ልጄ በትክክል እያደገ መሆኑን በምን አውቃለው?
- September 17, 2021
- የጤና እክሎች
ልጅዎ በትክክል ማደግ አለማደጉን ለመመዘን ሐኪምዎ የልጅዎን የእድገት ደረጃ ያጠናል፡፡ ይህን ሐኪምዎ የእድገት ደረጃን ለማጥናት የሚጠቀምበት ዝርፍ ዲቨሎፕመንታል ማይል እስቶን ይባላል።
-
በመጀመሪያው አንድ ሳምንት ሕፃኑ በተወለደበት ጊዜ ከነበረው ክብደት ከ 5% እስከ 10% ገደማ ይቀንሳል። ከ 2 ሳምንት በኋላ ግን ክብደት መጨመር እና በፍጥነት ማደግ መጀመር አለበት፡፡ እስከ አንደኛ ወር መጨረሻ ሕፃኑ በቀን 30 ግራም ክብደት እንዲጨምር ይጠበቃል፡፡
-
በመቀጠልም ከ 4 እስከ 6 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ የሕፃኑ ክብደት በተወለደበት ጊዜ ከነበረው ክብደት በእጥፍ እንዲጭምር ይጠበቃል። በአጠቃላይ በ12 ወሩ በአማካይ 10 ኪ.ግ. ይመዝናል፤ ቁመቱ ደግሞ 75 ሴ.ሜ. አካባቢ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡
-
ከዚህ በተጨማሪ በ 3 ወር ዕድሜው ሕፃኑ ጭንቅላቱን መደገፍ ይጀምራል፡፡ በ 6 ወሩ ደግሞ ያለ ድጋፍ ይቀመጣል፡፡ በ12 ወሩ ያለ ድጋፍ ይቆማል፡፡ ከ 3 እሰከ 4 ወር ባለው ዕድሜ ሕፃኑ ነገሮችን በእጁ መያዝ ይጀምራል፡፡ ከ 5 እስከ 6 ወሩ ደግሞ ዕቃዎችን ከእጅ ወደ እጅ ማስተላለፍ ይጀምራል፡፡
-
ማኅበራዊ እድገቱን ስናይ ደግሞ በ 6 እሰከ 8 ሳምንቱ ፈገግታ ይጀምራል፡፡ በ 4 ወሩ መሳቅ፣ ከ6 እስከ 8 ወሩ ደግሞ እንግዳ ሰው ሲያይ መጨነቅ ይጀምራል፡፡ የቋንቋ ችሎታን በተመለከተ በ 9 ወሩ 'ባባ' እና 'ማማ' ማለት ይጀምራል፤ በ 12 ወሩ ደግሞ ጥቂት ቃላትን መጠቀም ይጀምራል፡፡
ስለ ዲቨሎፕመንታል ማይል እስቶን ሙሉ ማብራሪያ ለማግኘት ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ።