Learning materials for your health  Learn

የሳንባ ነቀርሳ (የቲቢ) በሽታ

 • October 7, 2021
 • የጤና እክሎች

ቲቢ ማይኮባክቴሪየም ቱበርክሎሲስ (Mycobacterium tuberculosis) በተባለ ባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣ በሽታ ነው። የቲቢ በሽታ በዋናነት ሳንባን የሚያጠቃ ቢሆንም ከሳንባ ውጪ ማንኛውንም የሰውነት ክፍል ሊያጠቃ ይችላል። ለምሳሌ አጥንት፣ ጭንቅላት፣ አንጀትን እና ኩላሊትን ጨምሮ ሊያሳምም ይችላል።

በዓለማችን ላይ በየዓመቱ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በሳንባ ነቀርሳ (የሳንባ ቲቢ) ይታመማሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 1.5 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በቲቢ በሽታ ምክንያት ይሞታሉ ።

ይህም በዓለም ላይ ቲቢ በሽታን ከተላላፊ በሽታዎች (Communicable diseases) ውስጥ ቁጥር አንድ ገዳይ ያደርገዋል። ስለዚህ የቲቢ በሽታ በአግባቡ ካልታከመ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል። በተጨማሪም ቲቢ በኤች. አይ. ቪ ለተያዙ ሰዎች ሞት ዋነኛው መንሥኤ ነው።

የቲቢ በሽታ እንዴት ይተላለፋል?

በዓለም ጤና ድርጅት ጥናት መሠረት ከዓለም ሕዝብ አንድ አራተኛ የሚሆነው በቲቢ ባክቴሪያ እንደተጠቃ ይገመታል፡፡ ከእነዚህ  መካከል ከ 5 - 15% የሚሆኑት ሰዎች ብቻ በቲቢ በሽታ (Active TB) ይያዛሉ፡፡ ቀሪዎቹ የቲቢ ባክቴሪያ በሰውነታቸው ውስጥ ቢኖርም (Latent TB) በቲቢ በሽታ ግን አይያዙም፤ ወደ ሌላ ሰውም አያስተላልፉም። የቲቢ ባክቴሪያ ከታማሚው ሰው ወደ ሌላው ሰው በአየር ወይም በትንፋሽ አማካኝነት ይተላለፋል፡፡ 

የሳንባ ነቀርሳ ወይም የጉሮሮ ቲቢ ታማሚ ሰው ሲስል፣ ሲያስነጥስ ወይም ሲናገር የቲቢ ባክቴሪያዎች ወደ አየር ይረጫሉ። በዚህም ምክንያት በቲቢ ታማሚው አካባቢ ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉ ሰዎች (ቤተሰብ፣ የሥራ ባልደረባ እና ጓደኛ) በባክቴሪያው የመያዝ ዕድላቸው የሰፋ ነው።

ባክቴሪያው በትንፋሽ በኩል ወደ ሳንባ ከገባ በኋላ ሳንባ ውስጥ ማደግ ይጀምራል። ቀጥሎም የበሽታው መዛመት የሚወሰነው በዋነኝነት በሰውነት በሽታን የመከላከል ሥርዓት ላይ ይሆናል። 

ጤናማ የሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓት ያላቸው 90 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ኢንፌክሽኑን በመቆጣጠር በሰውነት ውስጥ እንዳይዛመት ማድረግ ይችላሉ። ነገር ግን በውስጣቸው የቲቢ ባክቴሪያ ስለአለ በሽታ የመከላከል ዐቅማቸው በሚወርድበት ወቅት በሽታው ሊከሠት ይችላል።

ቀሪዎቹ 10 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ባክቴሪያው ሳንባ ውስጥ በመራባት የሳንባ ነቀርሳ ወይም በደም አማካኝነት ወደ ሌላ የሰውነት ክፍል በመሰራጨት በቲቢ በሽታ ይታመማሉ።

በአጠቃላይ የሰውነት የመከላከል ሥርዓት (Immune system) በቂ ባልሆነ ጊዜ ግን በሽታው በቀላሉ ሊከሠት እና ሊዛመት ይችላል። ለምሳሌ

 • የኤች አይ ቪ ኤድስ ታማሚዎች፣ ካንሰር ታማሚዎች

 •  ሕፃናት

 • በዕድሜ የገፉ ሰዎች 

 • የተመጣጠነ የምግብ እጥረት የአለባቸው

 • አንዳንድ መድኃኒቶችን (Steroids) የሚወስዱ ናቸው።

 • ሌሎች የሰውነት ክፍሎችን የሚያጠቃ የቲቢ በሽታ (ኩላሊት፣ አከርካሪ አጥንት፣ አንጀት) አብዛኛውን ጊዜ ከሰው ወደ ሰው ተላላፊ አይደለም። ምክንያም እነዚህ ሰዎች ባክቴሪያውን ወደ አየር የመርጨት ዕድላቸው ዝቅተኛ ስለሆነ ነው። 

የቲቢ በሽታ የማይተላለፍባቸው መንገዶች

 • በመጨባበጥ

 • ምግብ ወይም መጠጥ በመጋራት

 • የታማሚውን ልብስ በመንካት ወይም መፀዳጃ ቤትን አንድ ላይ በመጠቀም 

 • የጥርስ ብሩሽን በመጋራት እና

 • በመሳሳም አይተላለፍም።

ለቲቢ በሽታ አጋላጭ  ምክንያቶች

 • የኤች.አይ.ቪ በሽታ ካለ

 • ዕድሜያቸው ከ 5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት

 • ስኳር በሽታ

 • አብረውት የሚኖሩት ሰው በቲቢ ከተያዘ

 • የቲቢ ክትባት ከአልተከተቡ

 • ሲጋራ ማጨስ እና አልኮል መጠጥ መጠጣት

 • የተጨናነቀ እና የኑሮ ዐቅማቸው (ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ) ዝቅ ያለ አካባቢ መኖር

 • የአደንዛዥ ዕፆች ሱስ

 • ከባድ የኩላሊት በሽታ

 • ዝቅተኛ ወይም ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት

 • የንቅለ ተከላ ቀዶ ጥገና የተደረገላቸው ሰዎች

 • የካንሰር በሽታ

 • በሽታ የመከላከል ዐቅምን የሚቀንሱ መድኃኒቶች

 • የጤና ተቋም ሠራተኛ መሆን (ተገቢውን ጥንቃቄ የማያደርጉ ከሆነ)

የቲቢ በሽታ ምልክቶች ምንድናቸው?

የቲቢ ታማሚ አብዛኛውን ጊዜ የሳንባ ነቀርሳ (Pulmonary TB) ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ምልክቶቹ እንደታመመው የሰውነት አካል ይለያያሉ።

የሳንባ ነቀርሳ ምልክቶች

 • ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ ሳል ( ሁለት ሳምንት እና ከዚያ በላይ)

 • የደረት ሕመም

 • አክታ፣ አክታው ደም የቀላቀለ ሊሆን ይችላል፡፡

የሳንባ ነቀርሳ እና ከሳንባ ውጭ ያለ የቲቢ በሽታ የሚያሳዩአቸው የጋራ ምልክቶች አሉ። እነዚህም ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩ ናቸው።

 • የድካም ስሜት

 • ክብደት መቀነስ

 • የምግብ ፍላጎት አለመኖር

 • ብርድ ብርድ ማለት

 • መካከለኛ ትኩሳት እና

 • የሚያረጥብ የለሊት ላብ ናቸው።

ሌሎች የቲቢ በሽታ (Disseminated & Extra Pulmonary) ምልክቶች በሽታው በተከሠተበት የሰውነት ክፍል ይወሰናሉ። እነዚህም እንደሚከተለው ተጠቅሰዋል። 

 የተሰራጨ ቲቢ (Disseminated TB/Miliary TB)

የቲቢ በሽታ  በደም ዝውውር አማካኝነት ከሳንባ ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ሊሰራጭ ይችላል። በተለይም ወደ አጥንት መቅኔ (Bone marrow) በመዛመት የደም ማነስ እና የፕላቴሌት ቁጥር መቀነስ ሊያመጣ ይችላል። 

በቲቢ የሚመጣ ንፍፊት (TB lymphadenitis)  

አብዛኛውን ጊዜ አንገት እና ብብት አካባቢ ሕመም አልባ ንፍፊት ይወጣል፡፡ ንፍፊቱ መግል ሊኖረው ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ጠባሳን በመተው ይድናል።

የሳንባ ሽፋን ቲቢ (TB pleuritis)

የሳንባ ሽፋን መቆጣትን በማምጣት ሳንባ ዉሃ እንዲቋጥር ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ አየር ማጠር፣ የትንፋሽ መፍጠን እና ሳል ሊኖር ይችላል። 

የቲቢ ማጅራት ገትር (TB meningitis)

የማያቋርጥ ራስ ምታት፣ የጠባይ ለውጥ፣ የነርቭ ችግር፣ በትክክል ማሰብ (ንቃተ ኅሊና) መቀነስ፣ ኮማ ውስጥ መሆን ብሎም እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል።

የአከርካሪ አጥንት ቲቢ (spinal TB)

የጀርባ ሕመም፣ ከወገብ በታች ሽባ መሆን፣ የአጥንት ስብራት እና መግል መቋጠር ናቸው። 

የአንጀት ቲቢ (Intestinal TB)

ሆድ ሕመም፣ ሰገራ መድረቅ፣ ሆድ መነፋት ወይም ማበጥ ሊያስከትል ይችላል።

የሆድ ዕቃ ሽፋን ቲቢ (TB peritonitis)

የሆድ ሕመም፣ የሆድ  እብጠት፣ አንዳንድ ጊዜ አጣዳፊ የሆድ ሕመም መኖር።

የልብ ሽፋን ቲቢ(TB pericarditis)

የልብ ሽፋን ዉሃ መቋጠርን ወይም የልብ ሽፋን ጠባሳን (Constrictive pericarditis)  በማምጣት የልብ ድካም ዓይነት ምልክቶችን (ትንፋሽ ማጠር፣ ሰውነት ማበጥ) ሊያሳይ ይችላል።

የኩላሊት እና የመራቢያ አካላት ቲቢ (Genitourinary TB)

ደም የቀላቀለ ሽንት፣ ማሕፀን ወይም ዳሌ አካባቢ ሕመም፣ መሀን መሆን፣ ከማሕፀን ውጭ እርግዝና መፈጠር ናቸው።

 የማንቁርት ቲቢ (Laryngeal TB)

ይህ የድምፅ መጎርነን ሊያስከትል ይችላል።

በአጠቃላይ ቲቢ ሁሉንም የሰውነት ክፍል ማጥቃት የሚችል ስር የሰደደ በሽታ ነው። የቲቢ ምልክቶቹም በዛው ልክ ይለያያሉ፡፡

የቲቢ በሽታ ምርመራ

የሳንባ ነቀርሳ በሽታ በሽተኛው በሚያሳያቸው ምልክቶች፣ ሐኪሙ በሚያደርገው አካላዊ ምርመራ፣ በደረት ራጅ (ኤክስ ሬይ) ምርመራ እንዲሁም በሌሎች የላብራቶሪ ምርመራዎች ይታወቃል፡፡

ከሚከተሉት ምልክቶች አንዱ በአለባቸው ሰዎች ላይ የቲቢ በሽታ መጠርጠር አለበት።

 • ያልታወቀ ክብደት መቀነስ

 • የምግብ ፍላጎት ማጣት

 • የሌሊት ላብ

 • ትኩሳት

 • ድካም

የሳንባ ነቀርሳ በሽታ በሳንባ ውስጥ ከአለ (ሳንባ)፣ ምልክቶቹ የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ።

 • ከ ሁለት ሳምንታት በላይ የቆየ ሳል

 • ደም የቀላቀለ አክታ

 • የደረት ሕመም

በሽታው ከሳንባ ውጪ ከተሰራጨ ደግሞ እንደተጎዳው አካል የተለያዩ ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል።

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች የሚታይባቸው ታካሚዎች የደረት ራጅ (ኤክስ ሬይ) መነሣት አለባቸው። ራጁ የሳንባ ነቀርሳን ከአመላከተ ደግሞ ሦስት የአክታ ናሙናዎች ለ ስሚር እና ለካልቸር ምርመራ ይቀርባሉ፡፡ እነዚህ ናሙናዎች ቢያንስ በስምንት ሰዓታት ልዩነት ጠዋት ላይ መወሰድ አለባቸው። 

የደረት ራጅ (ኤክስ ሬይ)

የደረት ራጅ ምርመራዎች በሳንባ ነቀርሳ በሽታ ለተጠረጠሩ ሰዎች በቅድሚያ ከሚታዘዙ ምርመራዎች መካከል አንዱ ነው።

በተለይ በላይኛው የሳንባ ክፍል ያለ የተጎዳ የሳንባ ክፍል እንዲሁም በመካከለኛው የደረት ክፍል ያሉ ንፍፊቶች እብጠት የሳንባ ነቀርሳን ያመለክታል።

የሳንባ ነቀርሳን ለመመርመር ናሙና የሚወሰደው ከየት ነው?

የአክታ ናሙና 

ከደረት ራጅ ሌላ የሳንባ ነቀርሳ የሚመረመርበት መንገድ የአክታ ናሙናዎችን በመውሰድ ነው። ከላይ እንደጠቀስነው ትክክለኛ ናሙና አወሳሰድ የሚባው፡- 

 • ቢያንስ ሁለት የአክታ ናሙናዎች መወሰድ አለበት።

 • እነዚህ ናሙናዎች የሚወሰዱት  ከ 8 እስከ 24 ሰዓታት ልዩነት መሆን አለበት።

 • ከ ሦስቱ ቢያንስ አንዱ አክታ ጠዋት ላይ መወሰድ አለበት።

 • ናሙናዎቹ እያንዳንዳቸው ቢያንስ 5 ሚሊ መሆን አለባቸው።

 • አክታው ከውስጥ መውጣት አለበት። በተቻለ መጠን ከምራቅ ጋር ባይደባለቅ ጥሩ ነው።

ሕመምተኛው አክታ ማውጣት ከአልቻለ ደግሞ ብሮንኮስኮፒ የሚባውን የምርመራ ዓይነት በመጠቀም ከትናንሽ የአየር ቧንቧዎች ናሙና መውሰድ ይቻላል። ይህም ብሮንዶ አልቪኦላር ላቫጅ ይባላል።

አክታ ማውጣት የማይችሉ ሕፃናት ላይ ደግሞ ሌሊቱን ጡት ሳይጠቡ አድረው በጠዋት ከ ጨጓራ ፈሳሽ ላይ ናሙና መውሰድ ይቻላል። 

ተጨማሪ ምርመራዎች

 1. የተለያዩ የሰውነት ፈሳሽ ናሙናዎች

 2. የቲሹ ናሙና (Tissue biopsy)

 3. ከሊንፍ ዕጢ የሚወሰድ ናሙና

ናሙናዎችን ለመመርመር ምን እንጠቀማለን?

የስሚር ምርመራ

የአሲድ ፋስት ስሚር ምርመራ በጣም ፈጣን እና ርካሽ የቲቢ መመርመሪያ መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን በስሚር ምርመራ ባክቴሪያዎችን ለመለየት ቢያንስ ከ 5000 እስከ 10,000 ባሲሊ በሚሊ ሊትር ውስጥ ያስፈልጋል፡፡ በተቃራኒው በካልቸር ምርመራ ባክቴሪያዎችን ለመለየት ከ 10 እስከ 100 የሚደርሱ ባሲላይ ብቻ ያስፈልጋሉ፡፡

የካልቸር ምርመራ 

ይህ ምርምራ ከናሙና ላይ ባክቴሪያዎችን በ ላብራቶሪ በማሳደግ ባክቴሪያው በ ናሙናው ውሰጥ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ነው፡፡ ምንም እንኳን ይህ መንገድ ብዙ ቀናትን ቢወስድም በተሻለ መልኩ ባክቴሪያውን ይለያል፡፡

የቲቢ  በሽታ ሕክምና

ምልክት ለሌለው ቲቢ ሕክምናው እንዴት ነው?

የቲቢ በሽታን የሚያስከትለው ባክቴሪያ በሰውነት ውስጥ ከተገኘ እና በቲቢ በሽታ ለመያዝ ተጋላጭነት ከአለ በሽታውን ለመከላከል ሕክምና ማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ሕክምና በሽታው ምልክት ማሳየት ሳይጀመር ሌላ የጤና እክል ሊያስከትሉ የሚችሉትን የቲቢ አምጪ ተዋሕስያንን ይገድላል። የተለመደው የመከላከያ ሕክምና ከስድስት እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ በቀን አንድ ፍሬ ክኒን የሚወስደው ኢሶኒያዚድ (INH) የተባለው ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት ነው፡፡ ምልክት የሌለው ቲቢ በሰውነት ውስጥ ከአለ በሽታው ወደ ሌላ ሰው አይተላለፍም ፡፡

ምልክት የሚያሳይ ቲቢ ሕክምና እንዴት ነው?

ተገቢው የቲቢ መድኃኒቶች የሚወሰዱት እና ሕክምናው የሚወስደው ጊዜ በታካሚው ዕድሜ፣ በአጠቃላይ በታካው የጤና ሁኔታ፣ የበሽታ አምጪ ባክቴሪያ መድኃኒቶችን የመቋቋም ዐቅሙ እና ኢንፌክሽኑ የተገኘበት ሰውነት ክፍል ላይ የተመሠረተ ነው ፡፡

ይህንንም መሠረት በማድረግ  ከ 6 እስከ 12 ወር የሚቆይ የፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶች በጥምረት ይወሰዳሉ፡፡ የቲቢ በሽታን ለማከም የሚወሰዱ የተለመዱት መድኃኒቶች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ፡፡

 • ኢሶኒያዚድ / Isoniazid

 • ሪፋምፒን / Rifampin

 • ኤታምቡቶል / Ethambutol

 • ፒራዝናማይድ / Pyrazinamide

እነዚህን መድኃኒቶች የሚቋቋም የቲቢ በሽታ በሰውነት ውስጥ ከአለ (MDR-TB) በአፍ የሚወሰዱ ፍሎሮኪኖሎን / fluoroquinolones የተባሉ ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒቶች ይሰጣሉ፡፡ እንዲሁም በመርፌ የሚሰጡ መድኃኒቶች ለምሳሌ፤ አሚካሲን (amikacin) ወይም ካፕሪዮማይሲን (capreomycin) በመጠቀም እስከ 9 ወራት የሚቆይ ሕክምና ይደረጋል፡፡

አንዳንድ የቲቢ ዓይነቶች እነዚህን መድኃኒቶች  የመቋቋም ዐቅምን እያዳበሩ ናቸው (XDR-TB)። ይህም የታዘዘውን መድኃኒት በአግባቡ ከአለመውሰድ  ጋር ተያይዞ የሚመጣ ነው። ቤዳኩይሊን (Bedaquiline) ሊኒዞሊድ (Linezolid) የተባሉ መድኃኒቶች ለዚህ ዓይነቱ ቲቢ እንደ አማራጭ ቀርበዋል።

 • የቫይታሚን ቢ 6 (Pyridoxine) ኢሶኒያዚድ የሚያመጣውን የእጅ እና የእግር መደንዘዝ ለመከላከል፤

 • ኮርቲኮስቴሮይድ (Corticosteroids) ሳንባን ጨምሮ ሰውነት ውስጥ የተሰራጨ ቲቢ (Miliary TB) ወይም ከሳንባ ውጪ ላለ እንደ የጭንቅላት፣ የልብ፣ የአጥንት ቲቢ ተጨማሪ ሕክምና ለመስጠት ይረዳሉ፡፡

የቲቢ ሕክምና  የጎንዮሽ ጉዳቶች

የቲቢ መድኃኒቶች ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶችን ማስከተላቸው  የተለመደ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሲከሠቱ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ መድኃኒቶች በሚወሰዱበት ጊዜ የሚከተሉት ምልክቶች ከተስተዋሉ ወዲያውኑ ሐኪምን ማነጋገር ያስፈልጋል፡፡

 • ማቅለሽለሽ ወይም ማስታወክ

 • የምግብ ፍላጎት ማጣት

 • ለቆዳዎ ቢጫ ቀለም

 • ቀለሙን የቀየረ ሽንት

 • በቀላሉ ጠባሳ መውጣት ወይም መድማት

 • የእይታ መደብዘዝ

 • በእጆች ወይም በእግሮች ላይ የመደንዘዝ ስሜት

 • የቆዳ ማሳከክ፣ ሽፍታ

ሕክምናን  ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ አስፈላጊነቱ  ምንድንነው?

ታካሚው የቲቢ ሕክምና ከጀመረ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በሽታን አስተላላፊ አይሆንም፡፡ ጥሩ የጤንነት  ስሜት ሊሰማው ይችላል፡፡ ነገር ግን የቲቢ አምጪ ተሕዋስያንን ከሰውነቱ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ወራት ስለሚፈጅ፤  በሐኪም በታዘዘው መሠረት የሕክምና ክትትሉን እና የሚወስደውን መድኃኒት በትክክል ማጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡

መድኃኒቶቹን በትክክል ጊዜውን ጠብቆ በአግባቡ መውሰድ ከአቆመ ግን ሕመሙ ያገረሽና እንደገና ይታመማል፡፡ በሽታውንም ለሌሎች ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ በተጨማሪም መድኃኒቶቹን በአግባቡ በማይወስዱበት ጊዜ የቲቢ አምጪ ተሕዋስያን መድኃኒቶቹን በመለማመድ እየተቋቋሟቸው ይመጣሉ፡፡  በሚቀጥለው የሕክምና ወቅትም በሽታውን ለማከም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ የበሽተኛውን  የመዳን ዕድል የሚቀንስ በሽታ ይከሠታል።

ይህንንም የቲቢ ዓይነት ለመከላከል ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት በቀጥታ ጤና ተቋም እየሄዱ የቲቢ መድኃኒቶችን መውሰድ እና የቅርብ ክትትል ማድረግ የግድ ይሆናል፡፡

የቲቢ መድኃኒቶችን በአግባቡ ለመውሰድ የሚጠቅሙ  ምክሮች

የቲቢ መድኃኒትን ታካሚው በራሱ መውሰድ ሲጀምር፤ መድኃኒት አወሳሰዱን ሳያቋርጥ ከመደበኛው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ጋር አብሮ በማስገባት መውሰድ አስፈላጊ  ነው፡፡ መድኃኒቱ የሚወሰድበትን ጊዜና ሁኔታ ለማስታወስ የሚረዱ አንዳንድ መንገዶች እንደሚከተለው ተገልጸዋል፡፡

 • በየቀኑ መድኃኒቱ የሚወሰድበትን ተመሳሳይ ሰዓት መመደብ፤

 • መድኃኒቱ ሲወሰድ በቀን መቁጠሪያ ካላንደር ላይ ምልክት ማድረግ፤

 • መድኃኒቶችን በቀን ለይቶ መከፋፈል የሚያስችል የክኒን ማስቀመጫ መጠቀም፤

 • ታካሚው መድኃኒቱን በሰዓቱ መውሰዱን ለማረጋገጥ በየቀኑ የቅርብ ሰው እንዲከታተልና እንዲያስታውስ ማድረግ፤

 • ታካሚው የታዘዘለትን መድኃኒት (ክኒኖችን) መውሰድ ከረሳ፤ ምን ማድረግ እንዳለበት የጤና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል፡፡

የሳንባ ነቀርሳን ለመከላከል ምን ማድረግ ይገባል?

በቅርቡ በበሽታው የተያዘ ሰው በሽታው ወደ ሌላ ሰው እንዳይሰራጭ የሚከተለውን ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡

 • የታዘዙትን የቲቢ መድኃኒቶች በአግባቡ መውሰድ፡፡

 • በሐኪሙ የሚሰጡትን ቀጠሮዎች መጠበቅ፡፡

 • በሚስሉበት ወይም በሚያስነጥሱበት ጊዜ ሁል ጊዜ አፍን በመሐረብ መሸፈን፡፡ ከዚያም መሐረቡን በአግባቡ ማስወገድ።

 • ከሳሉ ወይም ካስነጠሱ በኋላ እጅን በሚገባ መታጠብ፡፡

 • በተቻለ መጠን በቤት መቆየት፡፡

 • የሕዝብ ማመላለሻ ሲጠቀሙ መስኮት በመክፈት በቂ አየር መኖሩን ማረጋገጥ።

Share the post

scroll top