Learning materials for your health  Learn

የአንድ ዓመት ልጄ በተሟላ ጤንነት እያደገ መሆኑን እንዴት ማወቅ እችላለሁ?

 • September 17, 2021
 • የጤና እክሎች

ልጅዎ በትክክል ማደግ አለማደጉን ለመመዘን ሐኪምዎ የልጅዎን የእድገት ደረጃ ያጠናል፡፡ ይህን ሐኪምዎ የእድገት ደረጃን ለማጥናት የሚጠቀምበት ዝርፍ ዲቨሎፕመንታል ማይል እስቶን ይባላል።

የእድገት ደረጃ (Developmental milestones) ምንድን ነው?

የእድገት ደረጃ ማለት አብዛኞቹ ልጆች በተወሰነ የዕድሜ ክልል ውስጥ ሊያከናውኗቸው የሚገባቸው ዕድሜ ተኮር ችሎታዎች ስብስብ ነው። የሕፃን ሐኪምዎ ልጅዎ በሚገባ እያደገ እንደመጣ ለመለየት የሚረዱ ነጥቦችን በውስጡ ይዞአል::

በአጠቃላይ የእድገት ደረጃ (Developmental milestones) በ አምስት ይከፈላል:: 

 1. ግሮስ ሞተር (Gross motor) ጉልህ ክሂሎቶች :- ለመቀመጥ፣ ለመቆም፣ ለመራመድ፣ ለመሮጥ፣ ወዘተ የመሳሰሉ በጉልህ የሚታዩ እንቅስቃሴዎችን  ጡንቻዎችን በመጠቀም የሚደረግ ጥረት

 2. ሶፍት ሞተር (Fine motor) ረቂቅ ክሂሎቶች :- ለመብላት፣ ለመሣል፣ ለመልበስ፣ ለመጫወት፣ ለመጻፍ እና ሌሎች ቴክኒካዊ ሥራዎችን ለመሥራት 

 3. የቋንቋ ችሎታ :- መናገር፣ የሰውነት ቋንቋን (Body Language) እና የእጅ ምልክቶችን በመጠቀም መግባባት እና ሌሎች የሚናገሩትን መገንዘብ

 4. የዕውቀት (cognitive) ችሎታዎች :- መማር፣ መረዳት፣ ችግሮችን መፍታት፣ ማመዛዘን እና ማስታወስ

 5. ማኅበራዊ ችሎታዎች :- ከቤተሰብ፣ ከጓደኞች እና ከመምህራን ጋር ግንኙነት መፍጠር 

ሕፃኑ ከተወለደበት ቀን ጀምሮ አሁን እስካለበት ዕድሜ (1 ዓመቱ) የምንጠብቀው እድገት እስከ ምንድን ነው?

በመጀመሪያው አንድ ሳምንት ሕፃኑ በተወለደበት ጊዜ ከነበረው ክብደት ከ 5% እስከ 10% ገደማ ይቀንሳል። ከ 2 ሳምንት በኋላ ግን ክብደት መጨመር እና በፍጥነት ማደግ መጀመር አለበት፡፡ እስከ አንደኛ ወር መጨረሻ ሕፃኑ በቀን 30 ግራም ክብደት እንዲጨምር ይጠበቃል፡፡ 

በመቀጠልም ከ 4 እስከ 6 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ የሕፃኑ ክብደት በተወለደበት ጊዜ ከነበረው ክብደት በእጥፍ እንዲጭምር ይጠበቃል። በአጠቃላይ በ12 ወሩ በአማካይ 10 ኪ.ግ. ይመዝናል፤ ቁመቱ ደግሞ 75 ሴ.ሜ. አካባቢ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በ 3 ወር ዕድሜው ሕፃኑ ጭንቅላቱን መደገፍ ይጀምራል፡፡ በ 6 ወሩ ደግሞ ያለ ድጋፍ ይቀመጣል፡፡ በ12 ወሩ ያለ ድጋፍ ይቆማል፡፡ ከ 3 እሰከ 4 ወር ባለው ዕድሜ ሕፃኑ ነገሮችን በእጁ መያዝ ይጀምራል፡፡ ከ 5 እስከ 6 ወሩ ደግሞ ዕቃዎችን ከእጅ ወደ እጅ ማስተላለፍ ይጀምራል፡፡ 

ማኅበራዊ እድገቱን ስናይ ደግሞ በ 6 እሰከ 8 ሳምንቱ ፈገግታ ይጀምራል፡፡ በ 4 ወሩ መሳቅ፣ ከ6 እስከ 8 ወሩ ደግሞ እንግዳ ሰው ሲያይ መጨነቅ ይጀምራል፡፡ የቋንቋ ችሎታን በተመለከተ በ 9 ወሩ 'ባባ' እና 'ማማ' ማለት ይጀምራል፤ በ 12 ወሩ ደግሞ ጥቂት ቃላትን መጠቀም ይጀምራል፡፡

ልጄ ጊዜዉን ጠብቆ እያደገ አይደለም፡፡ ምን ላድርግ?

ልጅዎ በዕድሜው ልክ ወደሚጠበቀዉ ወደ መደበኛዎቹ የእድገት ደረጃዎች ላይ ከአልደረሰ ከሐኪምዎ ጋር ይነጋገሩ።  ነገር ግን እያንዳንዱ ልጅ በተለየ ፍጥነት እንደሚያድግ ልብ ይበሉ፡፡

ልጅዎ ተደጋጋሚ እንቅስቃሴዎችን ወይም ያልተለመዱ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግ ከሆነ፤ ወይም ከሌሎች ጋር በተለይም እንክብካቤ ከሚያደርጉለት ሰዎች ጋር በደንብ የማይገናኝ ከሆነ ሐኪምዎን ያነጋግሩ። እንዲሁም ሰዎች ሲጠሩት፣ ሲያናግሩትም ሆነ ሲያጫውቱት በአግባቡ ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ የመስማት ችግር ሊኖር ስለሚችል የሕፃናት ሐኪም ያነጋግሩ፡፡

ሕፃናት በዕድሜያቸው ልክ እንዲያድጉ ከወላጆች ምን ይጠበቃል?

 • ትክክለኛ አመጋገብ ፡- ሕፃኑ እስከ 6 ወሩ የእናት ጡት ብቻ መጥባት አለበት፡፡ (ውሃ ሳይቀላቀል) ከ 6 ወር ጀምሮ ተጨማሪ ምግብ መጀመር፤ እንዲሁም እስከ 12 ወሩ የእናቱን ጡት ማጥባት መቀጠል፡፡

 • ከአመመው ቶሎ ወደ ጤና ጣቢያ መውሰድ፡፡

 • ጠዋት ጠዋት ከ 15 – 30 ደቂቃ፣ ዐይኑን እና የዘር ፍሬውን በጨርቅ ሸፍኖ፣ ምንም ዓይነት ቅባት ሳይቀባ ፀሐይ መሞቅ አለበት፡፡ ) 

 • ክትባት ጊዜውን ጠብቆ መከተብ አለበት፡፡

 • ወቅቱን ጠብቆ በሚገባ የሐኪም ክትትል ማድረግ፡፡

መደበኛ የሕክምና ጉብኝቶች ለምን ያስፈልጋሉ?

ሐኪሙ የሕፃናት ጉብኝት በሚያደርግበት ወቅት ልጅዎ እንደተጠበቀው እያደገ መሆኑን ለማወቅ ተገቢውን ምርመራ ያደርጋል፡፡ ልጅዎ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ክትባት ያገኛል፡፡ በተጨማሪም ሐኪሙ ልጅዎን እንደ ኦቲዝም ያሉ የእድገት ችግሮች ምልክቶች እንዳሉ ይፈትሻል፡፡ ስለዚህም ለልጅዎ የሕክና ክትትል ወይም ምርመራ መደበኛ ቀጠሮዎች መቼ እንደሚያደርጉ ከልጅዎ ሐኪም ጋር ይነጋገሩ፡፡

 

Share the post

scroll top