Learning materials for your health  Learn

ኮሌስትሮል ምንድን ነው? በጤና ላይ ያለው ጥቅምና ጉዳትስ?

  • September 7, 2021
  • የጤና እክሎች

ኮሌስትሮል በደም ውስጥ የሚገኝ ስብ መሳይ ንጥረ ነገር ሲሆን መጠኑ ይለያይ እንጅ በሁሉም ሰው ደም ውስጥ ይኖራል።

ሰውነታችን ኮሌስትሮልን ከየት ያገኛል?

አብዛኛውን ጊዜ ጉበት ሰውነታችን የሚፈልገውን የኮሌስትሮል መጠን ማምረት ይችላል። በተጨማሪም ኮሌስትሮልን ከምንመገበው ምግብ ውስጥ ማግኘት እንችላለን፡፡  የዶሮ እና የከብት ሥጋ እንዲሁም እንደ እንቁላል እና ወተት ያሉ የእንስሳት ተዋጽኦዎች ኮሌስትሮልን ይይዛሉ፡፡

ኮሌስትሮል ለጤናችን ምን ጥቅም አለው?

ኮሌስትሮል ለጤናችን የተለያዩ ጥቅሞችን ይሰጣል። እነዚህም፤

  • የሕዋሳትን (Cell) ሽፋኖች እና አወቃቀሮች ይሠራል። ይህም ሕዋሳትን በመጠበቅ፣ ቅርፃቸውን በመለዋወጥ የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን እንዲያስገቡ እና የሙቀት መጠንን እንዲቆጣጠሩ ይረዳቸዋል።

  • ሰውነታችን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ሆርሞኖችን ለመሥራት ኮሌስትሮልን ይጠቀማል፡፡ ለምሳሌ ኮርቲሶል (Cortisol)፣  ቴስቶስትሮን (Testosterone)፣  ፕሮጄስትሮን (Progesterone)  እና ኢስትሮጅን (Estrogen) የተባሉትን ንጥረ ነገሮች ለማዘጋጀት ያገለግላል።

  • ጉበት ሐሞትን ለማምረት ከሚፈልጋቸው ንጥረ ነገሮች አንዱ ኮሌስትሮል ነው። ሐሞት ቅባታማ ምግቦችን ለመፍጨት ያገለግላል።

  • ኮሌስትሮል ለነርቭ ሕዋሳት እንደሽፋን በመሆን ሥራቸውን ያቀላጥፍላቸዋል።  

  • ሰውነት ቫይታሚን ዲ የሚባለውን ንጥረ ነገር  ለማዘጋጀት  ኮሌስትሮልን ይጠቀማል። ይህም የፀሐይ ብርሃን ቆዳችን ላይ በሚያርፍበት ወቅት ኮሌስትሮል ወደ ቫይታሚን ዲ ይለወጣል፡፡

ኮሌስትሮል ጤናችን ላይ ጉዳት የሚያስከትለው መቼ ነው?

ኮሌስትሮል ጤናችን ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ይህ የሚወሰነው መጠኑ ከፍ ባለው የኮሌስትሮል ዓይነት እና ሌሎች ለልብ ድካም እና ለስትሮክ ተጋላጭነትን በሚጨምሩ ነገሮች ላይ ነው።

የኮሌስትሮል ዓይነቶች ይለያያሉ?

የተለያዩ የኮሌስትሮል ዓይነቶች አሉ። የጤና ባለሙያዎች ከኮሌስትሮል ምርመራ በኋላ ስለኮሌስትሮል ዓይነቶች ሲወያዩ ሊሰሙ ይችላሉ።  

  • ኤል.ዲ.ኤል. ኮሌስትሮል (LDL) - በደማቸው ውስጥ ከፍተኛ የኤል.ዲ.ኤል. ኮሌስትሮል መጠን ያላቸው ሰዎች ለልብ ድካም፣ ለስትሮክ እና ለሌሎች የጤና ችግሮች ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ዓይነቱ ኮሌስትሮል  “መጥፎ ኮሌስትሮል” (Bad cholesterol) በመባል ይታወቃል።

  • ኤች.ዲ.ኤል. ኮሌስትሮል (HDL) -   ከፍተኛ የኤች.ዲ.ኤል. ኮሌስትሮል መጠን ያላቸው ሰዎች በተቃራኒው  በልብ ድካም፣ በስትሮክ ሕመም እና በሌሎች የጤና ችግሮች የመያዝ ዕድላቸው ዝቅተኛ  ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ዓይነቱ ኮሌስትሮል  “ጥሩ ኮሌስትሮል ” (Good cholesterol) በመባል ይታወቃል።

  • ኤች.ዲ.ኤል ያልሆነ ኮሌስትሮል (Non-HDL cholesterol) - ይህ ከጠቅላላ ኮሌስትሮል  ኤች.ዲ.ኤል ኮሌስትሮል  ሲቀነስ የሚገኘው ነው፡፡

  • ጠቅላላ ኮሌስትሮል (Total cholesterol)

  • ትራይግላይሰርሳይድ(Triglyceride) -  ይህ ከኮሌስትሮል ዓይነቶች አንዱ ባይሆንም ነገር ግን ብዙ ጊዜ ከኮሌስትሮል ጋር አብሮ ይሠራል፡፡ ከፍተኛ የትራይግላይሰርሳይድ መጠን እንዲሁ  ለልብ ድካም እና ለስትሮክ ተጋላጭነትን ይጨምራል።

የኮሌስትሮል መጠን ቁጥር ጤናማ የሚባለው ምን ያህል ሲሆን ነው?

ይህ በታማሚው ዕድሜ፣ ፆታ እና አጠቃላይ ባለው የጤና ሁኔታ ላይ የሚወሰን ይሆናል። ስለዚህ ከጤና ባለሙያ ጋር መነጋገር አስፈላጊ ይሆናል።

  • አጠቃላይ ኮሌስትሮል (Total cholesterol) ከ 200 በታች

  • ኤል.ዲ.ኤል. ኮሌስትሮል (LDL)  ከ 130 በታች  

  • ኤች.ዲ.ኤል. ኮሌስትሮል (HDL)ከ 60 በላይ መሆን አለበት፡፡

  • ኤች.ዲ.ኤል ያልሆነ ኮሌስትሮል (Non-HDL cholesterol) ከ 160 በታች 

  • ትሪግሊሰሪይድስ (Triglyceride) ከ 150 በታች

በአጠቃላይ ለልብ ድካም ወይም ለስትሮክ እና ለሌሎች ሕመሞች ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች የኮሌስትሮል መጠናቸውን ከዚህም በታች በጣም መቀነስ ይኖርባቸዋል።

ሌሎች አጋላጭ ሁኔታዎች ከከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን ጋር ሲደመሩ የልብ ሕመም፣ ስትሮክ እና ሌሎች ሕመሞች የሚያመጡ ምንድናቸው?

  •  ሲጋራ ማጨስ

  • ከፍተኛ የደም ግፊት

  • የስኳር ሕመም

  • በቤተሰብ የልብ ሕመም መኖር

  • የዕድሜ መግፋት

  • ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ -  ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችን እና  እንደ ዓሣ  ያሉ ጤናማ ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች አለማዘውተር ወይም አለመመገብ፡፡ እንዲሁም ስኳር እና  ሌሎች ጤናማ ያልሆኑ ቅባቶችን መጠቀም ናቸው። 

የኮሌስትሮል ምርመራ ምንድነው?

ምርመራ የሚደረገው የደም ናሙናን በመውሰድ ነው። የደም ናሙና ከመወሰዱ በፊት ግን ቢያንስ ከ9 እስከ 12 ሰዓታት መፆም ያስፈልጋል። ስለዚህ ምርመራው ጠዋት ቢደረግ ይመረጣል።

 የኮሌስትሮል ሕክምና

 ሕክምናው የአኗኗር ዘይቤዎችን መቀየር እና ምድኃኒቶችን ሊያካትት ይችላል።

በአጠቃላይ የሚከተሉት ችግሮች ከአሉ የጤና ባለሙያዎች የኮሌስትሮል መድኃኒት (Statin) እንዲጀምሩ ሊያደርጉ ይችላሉ።

  • ቀድሞውኑ የልብ ድካም ወይም ስትሮክ ተከሥቶ ከነበረ

  • የታወቀ የልብ በሽታ ከአለ

  • የስኳር በሽታ 

  • በቅባት ክምችት ምክንያት የሚመጣ የደም ቧንቧ በሽታ ከአለ (PAD,IHD)

የኮሌስትሮልን መጠን ሊቀንሱ የሚችሉ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ምንድናቸው?

●        የአመጋገብ ለውጥ ማድረግ

  • ቀይ ስጋን፣ ቅቤ፣ የተጠበሰ ምግብ፣ አይብ እና ሌሎች ስብነት ያላቸውን ምግቦች ማስወገድ

  • ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችን እና  እንደ ዓሣ  ያሉ ጤናማ ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች ማዘውተር

●        የሰውነት ክብደትን ጤናማ ማድረግ

●         ቢያንስ በሳምንት 4 ቀን ለግማሽ ሰዓት የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ (ፈጣን እርምጃ ሊሆን ይችላል)

●        ሲጋራ ማጨስ ማቆም

●        አልኮሆል መጠጥን መቀነስ

●        በሐኪም የታዘዘን መድኃኒት በአግባቡ መውሰድ እና ቋሚ የጤና ክትትል ማድረግ ናቸው።

በአጠቃላይ እነዚህን ማድረግ የኮሌስትሮል ሕመም ባይኖር እንኳን እንዳይከሠት ለመከላከል ይጠቅማሉ። 

Share the post

scroll top