Learning materials for your health  Learn

አጣዳፊ የኩላሊት ጉዳት

  • September 22, 2021
  • የጤና እክሎች

ኩላሊት ሥራው ምንድነው?

ኩላሊት በመደበኛነት ደምን ያጣራል፡፡ እንዲሁም በደም ውስጥ ያሉትን ከመጠን በላይ ጨው፣ ውሃ እና አላስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን ያስወግዳል፡፡ 

አጣዳፊ የኩላሊት ጉዳት ማለት፤ ኩላሊት በድንገት ሥራውን እየቀነሰ ሲሄድ ወይም  በፍጥነት ሥራውን ሲያቆም  ማለት ነው፡፡ ይህም በሰውነታችን ውስጥ ከመጠን በላይ ጨው፣ ውሃ እና የማያስፈልጉ ንጥረ ነገሮች እንዲጠራቀሙ ያደርጋል። አጣዳፊ የኩላሊት ጉዳት በአግባቡ ሕክምና ከተደረገለት የኩላሊት እጥበት ደረጃ ላይ  እንኳን ቢደርስ ኩላሊት መልሶ ሙሉ ለሙሉ ሊያገግም ይችላል። አጣዳፊ የኩላሊት ጉዳት በጊዜ ሕክምና ከአልተደረገለት እስከ ኩላሊት ሥራ ማቆም ሊደርስ ይችላል።

አጣዳፊ የኩላሊት ጉዳት መንሥኤዎች

ከተለመደው የደም ዝውውር መጠን ያነሰ ደም ወደ ኩላሊት መፍሰስ

  • ይህም ከ 40 እስከ 80% ለአጣዳፊ የኩላሊት ጉዳት መንሥኤ ይሆናል፡፡ ተገቢው ሕክምና በጊዜ ከተደረገለትም በቀላሉ ሊድን ይችላል።

የደም ዝውውር መጠንን የሚቀንሱ ነገሮች ምንድናቸው?

  • ተቅማጥ፣ ትውከት  

  • የደም መፍሰስ፣ ቃጠሎ

  • ከእርግዝና ጋር የተያያዘ ደም መፍሰስ

  • የልብ ድካም፣ የጉበት በሽታ፣ የተሰራጨ የደም ኢንፌክሽን (Sepsis)                        

  • መድኃኒቶች (diuretics,NSAID)

ኩላሊት ላይ ጉዳት ሲደርስ 

 ውስጣዊ (Parenchymal) የኩላሊት ችግር         

  • የኩላሊት መቆጣት (Glomerulonephritis)
  • ኢንፌክሽን፣ ካንሰር 
  • የተወሰኑ መድኃኒቶች (antibiotics, chemotherapy)
  • የሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓት ኩላሊትን ሲያጠቃ (autoimmune diseases) 

 ሌላው መንሥኤ የሽንት ቧንቧ መዘጋት ነው ( <5%)

ይህም ሽንት ከሰውነት እንዳይወጣ በመከልከል ሽንት ኩላሊት ውስጥእንዲጠራቀም  እና  ኩላሊት እንዲጎዳ ያደርጋል።

መንሥኤ         

  • የፕሮስቴት ችግር (በወንዶች)
  • የኩላሊት ጠጠር
  • የሆድ፣ የማኅፀን፣የሽንት ቧንቧ አካባቢ  እጢ\ካንሰር

አጣዳፊ የኩላሊት ጉዳት ምልክቶች ምንድናቸው?

አንዳንድ ሰዎች ለጊዜው ምንም ዓይነት ምልክቶችን  ላያሳዩ ይችላሉ፡፡  አልያም በሆስፒታል  ውስጥ ከሆነ ያሉት በሌላ ምክንያት የተደረገ  የደም  ምርመራ  የኩላሊት ችግር እንዳለ ሊያሳይ  ይችላል፡፡

ምልክቶቹ የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ፡፡

  • የሽንት መጠን ማነስ ፣ ወይም በጭራሽ አለመሽናት፡፡ ማለትም በ 24 ሰዓት ውስጥ ከ 400 ሚሊ ሊትር ያነሰ መሽናት፡፡
  • ደም የቀላቀለ ሽንት፣ ቀይ ወይም ቡናማ የሆነ ሽንት፤
  • ሰውነት ማበጥ በተለይም እግር ኣካባቢ፤ 
  • ማስታወክ፣ የምግብ ፍላጎት አለመኖር፤
  • በቀላሉ የመድከም ስሜት፣ የማዞር ስሜት፤
  • የደረት ሕመም ወይም ግፊት
  • ያልተስተካከለ የልብ ምት
  • የትንፋሽ እጥረት

ከላይ የተጠቀሱት  ምልክቶች  ከአጋጠመዎ በቶሎ ወደ ሕክምና ተቋም  መሄድ ይኖርብዎታል። 

ምርመራ

በየተወሰነ  የጊዜ ገደብ የደም እና የሽንት ምርመራ ደጋግሞ ሊታዘዝ ይችላል። ምክያቱም  የኩላሊትን ሥራ ለመከታተል  በደም ውስጥ ያለውን  የክሬቲኒን  መጠን እና የሽንት ውጤትን ማየት ጠቃሚ ስለሆነ።

  • አልትራሳውንድ
  • የኩላሊት ራጅ
  • ከአስፈለገም የኩላሊት ናሙና  ተወስዶ ምርመራ ሊደረግ ይችላል። 

የአጣዳፊ የኩላሊት መጎዳት  ሕክምና

ሕክምናው  በ ሁለት ነገሮች ላይ ይወሰናል።  

      እነዚህም  

  • በመንሥኤውና 
  • በ ጉዳቱ ክብደት 

መንሥኤው ያነሰ ደም ወደ ኩላሊት መፍሰስ ከሆነ፤ የደም ዝውውር መጠንን የሚጨምሩ ሕክምናዎች ይደረጋሉ። 

  • የሰውነትን ፈሳሽ መተካት - በአፍ የሚወሰድ ፈሳሽ፣ በደም ስር የሚሰጥ ፈሳሽ (ግሉኮስ) ወይም ደም በመስጠት የሰውነትን ፈሳሽ መተካት ይቻላል።
  • በተጨማሪም የሚከተሉት  መድኃኒቶች ይሰጣሉ።
    • የደም ዝውውርን የሚያግዙ
    • ኩላሊት ቶሎ እንዲያገግም ሚረዱ (steroids)
  • መንሥኤው  ኢንፌክሽን ከሆነ  አንቲባዮቲክስ  ናቸው፡፡
  • መንሥኤው የሽንት ቧንቧ መዘጋት ከሆነ የዘጋውን ነገር በማስወገድ  የኩላሊት መጎዳትን ማከም ይቻላል።

 የኩላሊት እጥበት ሕክምና

የሰውነትን ፈሳሽ እና ጨው  በማስተካከል  እንዲሁም ጎጂ ንጥረ ነገሮችን በማስወገድ ኩላሊት እንደገና መሥራት እስኪጀምር  የኩላሊትን  ሥራ ይረከባል።

አጣዳፊ የኩላሊት መጎዳትን  ለመቀነስ  ምን ማድረግ አለብን?

  • የሰውነት ፈሳሽን በቂ ማድረግ፣ በቂ ውሃ መጠጣት (በቀን 2 - 2.5 ሊትር)
  • ተቅማጥ ወይም ትውከት ከአለ በአግባቡ መታከም
  • በምግብ ውስጥ ጨው መቀነስ
  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አዘውትሮ ማድረግ
  • የታወቀ የኩላሊት ሕመም ከአለ በአግባቡ መታከም
  • ከሐኪም ትእዛዝ ውጭ መድኃኒት አለመውሰድ
  • ኩላሊትን የሚጎዱ መድኃኒቶችን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለመውሰድ አለመሞከር፤ የጤና ባለሙያዎችም መስጠት የለባቸውም።
  • የሕመም ማስታገሻዎችን አዘውትሮ አለመጠቀም (paracetamol, ibuprofen)
  • ስኳር፣ ደም ግፊት እና ሌሎች ሕመሞችን በአግባቡ መታከም
  • ቋሚ የጤና ክትትል ማድረግ

Share the post

scroll top