Learning materials for your health  Learn

የቆዳ አስም (የቆዳ አለርጂ) ምንድን ነው?

  • September 16, 2021
  • የጤና እክሎች

የቆዳ አስም (የቆዳ አለርጂ) የተለመደ የቆዳ በሽታ ዓይነት ሲሆን፤ ቆዳን በማድረቅ እና በማሳከክ የቆዳን ብግነት ወይም መጉረብረብ (Inflammation)  የሚያመጣ ሕመም ነው። 

ይህ በሽታ በአብዛኛው እስከ አምስት ዓመት ባሉ ሕፃናት ላይ ይከሠታል፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትም ሕፃናት ዕድሜአቸው እየጨመረ ሲሄድ ምልክቶቹ እየጠፉ ይሄዳሉ። 

ስለዚህም ብዙውን ጊዜ ይህ በሽታ አለርጂ፣ አስም ወይም ደግሞ በቤተሰብ ተመሳሳይ ችግር ባላቸው ሰዎች ላይ ይከሠታል። ስለዚህም ተመሳሳይ ችግር ከአለባቸው ወላጆች ወይም እናትና አባት የተወለዱ ሕፃናት፤ ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ የቆዳን እርጥበት የሚጠብቁ ቅባቶች ቢጠቀሙ ቢያንስ እስከ አንድ ዓመታቸው ድረስ በቆዳ አስም የመያዝ ዕድላቸው ዝቅተኛ ይሆናል።

የቆዳ አስም ምልክቶች ምንድናቸው?

ሰዎች በቆዳ አስም በሚጠቁበት ጊዜ ቆዳቸው የማሳከክ፣ የመድረቅ፣ የመሻከር፣ ዉሃ የቋጠረ ቀይ ሽፍታ እና የመቆጣት ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል። ምልክቶቹም ከሰው ወደ ሰው የማይተላለፉ ሲሆን፤ እየጠፉ ተመልሰው በመምጣትም ረጅም ጊዜ የመቆየት ጠባይ አላቸው።  

የቆዳ አስም ብዙ ጊዜ እንደ ታማሚዎች የዕድሜ ክልል የተለያየ መልክ ይኖረዋል። ለምሳሌ፡- 

  • ዕድሜያቸው ከ 2 ዓመት በታች በሆኑ ሕፃናት ላይ በእጃቸው፣ በእግራቸው፣ በጉንጭ  ወይም በጭንቅላታችቸው ላይ ይወጣል፡፡ ነገር ግን ዳይፐር (ሽንት ጨርቅ) አካባቢ ያለውን የሰውነት ክፍል ብዙውን ጊዜ አያጠቃም።

  • በትላልቅ ልጆች እና ዐዋቂዎች ላይ ብዙውን ጊዜ የአንገት አካባቢ፣ የክርን መሰንጠቂያዎችን እና የጉልበት ጀርባዎች ላይ የሚወጣ ሲሆን፤ እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ በእጅ፣ በእግር፣ በክንድ እና በፊት ላይ ሊወጣ ይችላል።

  • በትላልቅ ልጆች እና ዐዋቂዎች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ  ቆዳው እየጠነከረ ሊሄድ እና ከብዙ ማከክ የተነሣ ጠባሳ  ሊፈጥር ይችላል።

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ከአለዎት ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ሐኪምዎን ያነጋግሩ።

የቆዳ አስም እንዴት ይታከማል?

ምንም እንኳን ዘላቂ የሆነ ፈውስ ማምጣት ባይቻልም ምልክቶቹን ግን በሕክምና ማስታገስ  ይቻላል። በአንፃሩ በአግባቡ ካልታከመ የማያቋርጥ ማሳከክ እና የቆዳ ጠባሳን ሊያመጣ ይችላል። ይህም ለበሽታ አምጪ ተሐዋስያን ሊዳርግ ብሎም የቆዳ ኢንፌክሽን ሊያስከትል ይችላል። 

በአጠቃላይ የቆዳ አለርጂ ሕክምናው የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች እና መድኃኒቶችን ያካተተ ይሆናል፡፡ 

ምን ዓይነት የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ማድረግ አለብኝ?

ቆዳችን እንዳይደርቅ የቆዳን እርጥበት የሚጠብቁ ሽታ አልባ ክሬሞችን እና ቅባቶችን (Moisturizer) መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ እንዲሁም የሚከተሉትን የሐኪም ምክሮች በመተግበር አለርጂው እንዳይባባስ ማድረግ ይቻላል። እነዚህም ፡-          

  • ገላን ከመታጠብ በፊት ወይም ከታጠቡ በኋላ ወዲያውኑ የእርጥበት ክሬምን (Moisturizer) ማድረግ፡፡

  • ገላን ከታጠቡ በኋላ በለስላሳ ፎጣ በቀስታ ማድረቅ፤ በጭራሽ በፎጣ አለመፈተግ፤ኢንፌክሽን ሊያስከትል ስለሚችል መቧጠጥን ማስወገድ።

  • በጣም ሞቃት ወይም ደረቅ አየር በሚሆንበት ጊዜ ረጠብ ወይም ቀዝቀዝ ያለ ፎጣ ማድረግ፡፡

  • ጭንቀት ወይም ውጥረትን መቀነስ፡፡

  • ሻካራ ሳሙናዎች ወይም የጽዳት ምርቶችን አለመጠቀም።

  • መዓዛ  አልባ ማጽጃዎች፣ መዋቢያዎች እና ሌሎች የቆዳ እንክብካቤ ምርቶችን መጠቀም።

  • ኬሚካሎችን በሚይዙበት ጊዜ ሁሉ ጓንት እና መከላከያ ልብሶችን መልበስ።

የቆዳ አለርጂ መድኃኒቶች ምን ምንድን ናቸው?

የጤና ባለሙያው የቆዳ ማሳከክ ወይም ኢንፌክሽን ለማከም እንዲሁም ቀይ ሽፍታዎችን ለማስወገድ እንደአስፈላጊነቱ የሚከተሉትን መድኃኒቶች ሊያዝ ይችላል።  

  • እርጥበት ያላቸው ክሬሞች ወይም ቅባቶች

  • ማሳከክን የሚቀንሱ፤ አንቲ ሂስታሚን (Antihistamine)

  • የቆዳ ኢንፌክሽን ለማከም፤ አንቲባዮቲክስ (Antibiotics)

  • ማሳከክን፣ ሽፍታን፣ እብጠት እና የቆዳ መቆጣትን ለመቆጣጠር፤ ስቴሮይድ ክሬሞች እና ቅባቶች (Topical or oral steroids) ሊታዘዙ ይችላሉ።

 

Share the post

scroll top