Learning materials for your health  Learn

ስለ ብጉር ምን ያህል ያውቃሉ?

  • September 21, 2021
  • የጤና እክሎች

ብጉር የቆዳ ቀዳዳዎች በሞቱ የቆዳ ሕዋሳት፣ በቅባት እና በባክቴሪያዎች ሲደፈኑ የሚፈጠር  የቆዳ ችግር ነው። ይህም ቆዳው እንዲቀላ፣ እንዲያብጥና እንዲቆጣ ያደርገዋል። በተገቢው ሁኔታ ያልታከመ ብጉር በቆዳ ላይ ጠባሳ በማምጣት የቆዳን ውበት ይቀንሳል፡፡ በዚህ የተነሣም በራስ መተማመንን ዝቅ  ሊያደርገው ይችላል።

ብጉር  በተለምዶ  በፊት፣ በግንባር፣ በደረት፣ በላይኛው ጀርባ እና ትከሻ ላይ ይወጣል።ምክንያቱም እነዚህ የቆዳ አካባቢዎች ብዙ የቅባት ዕጢዎች ስለሚኖራቸው ነው።

ለብጉር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

  • ዕድሜ፤ በተለይም በዓሥራዎቹ  የዕድሜ ክልል ውስጥ በጣም የተለመደ ነው፡፡

  • የሆርሞን ለውጦች፤ በጉርምስና  ወይም በእርግዝና ወቅት፤ 

  • በቤተሰብ ተመሳሳይ ታሪክ ካለ፤

  • የተወሰኑ መድኃኒቶች (Corticosteroids)

  • አመጋገብ፤ ከፍተኛ ቅባት ያላቸው ምግቦች ወይም ቸኮሌት አዘውትሮ መመገብ፤ ሆኖም ግን እስከአሁን ጠንካራ የሆነ ማስረጃ  አልተገኘም።

  • አንዳንድ ሕመሞች( Polycystic ovarian syndrome, Cushing syndrome)

  • ቅባት ወይም ቅባትነት የአላቸው ክሬሞች ወይም ኮስሞቲክሶች፡ ብጉር እንዲወጣ ሊያደርጉ ወይም ሊያባብሱት ይችላሉ፡፡

  • ውጥረት ወይም ጭንቀት፤  ቀደም ሲል የነበረን ብጉር የከፋ ሊያደርገው ይችላል።

ምርመራ 

በአብዛኛውን ጊዜ ብጉርን በማየት ብቻ መመርመር ይቻላል። ነገር ግን አንዳንድ የሆርሞን መዛባት በሽታዎችን (Polycystic ovarian syndrome, Cushing syndrome) ለመለየት የደም ምርመራዎች ሊደረጉ ይችላሉ።

ሕክምና

ሕክምናው በብጉሩ የደረጃ መጠን የሚወሰን ይሆናል። በመደበኛነት በቆዳ ሐኪም ክትትል ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡  ለውጡን ለማየት ቢያንስ ከሁለት እስከ ሦስት ወር ያህል ሕክምናውን መውሰድ ያስፈልጋል። ስለዚህም የጤና ባለሙያው እንደአስፈላጊነቱ የሚቀቡ ክሬሞችን ወይም የሚዋጡ መድኃኒቶችን ሊያዝ ይችላል። 

በአጠቃላይ የጤና ባለሙያው ከሚሰጠው ሕክምና በተጨማሪ በቤት ውስጥ የሚከተሉትን ማድረግ መልካም ነው።  

  • የቆዳ ንጽሕናን መጠበቅ፤ የፊት ቆዳን ማጽጃ (Soap free) በመጠቀም ሞቅ ባለ ውሃ ፊትን በቀን ሁለት ጊዜ ቀስ ብሎ ማጽዳት። ጥንክር ብሎ ቆዳን ማሸት ወይም ማጠብ፣ መቧጠጥ ብጉርን ሊያባብሰው እና የቆዳን ገጽ ሊጎዳ ይችላል። እንዲሁም ብጉርን ማፍረጥ  ወይም  መጭመቅ  ብጉርን ያባብሰዋል፡፡  ብሎም የቆዳ እብጠት እና ጠባሳ ሊያስከትል ይችላል፡፡ 

  • የቆዳ እርጥበትን መጠበቅ፤ አንዳንድ የብጉር መድኃኒቶች ቆዳን የማድረቅ እና የመፋቅ ጠባይ አላቸው። ይህንንም ለመከላከል የቆዳን እርጥበት የሚጠብቁ ክሬሞችን (non comedogenic moisturizer) መጠቀም አስፈላጊ ነው። 

  • ቅባትነት ያላቸውን ክሬሞችን እና መዋቢያ ቁሶችን አለመጠቀም፡፡

  • የፀሐይ መከላከያዎችን መጠቀም፤ ለፀሐይ የሚኖረውን ተጋላጭነትን መቀነስ እና ሰንስክሪን መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡

Share the post

scroll top