Learning materials for your health  Learn

ለጨቅላ ሕፃናት የሚደረግ ክብካቤ

 • June 24, 2022
 • የጤና እክሎች

ለጨቅላ ሕፃናት የሚደረግ ክብካቤ

(New born care for parents)

አዲስ የተወለዱ ሕፃናትን እንዴት አድረገን እንከባከባቸው? 

 • አዲስ የተወለዱ ሕፃናት ለወላጆች ከሚያመጡት ደስታ እና ጥልቅ ስሜት በተጨማሪ ወላጆች ስለ ልጅ አስተዳደግ ተሞክሮ የሚያገኙበት ነው። 

 • ምንም እንኳን ስለሕፃናት አስተዳደግ ሰፊ ዝግጅት አድርገናል ብንልም፤ አንዳንድ ጊዜ ግን የአልጠበቅናቸው ተግዳሮቶች ሊገጥሙን ይችላሉ። የሚከተሉት አዲስ ለተወለዱ ሕፃናት ክብካቤ መመሪያዎች ናቸው።

     ጡት ማጥባት

 • ጨቅላ ሕፃናት በተወለዱ በአንድ ሰዓት ውስጥ የእናት ጡት መጥባት መጀመር አለባቸው፡፡ የእናት ጡት ማጥባት ካልተቻለ በሕፃኑ ዕድሜ መሠረት የተዘጋጀ የጣሳ ወተት መጠቀም ያስፈልጋል።

 • በመጀመሪያ አካባቢ የእናት ጡት ወተት በቂ ላይመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን ጡት ማጥባት ሳይቋረጥ ከቀጠለ ከ 2 ወይም 3 ቀናት በኋላ መጨመር ይጀምራል።

 • ሕፃኑን ጡት በየ 2 ወይም 3 ሰዓት፣ ለ10 - 20 ደቂቃ ያህል ማጥባት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ሕፃኑ ጡት እንደፈለገ ሲታወቅ በየትኛውም ሰዓት ማጥባት ይቻላል።

 •  ጡት ከመቀያየር በፊት አንደኛውን ጡት በደንብ ማጥባት ይመረጣል። በተጨማሪም ጡት ከአጠቡ በኋላ ሕፃኑን ቀጥ አድርጎ ወደ ላይ ደረት ላይ በመያዝ ማስገሳት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ቅርሻት እና ትውከትን ለመቀነስ ይረዳል።

ልብ ይበሉ፤ ሕፃኑ 6 ወር እስኪሆነው ድረስ ጭማቂ፣ ውሃ ወይም ሌላ ዓይነት ምግብ ወይም ፈሳሽ መስጠት አያስፈልግም።

የወላጅ እና የልጅ ግንኙነት (Bonding)

 • ሕፃናት ከተወለዱ ጊዜ ጀምረው ከእናታቸው ጋር ጡት በማጥባት ወቅት እና ቆዳ ለቆዳ በሚኖር ንክኪ ትስስራቸውን ማጠንከር ይቻላል። በተጨማሪም አባቶች ድምፃቸውን በማሰማት፣ ዐይን ለዐይን በመተያየት፣ ሕፃኑን በመታቀፍ እና የሕፃኑን ገላ በማጠብ  ከሕፃኑ ጋር የአላቸውን ግንኙነት ማጠንከር ይችላሉ።

የእትብት ክብካቤ

 • በአጠቃላይ እትብት አካባቢ ደረቅ እና ንጹሕ መሆን አለበት፡፡ ይህም እትብቱ ቶሎ እንዲወድቅ ያደርገዋል።

 • በአብዛኛው እስከ ሁለት ሳምንት በአለው ጊዜ ውስጥ እትብት ይወድቃል፡፡ ከ ሦስት ሳምንት በላይ ሳይወድቅ ከቆየ ግን የጤና ባለሙያን ማማከር ያስፈልጋል።

 • ከተቻለ የሕፃኑን ገላ ማጠብ እትብቱ እኪወድቅ ድረስ ማቆየት የተሻለ ነው፡፡ ከማጠብ ይልቅ በንጹሕ ጥጥ (ጋቢ) እና ሞቅ በአለ ዉሃ የሕፃኑን ሰውነት ማጽዳት ያስፈልጋል።

 • እትብት አካባቢ መቅላት ወይም ሽታ የአለው እንደ መግል ዓይነት ፈሳሽ ከአለ ለጤና ባለሙያ ማሳየት ይገባል፡፡

ገላን ማጠብ / ማጽዳት

 • ሕፃናት በፍጥነት ሙቀት ሊያጡ እና ለብርድ ሊጋለጡ ስለሚችሉ ሕፃናትን ገላቸውን ስናጥብ በጣም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። 

 • መጀመሪያ ለማጠብ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ማዘጋጀት፤ እነዚህም ሞቅ የአለ ዉሃ፣ የሕፃናት ማጽጃ ሳሙና፣ መታጠቢያ ቦታ (ገንዳ)፣ ማድረቂያ እና መጠቅለያ ጨርቅ ናቸው።

 •  ከዚያም በዝግታ እንዳያሟልጭ በመጠንቀቅ የሕፃኑን ገላ ማጠብ፤ የመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ ልምድ ከአለው ሰው ጋር ቢደረግ ይመከራል። 

 

SpLNXrXDdS8iW4v_VxY06i11zVjCWze5UwO3CY0gybdLI6RY6XCbq0BVXiBX7Sf6ORytATGWaoRMNuXyTDtyc60WxsMj-DkNs2wOQG8DXCpwEsWgRZmbGSIglnFhPYrbmLalcdWqZK_Scy9Pow


 

እንቅልፍ

 • አብዛኛውን ጊዜ አዲስ የተወለዱ ሕፃናት በየ ሁለት ሰዓቱ ጡት መጥባት ይፈልጋሉ፡፡ በአራስ ልጅ ክብካቤ ወቅትም ወላጆች አድካሚ ጊዜ ሊያሳልፉ ይችላሉ። ስለዚህ ወላጆች አስቀድመው ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ይመከራል፡፡ 

 • በተጨማሪም አዲስ የተወለዱ ሕፃናት በ24 ሰዓታት ውስጥ 18 ሰዓታቱን በእንቅልፍ ያሳልፋሉ። ስለዚህ ለወላጆች ዕረፍት የማድረጊያ ሰዓት መርሐ ግብር ማውጣት ጠቃሚ ይሆናል።

የሕፃኑን/ኗን ደኅንነት መጠበቅ

 • በተቻለ መጠን ሕፃናትን ሊያጋጥሟቸው ከሚችሉ አደጋዎች መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ትኩስ ፈሳሽ ወይም ምግብ፣ ኤሌክትሪክ፣ የተቀጣጠለ ከሰል ወይም እሳት ከሕፃኑ አካባቢ ማራቅ ይገባል። 

 • በተጨማሪም ሕፃናት አካባቢያቸውን የመቃኘት እና ባዕድ ነገር አፋቸው ውስጥ የመክተት ዝንባሌ ስለአላቸው ትኩረት በመስጠት መከታልና አካባቢን መቃኘት ያስፈልጋል።

ፀሐይ ማሞቅ

 • ሕፃናት ከተወለዱ ከ 6 ሳምንት ጀምሮ በሳምንት ቢያንስ ለ 4 ቀናት፣ ጠዋት ከ 1 - 4 ሰዓት በአለው ጊዜ ከ 15 - 30 ደቂቃ የሚሆን፣ ራቁታቸውን በማድረግ (ዐይናቸው እና ብልታቸው አካባቢ ብቻ በጨርቅ በመሸፈን) ያለምንም ቅባት ፀሐይ ላይ ማሞቅ ይገባል። 

 • የፀሐይ ብርሃን ቀጥታ ቆዳቸው ላይ ማረፍ አለበት፡፡ በመስታወት በኩል የሚያልፍ የፀሐይ ጨረር ለሕፃኑ ጠቀሜታ የለውም፡፡ የፀሐይ ብርሃን ቫይታሚን ዲ ለመሥራት ያገለግላል።

የሕፃኑን/ኗን ክትባት በአግባቡና በወቅቱ ማስከተብ

 • በጤና ተቋም ውስጥ ክትትል ማድረግ
 • ይህ ስለ ሕፃኑ ሁለንተናዊ ዕድገት፣ አመጋገብ እና ጤና ሁኔታ ከጤና ባለሙያ ጋር ለመመካከር ዕድል ይፈጥራል። 

 • በተጨማሪም የጨቅላ ሕፃናት አደገኛ ምልክቶች (ትኩሳት፣ ማስመለስ፣ ማቃሰት፣ የሆድ ድርቀት፣ ተቅማጥ፣ እምብርት አካባቢ መቅላት የመሳሰሉት) ሲከሠቱ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መውሰድ ያስፈልጋል። 

የቆዳ እንክብካቤ እና የሽንት ጨርቅ/ ዳይፐር አጠቃቀም

 • ለሕፃናት የተዘጋጁ የቆዳ ቅባቶችን መጠቀም፤ ዳይፐር እንደአስፈላጊነቱ (በቀን 4 - 6 ጊዜ) መቀየር እና ዳይፐር የሚያርፍበትን ቆዳ ቅባት ወይም ቫዝሊን መቀባት። ይህም የቆዳ ሽፍታ እና መላጥን ይከላከላል። 

ለራስ ጊዜ መስጠት

 • አንዳንድ ጊዜ ለአራስ ልጅ የሚደረግ ክብካቤ ሙሉ ጊዜን ሊወስድ እና የሥራን እና ለራስ የሚሰጥ ጊዜን ሊሻማ ይችላል።

 • ለዚህ መፍትሔ ለማግኘትና የተለያዩ አማራጮችን ለመጠቀም፤ ከቤተሰብ፣ ከሥራ ባልደረባ እና ከጓደኛ ጋር ምክክር ማድረግ ጠቃሚ ነው።

 •  በተጨማሪም የዕለት መርሐ ግብርን አስቀድሞ ማውጣት የጊዜ አጠቃቀምን ለማሻሻል በጣም ጠቃሚ ይሆናል። 

በጨቅላ ሕፃናት ላይ የሚታዩ አደገኛ የጤና ምልክቶች ምንድናቸው? 

(Danger signs of neonate)

አዲስ የተወለዱ ጨቅላ ሕፃናት ላይ ሊከሠቱ የሚችሉ አደገኛ የጤና ምልክቶችን ማወቅ አፋጣኝ የጤና ርዳታ ለማቅረብ በጣም ጠቃሚ ነው። 

 • ትኩሳት (ከ38 ዲግሪ ሴ.ግ. በላይ)

 • ጡት መጥባት መቀነስ ወይም አለመጥባት

 • ተቅማጥ (አጣዳፊ ተቅማጥ በሕፃናት ላይ)

 • ሳያቋርጡ ማልቀስ 

 • ቶሎ ቶሎ መተንፈስ / ሳል

 • ሰውነት በጣም መቀዝቀዝ (የጨቅላ ሕፃናት ሙቀት መጠን መቀነስ)

 • ረጅም ሰዓት የሚቆይ ማቃሰት 

 • ትውከት (የማያቋርጥ እና ኃይለኛ ትውከት)

 • ሆድ ከመጠን በላይ መነፋት 

 • ሰውነት መንቀጥቀጥ 

 • የዐይን ወይም ሰውነት ቢጫ መሆን 

 • ከወትሮ በተለየ መፍዘዝ፣  አለመንቃት ወይም ራስን መሳት

 • የከንፈር ወይም የምላስ መጥቆር 

 • ሕፃኑ/ኗ በተወለደ/ች በ 48 ሰዓት ውስጥ ዐይነ ምድር ከአልወጣ ወይም በ 24 ሰዓት ውስጥ ሽንት ከአልሸና/ች

 

Share the post

scroll top