወቱ እንዲሁም በቤት ውስጥ ይታያሉ። በዚህ ምክንያት በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ለማምጣት ይቸገራሉ። እንዲሁም ከጓደኞቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት አይኖራቸውም።

እዚህ ላይ መረዳት የአለብን ነገር እነዚህ ምልክቶች እንደ ሕመም የሚቆጠሩት የሚከተሉት ነገሮች ከተሟሉ ነው። እነዚህም፤

 • ምልክቶቹ ቢያንስ ለአለፉት ስድስት ወራት መታየት አለባቸው፡፡ 

 • ምልክቶቹ ሲጀምሩ የሕፃኑ ዕድሜ ከ ሰባት ዓመት በታች ከሆነ

 • ምልክቶቹ ቢያንስ ሁለት እና ከዚያ በላይ የሆነ ቦታ መታየት ይጠበቅባቸዋል። ለምሳሌ ሕፃኑ ምልክቶቹን የሚያሳየው ቤት ውስጥ ብቻ ከሆነ ኤዲ ኤች ዲ ለማለት ያዳግታል። በተጨማሪም ምልክቶቹ በትምህርቱ ላይ እና በማኅበራዊ ሕይወቱ፣ ከእኩዮቹ ጋር በሚኖረው ግንኙነትና ጨዋታ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አለበት።

 • ሕፃኑ እነዚህን ምልክቶች ሊያሳይ የሚችል ሌላ የሥነ ልቦና በሽታ እንደሌለበት ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

በበሽታው ከተጠቁ ሕፃናት ውስጥ 60% የሚሆኑት ከአደጉ በኋላም ምልክቶቹን ሊያሳዩ ይችላሉ። በትምህርታቸው እና ሥራቸው ላይ ሐሳባቸውን መሰብሰብ ስለማይችሉ ውጤታማ ለመሆን ይቸገራሉ። በተጨማሪም ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ይቸገራሉ፡፡ ነገሮችን በቀላሉ ይረሳሉ፤ እንዲሁም ትዕግሥት የላቸውም። ነገር ግን በአጠቃላይ ዕድሜ በጨመረ ቁጥር የበሽታው ክብደት እየቀነሰ የመሄድ አዝማሚያ አሳይቷል። 

የ ኤ ዲ ኤች ዲ በሽታ ዓይነቶች 

ሦስት ዓይነት የ ኤ ዲ ኤች ዲ ዓይነቶች አሉ። 

 1. በዋነኝነት ትኩረት ለመሰብሰብ የሚቸገሩ

 2. ለመረጋጋት የሚቸገሩ

 3. ትኩረት ለመሰብሰብም ሆነ ነገሮችን ተረጋግተው ለመሥራት የሚቸገሩ ናቸው።

ምንም እንኳን አብዛኞቹ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ትኩረት ለመሰብሰብም ሆነ ነገሮችን ተረጋግተው ለመሥራት የሚቸገሩ ቢሆንም፤ በሴቶች ላይ በስፋት የሚታየው በዋነኝነት ትኩረት ለመሰብሰብ መቸገር ነው። እነዚህ ሕፃናት ክፍል ውስጥ ስለማይበጠብጡ በሽታቸው ሳይታወቅላቸው ብዙ ዓመት ሊኖሩ ይችላሉ።

ሕክምናውስ ምንድን ነው?

በ ኤ ዲ ኤች ዲ የተጠቁ ሰዎች ትክክለኛውን የሕክምና ክትትል ማግኘታቸው በመጠኑም ቢሆን ምልክቶቻቸውን ለመቀነስ ይረዳቸዋል። ከወላጆቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው እንዲሁም ከአስተማሪዎቻቸው ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዲመሠርቱ እና በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ሕክምናው ያግዛቸዋል፡፡ 

በዋነኝነት የበሽታው ሕክምና አነቃቂ መድኃኒቶች ናቸው፡፡ የምክር አገልግሎት እና የተለያዩ የሳይኮቴራፒ ዓይነቶች እንደአስፈላጊነታቸው ሊጨመሩ ይችላሉ። 

ከአነቃቂ መድኃኒቶች ውስጥ በምዕራቡ ዓለም በሰፊው የሚታወቀው ሜታይልፌኒዴት (Methylphenidate) የሚባለው መድኃኒት ሲሆን፤ በሃገራችን ውስጥ በስፋት አይገኝም። ስለዚህም በምክር አገልግሎት እና በሀገራችን በሚገኙ ሌሎች ንዴትን ለመቀነስ የሚረዱ መድኃኒቶችን በመስጠት ምልክቶቹን ለመቆጣጠር ጥረት ይደረጋል።

 ለምሳሌ

 • የቀን ውሎ ዕቅድ በማውጣት መምራት

 • ሐሳብን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ነገሮችን መቀነስ

 • ሐሳብን ሊይዙ የሚችሉ የጥናት መንገዶችን መጠቀም

 • በሥራ ወይም ጥናት መካከል የዕረፍት ሰዓት ማዘጋጀት

 • ሕፃኑ የሚወደውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለይቶ ማወቅ እና እንዲሳተፍ መፍቀድ

 

Share the post

scroll top