Learning materials for your health  Learn

ሲጋራ የማጨስ ጉዳቶች (Effects of cigarette smoking )

  • June 19, 2023
  • የጤና እክሎች

ሲጋራ የማጨስ ጉዳቶች (Effects of cigarette smoking )

  • ሲጋራ ማጨስ ለበርካታ አካላዊ እና ስነ አእምሮአዊ  በሽታዎች መከሰት መንስኤ ነው። በአለም የጤና ድርጅት ጥናት መሰረት በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ 4 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ሲጋራ ያጨሳል። 

  • ሲጋራ በውስጡ ኒኮቲን የተባለ ንጥረ ነገር አለው። ኒኮቲን የአንጎልን ነርቭ አስተላላፊዎችን በማወክ  ጊዜያዊ የሆነ የደስታ ስሜት እዲፈጠር የሚያደርግ ንጥረ ነገር ነው። 

  • ሲጋራን የሚያጨሱ ሰዎች ተመሳሳይ የሆነ የደስታን ስሜት ለማምጣት የሚወስዱትን የኒኮቲን መጠን መጨመር ይኖርባቸዋል፤ ከዚህ የተነሳ በዛ የአለ ሲጋራን ለማጨስ ይገደዳሉ። 

  • በተጨማሪም ማጨስን ለማቆም በሚሞክሩበት ጊዜ ደስ የማይል አካላዊ እና ስሜታዊ ለውጦች ይኖሯቸዋል።

ለሲጋራ ማጨስ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች እነማን ናቸው?

  • ዕድሜ፤ አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች ወይም በአስራዎቹ እድሜ የአሉ ሰዎች በሲጋራ ሱስ የመያዝ እድላቸው ሰፊ ነው።

  • የዘረ-መል ተፅእኖ፤ የዘረ መል አወቃቀር የአንጎል ሕዋሳት ለሲጋራ (Nicotine) ጥገኝነት እዲዳረጉ የራሱ የሆነ ተፅእኖ ሊያሳድር ይችላል። 

  • የወላጅ እና የአቻ ተፅእኖ፤ የሚያጨሱ ወላጆች ወይም የሚያጨሱ አቻ ጓደኞች የአሏቸው ሰዎች የማጨስ ዕድላቸው ሰፊ ነው።

  • የስነ ልቦና ችግሮ ች፤ ለምሳሌ ድባቴ፣ ስኪዞፍሬኒያ ወይም ጭንቀት ሲጋራ የማጨስ እድልን ይጨምራሉ

  • የአልኮሆል እና ሌሎች የደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች ሲጋራ የማጨስ እድላቸው ሰፊ ነው። 

 

ሲጋራ ማጨስ የሚያመጣቸው ስነ ልቦናዊ ጉዳቶች ምንድናቸው?

  • ሲጋራ ማጨስ ከሚያከትላቸው ስነ- ልቦናዊ ቀውሶች ውስጥ ዋነኛው የሲጋራ-ጥገኝነትን (Nicotine dependence)ማስከተል ነው። የሲጋራ ጥገኝነት ምልክቶች በየትኛውም የሲጋራ መጠን ላይ ሊከሰቱ ይችላሉ።

የሲጋራ ጥገኝነት ምልክቶች ምንድናቸው?

  • ሲጋራ ማጨስን ማቆም አለመቻል ፤

  • ይህ ምንም እንኳን ሲጋራ ማጨስ ለማቆም ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም ግን አለመቻል ነው። 

  • ማጨስ ለማቆም ሲሞክሩ የተለያዩ አካላዊ እና ስነ አእምሮአዊ  ችግሮች መታየት፤

 

  • ለምሳሌ፣  ለማጨስ ከፍተኛ ፍላጎት መኖር ፣ ጭንቀት ፣ ብስጭት ፣ መረጋጋት አለመቻል ፣ ትኩረትን የመሰብሰብ ችግር ፣ የረሃብ ስሜት መጨመር ፣ እንቅልፍ ማጣት ፣ የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ መኖር ናቸው። 

  • የጤና ችግሮች (የሳንባ ወይም የልብ) እንደአሉ እያወቁ እንኳን ማጨስን መቀጠል፤ 

  • ማህበራዊ ህይወትን መቀነስ ፡፡ ሲጋራ ማጨስ ከባድ ወደ ሆኑባቸው አካባቢዎች ወይም ሁኔታዎች ከመሔድ መቆጠብ፤ 

  • ለምሳሌ፣ ከቤተሰብ ወይም ከጓደኞች ጋር መገናኘት፣ ምግብ ቤቶች ወይም መዝናኛ ቦታዎች መሔድ መቀነስ ናቸው።

ሲጋራ ማጨስ የሚያስከትለው አካላዊ የጤና ጉዳቶች ምንድናቸው?

  • የሲጋራ ጭስ በውስጡ ከ 60 በላይ ካንሰርን የሚያስከትሉ ኬሚካሎችን እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ጎጂ ንጥረ ነገሮች አሉት ፡፡ 

  • ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች በአንፃሩ ከማያጨሱ ሰዎች በተለየ መልኩ በበሽታ የመያዝ እና የመሞት ዕድላቸው ሰፊ ነው።

  • የሳንባ ካንሰር ወይም ሥር የሰደደ የሳንባ በሽታ። 

  • ሲጋራ ለሳንባ ካንሰር መከሰት እና ሞት ዋነኛው መንስኤ ነው። በተጨማሪም ሊሎች እንደ ኤምፊዚማ፣ ብሮንካይተስ፣ አስም እና የመሳሰሉ የሳንባ በሽታዎችን ያስከትላል። እንዲሁ ከአሉም እዲባባሱ ያደርጋል። 

  • ሌሎች ሲጋራ ማጨስ የሚያመጣቸው የካንሰር አይነቶች እነማን ናቸው?

  • ሲጋራ ማጨስ የአፍ ፣ የጉሮሮ ፣ የፊኛ ፣ የቆሽት ፣ የኩላሊት ፣ የማህጸን ጫፍ፣  የደም ካንሰር እና ሌሎች በርካታ የካንሰር ዓይነቶች ተጋላጭነትን ይጨምራል ፡፡

  •  በአጠቃላይ ሲጋራ ማጨስ  በካንሰር  የመሞት ዕድልን 30 በመቶ ያህል ይጨምረዋል ፡፡

  • የልብ ድካም እና የደም ዝውውር ስርዓት ህመም። 

  • በስትሮክ የመመታት እና የመሞት ዕድልን ይጨምራል።

  • የስኳር በሽታ

  • የአይን ህመም

  • መካንነት እና ስንፈተ ወሲብ

  • በእርግዝና ወቅት ችግር መፈጠር (ምጥ የአለ ጊዜ መጀመር፣ ከጤናማ ክብደት በታች የሆነ ልጅ መውለድ) እና

  • የጥርስ እና የድድ ብግነት ወይም መቆጣት ናቸው።

ማጨስ ለማቆም ምን እናድርግ?

  • በራስ ተነሳሽነት ያለጤና ባለሙያ እርዳታ ማጨስን ለማቆም የሚደረጉ ሙከራዎች ረዥም ጊዜ ከመውሰዱም በላይ ውጤታማ ላይሆን ይችላል። 

  •  ከጤና ባለሙያዎች ጋር በመመካከር፣ የተለያዩ መድኃኒቶች እና የስነ ልቦና ምክክሮችን በማድረግ ከሲጋራ ጥገኝነት ነፃ መውጣት ይቻላል። 

መድኃኒቶች

  • የጤና ባለሙያዎች የማጨስ ፍላጎትን የሚቀንሱ እና ማጨስ የመተው ምልክቶችን የሚያስታግሱ መድኃኒቶች በመስጠት ሕክምናውን ያቀላጥፉታል።

የስነ ልቦና ምክክር

  • የስነ ልቦና ምክክር ማድረግ ሲጋራን ለመተው የሚያስፈልጉ  ክሂሎቶችን ለማዳበር ይጠቅማል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከጤና ባለሙያ ጋር ጊዜ ወስዶ ስለአኗኗር ዘይቤዎች እና ስለ ስራ እቅድ በማውጣት እና በትግበራው ላይ መማከር ያስፈልጋል።

  • ከቤተሰብ፣ ጓደኛ እና ተመሳሳይ ችግሮች ከአሉባቸው ሰዎች ጋር በመጣመር የልምድ ልውውጥ ማድረግ ጠቃሚ ነው። 

  ኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎች (e-Cigarettes)

  • ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎችን ማጨስ ከሲጋራ ሱስ ለመላቀቅ መፍትሔ መሆን አይችልም፤ ወይም ሲጋራን ለመተካት ተብሎ ሌሎች ኒኮቲንን የያዙ ንጥረ ነገሮችን (ጭስ አልባ ትንባሆ፣ጋንጃ፣ ሺሻ) መጠቀም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። 

ሲጋራ ማጨስ ለማቆም አስበን የጤና ባለሙያ ጋር ለመሔድ ስንዘጋጅ ምን ማድረግ አለብን?

የጤና ባለሙያን ለማማከር ስናስብ ማድረግ ከሚገቡን ነገሮች መካከል የሚከተሉት ማድረግ ለሕክምናው የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

  • የማጨስ ፍላጎት የሚያነሳሳብዎትን ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ማስተዋል፤  ወይም ሲያጨሱ የአለውን ሁኔታን በዝርዝር መፃፍ   

  • ከማጨስ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ምልክቶችን እና ለምን ያህል ጊዜ እንደሚያጨሱ ያስተውሉ።

  • የሚወስዱትን መድኃኒቶች ማስታወስ

  • በሕክምናው ወቅት የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛን መጋበዝ። 

Share the post

scroll top