Learning materials for your health  Learn

የሐሞት ጠጠር ምንድንነው?

  • September 20, 2021
  • የጤና እክሎች

የሐሞት ጠጠር በሐሞት ከረጢት ውስጥ የሚፈጠሩ ትናንሽ ጠጠሮች ናቸው:: የሐሞት ከረጢት ጥቅም በሰውነታችን ውስጥ ቅባቶችን ለማዋሐድ የሚያግዝ ሐሞት የሚባል ፈሳሽ ማከማቸት እና ማመንጨት ነው፡፡ 

የሐሞት ጠጠር እንዴት ይፈጠራል?

ሐሞት በውስጡ ውሃ (97-98)% ፣  የሐሞት ጨው፣ ቢሊሩቢን እና ቅባቶችን (ኮሌስትሮል) ይይዛል። የሐሞት ፈሳሽ በጣም ብዙ ኮሌስትሮል ወይም ሌሎች ቆሻሻ ምርቶችን ከያዘ፣ እንዲሁም ሳይንቀሳቀስ ለብዙ ጊዜ ከቆየ ወደ ሐሞት ጠጠር ተቀይሮ ሊጠነክር ይችላል፡፡ ከዚያም ጠጠሩ ሐሞትን የሚያዘዋውሩ ቱቦዎችን በመዝጋት የሐሞት ፊኛ ሊያብጥ ይችላል፡፡ 

የሐሞት ጠጠር ምን ያህል ሰዎች ላይ ይከሠታል?

በአሜሪካ ውስጥ በግምት ወደ 6 ከመቶ ወንዶች እና 9 በመቶ ሴቶች ላይ ይታያል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ የሐሞት ጠጠር በሽታ በተያዙ 747 ሕሙማን ላይ በተደረገ ጥናት መሠረት፤ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በ 5 እጥፍ የመያዝ ዕድላቸው ይጨምራል፡፡ 

ለሐሞት ጠጠር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምን ምንናቸው?

  • በቤተሰብ ውስጥ የሐሞት ጠጠር ያለበት ሰው ከአለ፤

  • ሴቶች ከወንዶች ይልቅ ለዚህ በሽታ የተጋለጡ ናቸው፡፡

  • ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት፤

  • ረዘም ያለ ጾም  መጾም፤

  • በፍጥነት ክብደት መቀነስ፤

  • ዕድሜ መግፋት፤

  • ከመጠን ያለፈ ውፍረት፤

  • ነፍሰ ጡር መሆን፤

  • የወሊድ መከላከያ ክኒን መጠቀም፤ 

  • እንደ የስኳር በሽታ እና የጉበት በሽታ ያሉ በሽታዎች ሲኖሩ

የሐሞት ጠጠር ምልክቶች ምንድን ናቸው?

የሐሞት ጠጠር የአለባቸው አብዛኛዎቹ ሕመምተኞች ምንም ምልክቶች የላቸውም፡፡ ነገር ግን ምልክት ከአላቸው፤ የተለመደው ምልክት ከደረት ዝቅ ብሎ ጨጓራ አካባቢ ያለ ሕመም ስለሆነ፤ በብዛት በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ለብዙ ዓመታት ለጨጓራ በሽታ ሲታከሙ የኖሩ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቀኝ በኩል የላይኛው የሆድ ክፍል ላይ ሕመም ሊኖር ይችላል፡፡ ይህም ከ 30 ደቂቃ እስከ 6 ሰዓታት የሚቆይ የማያቋርጥ እና ከባድ የሚባል ሕመም ሲሆን ምግብ ከተመገቡ በኋላ ሕመሙ ይጨምራል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሕመሙ ወደ ጀርባ እና ትከሻ ሊሰራጭ ይችላል፡፡  ከዚህ በተጨማሪ የማቅለሽለሽ እና የማስታወክ ስሜት ሊኖር ይችላል፡፡ 

ሌሎች ምልክቶች እንደ ትኩሳት፣ የቆዳ እና የዐይን ቢጫ መሆን ከሐሞት ጠጠር ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ሊያመለክቱ ይችላሉ፡፡ አልፎ አልፎ ሌሎች ያልተለመዱ ምልክቶችም ሊታዪ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፦

  • የደረት ሕመም

  • የሆድ መነፋት

  • ቶሎ መጥገብ 

  • ቃር እና የመሳሰሉት ምልክቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከላይ የተገለጹት ምልክቶች ከታዩ ምን መደረግ አለበት?

  • በመጀመሪያ በአቅራቢያ ወደአለ ጤና ተቋም መሄድ ያፈልጋል፡፡

  • ሐኪሙ ስለ ምልክቶቹ ታካሚውን ጥያቄዎችን ይጠይቃል። 

  • በተጨማሪም አንዳንድ አስፈላጊ ምርመራዎችን ሊደርግ ይችላል፡፡ እነዚህም ምርመራዎች ኢንፌክሽን ከአለ ለመለየት እና ጉበት በትክክል እየሠራ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ የሚታዘዙ የደም ምርመራዎች ናቸው፡፡  

  • ከሁሉም በላይ ግን አስፈላጊ የሆነው ምርመራ የሆድ አልትራሳውንድ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ችግሮች አለመኖራቸውን ለማረጋገጥ  ሐኪሙ የሆድ ሲቲ ስካን ሊያዝዝ ይችላል፡፡ ነገር ግን የሐሞት ጠጠርን ለመለየት አልትራሳውንድ የበለጠ ውጤታማ ነው፡፡

የሐሞት ጠጠር እንዴት ይታከማል?

የሐሞት ጠጠር ሕክምና የሚወሰነው፤ ታካሚው ባሉበት ምልክቶች፣ በምርመራ ግኝቶች እና ከሐሞት ጠጠር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች መኖር አለመኖራቸው ከታየ በኋላ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ ሕመምተኛው ያለምንም ምልክት የሐሞት ጠጠር ብቻ ቢኖርበት ምንም ሕክምና አያስፈልገውም፡፡ ነገር ግን የሰውነትን በሽታ የመከላከል ዐቅም የሚቀንሱ እንደ ኤች.አይ.ቪ፣ ስኳርና የመሳሰሉት በሽታዎች ከአሉ፤ ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከል ሲባል ቀዶ ጥገናው ሊደረግ ይችላል፡፡ ምልክቶች ከአሉት ወይም ከሐሞት ጠጠር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች ከአሉ ደግሞ በቀዶ ጥገና የሐሞት ከረጢቱን ማስወጣት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ እስከ ቀዶ ጥገናው ግን የሕመም ማስታገሻ መድኃኒት በመስጠት ለጥቂት ቀናት ንጹሕ ፈሳሾችን ብቻ እንዲጠጡ ሊነገር ይችላል፡፡ እንዲሁም ቅባታማ ምግቦችን እንዲተው ይነገራል፡፡

ለሐሞት ጠጠር በሽተኞች የሚሠራው ቀዶ ጥገና ምን ዓይነት ነው?

ለሐሞት ጠጠር በሽተኞች በዋነኝነት የሚሠራው የቀዶ ጥገና  ዓይነት የሐሞት ከረጢቱን ከነጠጠሩ  ማውጣት ነው። ይህም በሁለት መልኩ ነው። 

  1. ላፓራኮስኮፒክ (laparoscopic) - ጫፉ ላይ ካሜራ ያለበት ቀጭን ቱቦ ወደ ሰውነት በማስገባት የሚሠራ ቀዶ ጥገና ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ቀዶ ጥገና ሰውነት ላይ ትንሽ ቀዳዳ  ብቻ ስለሚፈጥር  ቶሎ የመዳን እና ወደ መደበኛ ሥራ የመመለስ ዕድል ሰፊ ነው።  

  2.  ክፍት (open) ቀዶ ጥገና - ይህ ዓይነት ቀዶ ጥገና ደግሞ በቀኝ በኩል በላይኛው የሆድ ክፍል ላይ የሚሠራ የቀዶ ጥገና ዓይነት ነው፡፡ ከሐሞት ጠጠር ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ችግሮች ከአሉ ወይም ሐኪሙም ሰፋ ባለ ሁኔታ ለማየት የሚፈልግ ከሆነ ይህ የቀዶ ጥገና  ዓይነት ተመራጭ ይሆናል። 

ከቀዶ ጥገናው በኋላ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

  • ታካሚው ከቀዶ ጥገናው እንደወጡ ሐኪሙ የሕመም ማስታገሻ ያዝዛል፡፡ 

  • ምግብ መመገብ የሚጀምሩበትን ጊዜ ከሐኪሙ ጋር መነጋገር፡፡  መጀመሪያ ውሃ፣ ከዚያም ሻይና አጥሚት፣ በመጨረሻም መደበኛ ምግቦችን መጀመር ይቻላል፡፡ ሆድ መነፋት፣ ሕመምና ማስመለስ ከአለ ሐኪሙን ማነጋገር፡፡

  • በቀጠሮ ቀን መገኘት፡፡

 ወደ መደበኛ ሥራ የመመለሻው ጊዜ መቼ ነው?

ከላፕራኮስቲክ ቀዶ ጥገና በኋላ ብዙ ሰዎች ከ 1 እስከ 2 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ መደበኛ ሥራቸው መሄድ ይችላሉ፡፡ ታካው ክፍት ቀዶ ጥገና ከተደረገለት በኋላ ወደ መደበኛ ሥራ ከመመለሱ በፊት ምናልባት ከ 4 እስከ 6 ሳምንታት ሊወስድ ይችላል፡፡

ከሐሞት ጠጠር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮች ምንድን ናቸው?

የሐሞት ጠጠር ሕክምና ከአልተደረገለት የሐሞት ከረጢትን ቁስለት (Acute cholecystitis) ሊያስከትል ይችላል፡፡ የሐሞት ከረጢት ሲቆስል የሚያስከትለው ሕመም ከሐሞት ጠጠር ሕመም የሚለይበት ሁለት መንገዶች አሉ፡፡ 

  1. የሐሞት ከረጢት ሲቆስል የሚያስከትለው ሕመም ረዘም ያለ ጊዜ ይቆያል፡፡ ስለዚህ ሕመሙ ከ 6 ሰዓታት በላይ ከቆየ ቶሎ ወደ ሐኪም ቤት መሔድ ያስፈልጋል፡፡

  2. ምንም እንኳን በሐሞት ጠጠር ጊዜ የሆድ ሕመም ቢሰማንም የሕመሙን ትክክለኛ ቦታ ማግኘት ሊያዳግት ይችላል፡፡ የሐሞት ከረጢት ሲቆስል ግን የሕመሙን ትክክለኛ ቦታ በጣት ማመልከት ይቻላል፡፡

  3. በተጨማሪም በሽተኛው ትኩሳት፣ መንቀጥቀጥ፣ ብርድ ብርድ ማለትና ማስመለስ ይኖረዋል፡፡

በሌላ በኩል ጠጠሩ ከሐሞት ከረጢት  ወጥቶ በቧንቧው ውስጥ ሊከማች ይችላል፡፡ ይህም የሐሞት ቧንቧ ቁስለት ያመጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የዐይንና የሰውነት ቢጫ መሆን፣ የአንጀት መታጠፍ፣ የጣፊያ መቆጣትና የጉበት ሥራ ማቆም ችግር ሊያመጣ ይችላል፡፡

የሐሞት ጠጠርን በሽታ እንዴት መከላከል ይቻላል?

የሐሞት ጠጠር የመያዝ አደጋን ለመቀነስ 

  • መደበኛ የሰውነት ክብደትን መጠበቅ፤  

  • አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፤

  • አልኮል መጠጥ እና ከፍተኛ ስብ ያላቸው ምግቦችን ማስወገድ፤

  • እንዲሁም በየቀኑ ፋይበር እና ካልሲየም የያዙ ምግቦችን መመገብ፤ 

  • ከመጠን በላይ ውፍረት ከአለ ክብደት መነስ፤ ሆኖም ግን በፍጥነት ክብደት ለመቀነስ መሞከር አይመከርም፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በአቅራቢያ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን ማማከርና በጤናማ ሁኔታ ክብደት ለመቀነስ የሚያስችል ዕቅድ አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡

Share the post

scroll top