Learning materials for your health  Learn

የኮቪድ 19 በሽታ

  • September 30, 2021
  • የጤና እክሎች

ኮሮና ቫይረስ ምንድነው?

ኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን የሚያጠቁ የተለያዩ ቫይረሶች ስብስብ ነው። ኮሮና የተባሉበትም ምክንያት፤ ከእንግሊዘኛው “ክራውን” ከሚለው ቃል በመነሣት በቫይረሶቹ የውጪ ክፍል ላይ ”ዘውድ” የመሰለ ከሰውነት ኅብረ ሕዋስ ጋር የሚጣበቅ ፕሮቲን ስለአላቸው ነው።

የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ዓይነቶች?

የሳይንስ ሊቃውንት ኮሮና ቫይረስን አልፋ (alpha)፣ ቤታ (beta)፣ ጋማ (gamma) እና ዴልታ (delta) ተብለው በሚጠሩት አራት ንኡስ ክፍሎች ከፋፍለውታል። ከእነዚህ ቫይረሶች መካከል ሰባቱ ሰዎችን ሊያጠቋቸው ይችላሉ፡፡ 

📌 229 E (አልፋ)

📌 NL 63 (አልፋ)

📌 OC 43 (ቤታ)

📌 HKU 1 (ቤታ)

📌 MERS Cov በመካከለኛው ምሥራቅ የዓለም ክፍል አካባቢ በመተንፈሻ አካላት ላይ ጉዳት አምጪ የሆነ ቤታ ቫይረስ

📌 SARS-CoV, የመተንፈሻ አካላት ላይ ከባድ ጉዳት የሚያስከትል ቤታ ቫይረስ

 📌 SARS-CoV-2 የ COVID-19 አምጪ ቫይረስ

የኮቪድ 19 በሽታ ምንድን ነው?

የኮቪድ 19 በሽታ በዋነኝነት የመተንፈሻ አካላትን የሚጎዳ፣ በአዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ አማካኝነት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ ወረርሽኙ የጀመረው በቻይና ሁቤ ግዛት ውስጥ በምትገኘው ውሃን ከተማ ውስጥ ሲሆን፤ የመጀመሪያዉ የኮቪድ 19 በሽታ (ኬዝ) የተመዘገበው በታኅሣሥ ወር 2019 እ.ኤ.አ ነው፡፡ 

ምንም እንኳን ብዙ ሰዎች መለስተኛ ምልክቶች ብቻ ቢኖራቸውም፣ አልፎ አልፎ ግን ከባድ ሕመምና ሞት ሊያስከትል ይችላል፡፡ በዕድሜ የገፉ ሰዎች፣ እንደ ስኳር እና ደም ግፊት ያሉ መሠረታዊ የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ለከባድ ሕመም ተጋላጭ ናቸው ፡፡

የተለያዩ የኮቪድ 19 ቫይረስ ዝርያዎች የሚፈጠሩት እንዴት ነው?

የኮሮና ቫይረስ ዘረመል በሙሉ አር ኤን ኤ (ሪቦኑክሊክ አሲድ) በሚባል የሕዋስ ክፍል ውስጥ ይገኛል።

ቫይረሱ እርስዎን በሚያጠቃበት ጊዜ ከሕዋስዎት ጋር ይያያዛል፡፡ በመቀጠልም ወደ ውስጥ ይገባና አር ኤን ኤ የሚባለውን የሕዋስዎን ክፍል ተመሳስሎ ይገለብጠዋል፤ ኮፒ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ቫይረሱ እንዲሰራጭ ያግዘዋል። የመገልበጥ ስሕተት ካለ አር ኤን ኤ መዋቅሩን ይቀይራል። ሳይንቲስቶች እነዚህን ለውጦች ሚውቴሽን (mutation) ብለው ይጠሩታል። ይህ ክሥተት በቫይረሶች መካከል የተለመደ ነው ።

እነዚህ ለውጦች እንዲሁ በአጋጣሚ የሚከናወኑ በመሆናቸው በአንድ ሰው ጤንነት ላይ ምንም ለውጥ ላያመጡ ይችላሉ። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ የቫይረሱን አስከፊነት ሊያባብሱት ይችላሉ። 

አንድ ቫይረስ ሰዎችን በቀላሉ እንዲያጠቃና እንዲዛመት የሚያደርግ ድንገተኛ ለውጥ ካለው ይህ ቫይረስ ይበልጥ የተለመደ ይሆናል።

ዋናው ነጥብ ኮሮና ቫይረስን ጨምሮ ሁሉም ቫይረሶች ዝርያቸውን በጊዜ ሂደት ሊቀይሩ ይችላሉ።

እኤአ ጥር 2021፣ የሕክምና ባለሙያዎች በብራዚል በሚገኙ ታማሚዎች ላይ አዲስ የኮቪድ 19 ዝርያ አግኝተዋል። ይህ ዓይነቱ ዝርያ ቀደም ሲል ከነበረው የቫይረሱ ዓይነት ይበልጥ ተላላፊ ነው፡፡ በተጨማሪም ቀደም ሲል ኮቪድ 19 የያዛቸው ሰዎችንም ሊያጠቃ ይችላል።   

እኤእ በ 2020 መገባደጃ ላይ፤ በደቡብ ምሥራቅ እንግሊዝ በሚገኙ  ኮቪድ-19 ታማሚዎች ላይ ቫይረሱ የዘረመል ለውጥ (ሚውቴሽን)  እንደሚያሳይ ባለሙያዎች አመልክተዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ሳይንቲስቶችን ጨምሮ ይህ ዓይነቱ ለውጥ ቫይረሱ በቀላሉ ሊሰራጭ እንዲችል ማድረጉን ይገምታሉ። አንዳንድ ጥናቶች ይህንን ልዩነት ለሞት ከመጋለጥ ጋር አያይዘውታል፡፡ ነገር ግን ማስረጃው ጠንካራ አይደለም።

ሌሎች የቫይረሱ ዓይነቶች ደቡብ አፍሪካንና ናይጄሪያን ጨምሮ በሌሎች ሀገራትም ተገኝተዋል። በደቡብ አፍሪካ የተገኘው የቫይረሱ ዝርያ ከመጀመሪያው ቫይረስ ይልቅ በቀላሉ ቢዛመትም የከፋ በሽታ የሚያስከትል አይመስልም።

የኮቪድ 19 በሽታ በምን መልኩ ይተላለፋል?

ኮቪድ 19 የሚተላለፍባቸዉ ሁለት ዋና ዋና መንገዶች አሉ፡፡ 

  • ቫይረሱን የያዙ ትናንሽ ጠብታዎችን እና ቅንጣቶች ወደሌሎች በመተንፈስ ወይም ወደ ውስጥ በትንፋሽ አማካኝነት በማስገባት 
  • ዐይን፣ አፍንጫን ወይም አፍን በመንካት ነው።

የበሽታው ምልክቶችን ምን ምንድን ናቸው?

የኮቪድ 19 ሕመምተኞች የሚያሳዩት ብዙ ዓይነት ምልክቶች፣ ከቀላል ምልክቶች እስከ ከባድ ሕመም ድረስ ሪፖርት ተደርገዋል፡፡ ፡ በአጠቃላይ ግን ሕመምተኞች በቫይረሱ ​​ከተያዙ ከ 2 - 14 ቀናት በኋላ የሚከተሉትን ምልክቶችን ያሳያሉ ፡፡  

  • ትኩሳት ወይም ብርድ ብርድ ማለት
  • ሳል
  • የመተንፈስ ችግር
  • ድካም
  • የጡንቻ ሕመም
  • ራስ ምታት
  • መቅመስ እና ማሽተት አለመቻል
  • ማቅለሽለሽ ወይም ማስመለስ
  • ተቅማጥ 

በዕድሜ የገፉ፣ እና እንደ የልብ፣ የሳንባ በሽታ፣ የስኳር በሽታ የመሳሰሉ ከባድ መሠረታዊ የጤና እክሎች ያሉባቸው ሰዎች የሚከተሉትን ከባድ ምልክቶች የማሳየት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡

  • የመተንፈስ ችግር
  • በደረት ውስጥ የማያቋርጥ ሕመም 
  • ራስን መሳት
  • የጣት ጫፍ እና የከንፈር ቆዳ ቀለም ወደ ግራጫ ወይም ሰማያዊ ቀለም መቀየር

እነዚህን ምልክቶች ከአዩ በፍጥነት ወደ ጤና ጣቢያ መሄድ ተገቢ ነው፡፡

የ ኮቪድ 19 ምርመራ

 በአሁኑ ወቅት የ ኮቪድ 19 ምርመራዎች ሁለት ዓይነት ናቸው፡፡

  • በሽታው በሰውየው ውስጥ መኖር አለመኖሩን የሚያሳይ ምርመራ

አሁን ላይ የቫይረስ ምርመራ ቫይረሱ መኖር አለመኖሩን የሚያሳውቅ ነው፡፡ ሁለት ዓይነት የቫይራል ምርመራዎች ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ፡፡ የኒውክሊክ አሲድ ማጉላት ምርመራዎች (NAATs) እና አንቲጂን ምርመራዎች፡፡

  • ከዚህ በፊት ሰውየው በበሽታው መያዙን የሚያሳውቅ ምርመራ  (የአንቲ ቦዲ ምርመራ)

የኮቪድ 19 መሠረታዊ የሕክምና ዓይነቶች 

ለሕክምናው ይረዳ ዘንድ የኮቪድ 19 ታማሚዎች በ 4 ይከፈላሉ።

  1. ምንም ምልክት የማያሳዩ 

  2. ቀላል  ወይም መካከለኛ የሳምባ ምች ምልክቶችን የሚያሳዩ 

  3. ከበድ ያሉ የሳምባ ምች ምልክቶችን የሚያሳዩ 

  4. ጽኑ የኮቪድ 19 ታማሚዎች 

በአጠቃላይ ዕድሜያቸው ከ 65 በላይ፣ የልብ፣ የሳምባ እና የኩላሊት በሽታ ያለባቸው፣ የስኳር ሕመምተኞች፣ ካንሰር ያለባቸው፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ሲጋራ የሚያጨሱ ከበሽታው እስኪያገግሙ ድረስ የቅርብ ክትትል ያስፈልጋቸዋል። 

የሕክምና አቀራረቡም ይህን መሠረት ያደረገ ይሆናል።

1. የበሽታ ምልክት የሌላቸው ሰዎች (80 በመቶ)፤

ሆስፒታል መተኛት የማያስፈልጋቸው ሲሆን ነገር ግን በቤታቸው ውስጥ የሚከተሉትን ማድረግ ይኖርባቸዋል። 

  • ከቤተሰብ አባላት ጋር ያለውን ግንኙነት መቀነስ
  • መገናኘት አስፈላጊም ከሆነ ሰርጂካል ጭምብል (ማስክ) መጠቀም  
  • ምልክቶቹ እየባሱ ከሆነ (መተንፈስ ማቃት፣ ትኩሳት) በቅርብ ክትትል ማድረግ፣ ቶሎ የጤና እርዳታ ማግኘት
  • በአፍ በቂ የሆነ ፈሳሽ እና የተመጣጠኑ ምግቦችን መውሰድ 
  • ሕመም ካለ የሕመም ማስታገሻ (ፓራስቴሞል) መጠቀም  

በሽታው ከያዘው ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ቢያንስ ለ 14 ቀን ከላይ የተጠቀሱትን ቢያደርጉ ይመከራል።

2. የኮቪድ 19 ቀላል ወይም መካከለኛ የሳምባ ምች ሕመምተኞች 

  • ከላይ የተጠቀሱት መከላከያዎችን ማድረግ
  • በተጨማሪ በአፍ የሚወሰዱ አንቲባዮቲክስ መድኃኒቶችን ከ 5 - 7 ቀናት እንዲወስዱ ይታዘዛሉ 

3. የኮቪድ 19 ከከባድ የሳምባ ምች ሕመም ጋር 

የጤና ባለሙያዎች ሕመምተኞቹ ያሉበትን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ ሆስፒታል በማስተኛት ኦክስጅን፣ በደም ስር የሚሰጥ ፈሳሽ፣ በደም ስር የሚሰጥ አንቲባዮቲክስ መድኃኒቶችን እንዲጀምሩ ይደረጋል። እንደሚያሳዩት የጤና መሻሻል እና የደም ምርመራ ውጤት መሠረት የመድኃኒት ለውጦች እና የጤና እንክብካቤው ይቀጥላል። 

4 ጽኑ የኮቪድ 19 ሕመምተኞች (ARDS & hypoxemic respiratory failure) 

  • እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱ ታካሚዎች ጽኑ የጤና ክትትል የሚደረግበት የጤና ተቋም ያስፈልጋቸዋል ። 
  • ታማሚዎች የሰውነታቸውን ኦክስጅን በቂ ለማድረግ የመተንፈሻ አካላቸው ርዳታ ያስፈልገዋል። ይህም በፊት ጭምብል ከሚሰጥ ኦክስጅን ጀምሮ እስከ ሳምባ ውስጥ የሚገባ የመተንፈሻ ቱቦ (Mechanical Ventilator) ሊደርስ ይችላል።  
  • በተጨማሪም በሰውነታቸው ውስጥ የተሰራጨ ኢንፌክሽን፣ የደም መርጋት ችግርና የኩላሊት መጎዳትን ለመከላከል ብሎም ለማከም የባለሙያዎችን ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል። 
  • ብዙውን ጊዜ ሕመምተኞች እዚህ ደረጃ ከደረሱ የማገገም ዕድላቸው 20 በ መቶ ይሆናል። 

ከሆስፒታል ሕክምና ጨርሶ ለመውጣት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች 

  • በታካሚው ሰውነት የበሽታ ምልክቶች ሲቀንሱ እና በላብራቶሪ ምርመራ ነፃ መሆኑ ከተረጋገጠ
  • መረጋጋት እና መመገብ ሲችል 
  • እንዲሁም የሰውነት ሙቀት መጠን ቢያንስ ለሦስት ቀናት ያለ መድኃኒት በተለመደው ክልል ውስጥ የሚቆይ ሲሆን 

ልብ ይበሉ! የሕመም ምልክቶች ከጠፉ ወይም ከቀነሱ በኋላ ታካሚዎች ለ 2 ሳምንታት አስተላላፊ ሆነው መቆየት ስለሚችሉ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። 

አጠቃላይ የመከላከያ መንገዶች

  • ሲያስሉና ሲያስነጥሱ አፍና አፍንጫዎን በክንድዎ ይሸፍኑ 
  • ከሌሎች ሰዎች ቢያንስ 6 ጫማ መራራቅ 
  • የፊት ጭምብልን (ማስክ) በአግባቡ መጠቀም 
  • እጆችዎን በሳሙና እና በውሃ ይታጠቡ፤ ሳሙና እና ውሃ ከሌለ ሳኒታይዘር ይጠቀሙ፡፡
  • የ ኮቪድ 19 ክትባት ይውሰዱ፡፡

ስለ ኮቪድ 19 በሽታ ክትባት ማወቅ ያሉብን ነገሮች ምንድን ናቸው?

የ ኮቪድ 19 ክትባቶች፤ ሰውነታችን በበሽታው እንዳይጠቃ የመከላከል ዐቅሙን እንዲፈጥርና  ኮቪድ 19ን ለሚያስከትለው ቫይረስ የበሽታ መከላከያ እንዲያዳብር ይረዱታል፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ ብዙ ዓይነት የኮቪድ 19 ክትባቶች ቢኖሩም፤ ኤፍ ዲ ኤ (Food and Drug Administration)  ያጸደቃቸው ሦስቱን ብቻ ነው። የተፈቀዱ እና የሚመከሩ የ COVID-19 ክትባቶች ውጤታማ ናቸው፡፡ እንዲሁም ለከባድ ሕመም ተጋላጭነትን ይቀንሳሉ።

 ሦስቱ ክትባቶች የሚከተሉት ናቸው።

 1. የክትባት የምርት ስም - Pfizer-BioNTech

  • ይህንን ክትባት ማን ሊያገኝ ይችላል? - ዕድሜያቸው 12 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች
  • ክትባቱን ምን ያህል ጊዜ መውሰድ ያስፈልጋል? - 2 ጊዜ በ 3 ሳምንታት (21 ቀናት) ልዮነት
  • ሙሉ መከላከል የሚያገኙት መቼ ነው? - ከሁለተኛ ክትባትዎ ከ 2 ሳምንታት በኋላ

 2. የክትባት የምርት ስም - ሞደርና

  • ይህንን ክትባት ማን ሊያገኝ ይችላል? - ዕድሜያቸው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች
  • ክትባቱን ምን ያህል ጊዜ መውሰድ ያስፈልጋል? - 2 ጊዜ በ 4 ሳምንታት (28 ቀናት) ልዮነት
  • ሙሉ መከላከል የሚያገኙት መቼ ነው? - ከሁለተኛ ክትባትዎ ከ 2 ሳምንታት በኋላ

 3. የክትባት የምርት ስም - ጆንሰን እና ጆንሰን 

  • ይህንን ክትባት ማን ሊያገኝ ይችላል? ዕድሜያቸው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች
  • ክትባቱን ምን ያህል ጊዜ መውሰድ ያስፈልጋል? - 1 ጊዜ
  • ሙሉ መከላከያ የሚሰጡት መቼ ነው? - ከክትባቱ ከ 2 ሳምንታት በኋላ

አሁን በእኛ ሀገር የዓለም የጤና ድርጅት ለድንገተኛ ጥቅም እንዲውል የሚመክረው አስትራዚንካ (Astrazeneca) የተሰኘው ክትባት እየተሰጠ ይገኛል። ይህም ክትባት ሁለት ዙር ሲኖረው፤ ከመጀመሪያው ከ8 - 12 ሳምንታት በኋላ ሁለተኛው ክትባት ይሰጣል። 90 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ላይ ከ3 - 6 ወር ያህል በሽታውን ይከላከላል ተብሎ ይታመናል።

የአስተራዜኒካ ክትባት የጎንዮሽ ጉዳቶቹ ምንድን ናቸው ?

  • ክትባቱን ከወሰዱ 10 ሰዎች መካከል ከአንድ በላይ የሚከሠቱ የጎንዮሽ ጉዳቶች:-
    • የመድኃኒቱን መርፌ የተወጋንበት ቦታ ላይ ሕመም፣ ራስ ምታት፣ ድካም፣ የጡንቻ ሕመም፣ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የመገጣጠሚያ ሕመም፣ ማቅለሽለሽ
  • ክትባቱን ከወሰዱ 10 ሰዎች መካከል ከአንድ ሰው በታች ላይ የሚታዩ:-
    • የደም ውስጥ ፕሌትሌት (platelet) መጠን መቀነስ፣ ማስታወክ፣ ተቅማጥ፣ የተወጉበት ቦታ እብጠት እና ቀይ መሆን 
  • ክትባቱን ከወሰዱ 100 ሰዎች መካከል ከአንድ ሰው በታች ላይ የሚታዩ:- 
    • የንፍፊቶች እብጠት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ ማለት፣ መፍዘዝ፣ የሆድ ሕመም፣ ሽፍታ እና ማሳከክ 
  • ክትባቱን ከወሰዱ 100,000 ሰዎች መካከል አንድ ሰው ላይ የሚታዩ:-   
    • የደም መርጋት

 በአሁኑ ጊዜ በመሠራት ላይ ያሉት ወይም ተቀባይነት ያገኙ የኮቪድ-19 ክትባቶች አዳዲስ የቫይረሱን ዝርያዎች ለመከላከል ቢያንስ የተወሰነ ጥበቃ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ክትባቶች ሰዎች የተለያዩ ፀረ እንግዳ አካላትንና ሕዋስን የሚያጠቃልል ሰፊ በሽታ የመከላከል ዐቅም እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። የበለጠ ቫይረሱ እንዳይስፋፋ እና ዝርያዎቹን እንዳያበዛ እጅግ የላቀ ጥንቃቄ እና ክትባቱን በአገኘነው አጋጣሚ መውሰድ ብቸኛው መፍትሔ ነው።

ኮቪድ 19ን በተመለከተ በብዛት የሚነሡ ጥያቄዎች

ምን ዓይነት ማስክ ማድረግ አለብን?

  • ሊታጠብ የሚችል፣  ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ንብርብሮች ያለው ጨርቅ
  • የአፍንጫዎን እና አፍዎን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን
  • ከጭንብሉ ጎንና ጎን  ክፍተት የሌለውና የአፍንጫ ሽቦ ያለው

ሕፃናት ማስክ ማረግ አለባቸው?

በአጠቃላይ ከ 5 ዓመት እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ልጆች ጭምብል ማድረግ አለባቸው፡፡

የ ኮቪድ 19 በሽታ ከሰዎች ወደ እንስሳት ሊዛመት ይችላል?

አዎ፡፡ የቤት እንስሳት፣ ድመቶች እና ውሾች የ ኮቪድ 19 ካለበት ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት ከአደረጉ በበሽታው ሊጠቁ እንዲሁም በሽታውን ወደ ሰው ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡  

ከበሽታው ከአገገሙ በኋላ በድጋሚ ሊይዝዎ ይችላል?

ሲ ዲ ሲ (Centers for Disease Control) በሠራው ጥናት መሠረት አንድ ሰው ከበሽታው ከአገገመ በኋላ በተለይ ከአገገሙ ከ 3 - 6 ወር በኋላ ባለው ጊዜ ውስጥ በድጋሜ ሊያዝ ይችላል።

 

Share the post

scroll top