Learning materials for your health  Learn

 የእከክ በሽታ (Scabies) ምንድን ነው? እንዴት ይተላለፋል? ምልክቶቹስ?

  • September 15, 2021
  • የጤና እክሎች

የእከክ በሽታ (Scabies) ሳርኮፕተስ እስኬቢ (Sarcoptes scabiei) ተብሎ በሚጠራው ተባይ አማካኝነት የሚመጣ የቆዳ በሽታ ነው፡፡ ተባዩ ስምንት እግሮች እና ነጭ ቡናማ ቀለም ያለው ለዐይን የማይታይ ነፍሳት ነው። 

ሴቷ ስኬቢስ ከቆዳ በታች ሰርስራ ገብታ ዕንቁላሎችን ትጥላለች፡፡ ዕንቁላሎቹ ከተፈለፈሉ በኋላ ወደ ቆዳው ገጽ ተመልሰው የመቦርቦር እና ዕንቁላሎችን የመጣል ዑደቱን ይቀጥላሉ፡፡ የእከክ በሽታ ከፍተኛ የማሳከክ ስሜት ስለሚፈጥር ቆዳን በመንካት ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ሊዛመት ይችላል። 

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የበሽታው ስርጭት 14.5% ነው።

የእከክ በሽታ እንዴት ይተላልፋል?

አብዛኛውን ጊዜ በሽታው ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፈው በቆዳ ንክኪ አማካኝነት ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም ብዙውን ጊዜ ልጆች ከወላጆች በንክኪ ሊያዙ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪ ልብሶችን እና ፎጣዎችን በመጋራት፣ በአንድ ቤት ውስጥ ብዙ ሆኖ በመኖር፣ እንዲሁም በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ ሊተላለፍ ይችላል።

የበሽታው ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?

የእከክ በሽታ የተለያዩ ምልክቶች አሉት። በብዛት የሚታዩት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።

  • እከክ  

ከስሙ መረዳት እንደምንችለው የበሽታው ዋና ምልክት እከክ ነው። ብዙውን ጊዜ ምሽት ላይ ወይም ደግሞ ከሙቅ ሻወር በኋላ ይባባሳል፡፡ የሚከተሉት የሰውነት ክፍሎች ከሌሎቹ በበለጠ በበሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

  • በጣቶች መካከል

  • በክርን እና በጉልበቶች ዙሪያ መተጣጠፊያ ላይ

  • በብብት ቆዳ

  • በጡት ጫፍ ዙሪያ አካባቢ

  • በወገብ ዙሪያ

  • በመቀመጫ መሃል እና በላይኛው ጭኖች አካባቢ

ብዙውን ጊዜ የጀርባ እና የጭንቅላት ቆዳን አያጠቃም።

  • ቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ (ቁስሎች) 

  • በቆዳ ላይ የሚወጣ ቀጭን የመስመር ምልክት 

ይህ ምልክት ሴቷ ተባይ ቆዳን ሰርስራ ስትገባ የሚፈጠር ነው። ምንም እንኳን እከክ የአለባቸው ሰዎች ሁሉ የሚታይ መስመር ባይኖርባቸውም፤ ይህ ምልክት ከሌሎች ምልክቶች በተለየ ከበሽታው ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው።

በተጨማሪም በሽታ የመከላከል ዐቅማቸው የተዳከመ ሰዎች (ኤች አይ ቪ በሽተኞች፣ ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች እና ሌሎች ሁኔታዎችን ጨምሮ) ከባድ ምልክት ሊኖራቸው ይችላል። ይህም “ክረስትድ እከክ” ተብሎም ይጠራል ፡፡ ክረስትድ እስኬቢስ (crusted scabis) ከተለመደው እከክ በተለየ ሁኔታ በሙሉ ሰውነት ላይ የሚሰራጭ እና ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ የሚተላለፍ በሽታ ነው።

የእከክ በሽታ ህክምና

በሽታውን የሚያመጣውን ነፍሳት ማስወገድ

ለእዚሁ አገልግሎት በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው መድኃኒት ፐርሜቲን (permethrin) ይባላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቤንዛይል ቤንዞኤት (Benzyl benzoate)፣ ሰልፈር ሎሽን (Sulfur lotion) እንዲሁም ክረስትድ እከክን ለማከም አቨርሜክቲንን (Ivermectin) እንጠቀማለን፡፡

እንደማንኛውም መድኃኒት ሁሉ እነዚህም ቅባቶች ስኬታማ እንዲሆኑ ሐኪም ባዘዘው መሠረት ወቅቱን እና ጊዜውን ጠብቀው በአግባቡ መወሰድ አለበት፡፡ በተጨማሪም ከአንገት በታች በአለው የሰውነት ቆዳ ላይ ሙሉ በሙሉ መዳረስ አለበት። 

የቤተሰብ አባላትን ማከም

ተደጋጋሚ የኢንፌክሽን ዑደትን ለማስቀረት ሲባል ምንም ዓይነት ምልክቶች ባይኖሩም እንኳን የቤተሰብ አባላት በሙሉ መድኃኒቱን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የበሽተኛውን ልብሶች፣ ፎጣዎችን እና አልጋ ልብሶችን ማጠብ ወይም በሙቅ ውሃ መቀቀል ጥሩ ሐሳብ ነው። መቀቀል ባይቻል እንኳን ቢያንስ ለሦስት ቀናት በፕላስቲክ ከረጢቶች ውስጥ ማስቀመጥ ወይም ደግሞ ፀሐይ ላይ ማስጣት ይመከራል።

ተባዮቹ ከተወገዱ በኋላ ማሳከኩ ለብዙ ሳምንታት ሊቀጥል ይችላል፡፡ የእከኩ ስሜት በጣም ከባድ ከሆነ የስቴሮይድ ክሬም ሊጀመር ይችላል፡፡

ኢንፌክሽንን ማከም

በሽታው ከታከመ በኋላ ቆዳ ብዙውን ጊዜ ያለምንም ችግር ይፈወሳል፡፡ ቆዳን በንጽሕና መጠበቅ፣ ማድረቅ እና አለመነካካት ሊከሰት የሚችለውን ተያያዥ ኢንፌክሽን ለመከላከል ይረዳል፡፡

ሆኖም ተጨማሪ የቆዳ ኢንፌክሽን ምልክቶች (ለምሳሌ መቅላት፣ እብጠት፣ መግል፣ ሕመም) ከታዩ ከሐኪም ትእዛዝ በኋላ በአፍ የሚወሰዱ የፀረ ባክቴሪያ መደኃኒቶችን ቢወስዱ ይመከራል፡፡

Share the post

scroll top