Learning materials for your health  Learn

የጡት ካንሰር (Breast Cancer)

  • October 19, 2021
  • የጤና እክሎች

የጡት ካንሰር ከቁጥጥር ውጭ በሆነ ዕድገት እና በጡት ኅብረ ሕዋስ ላይ በሚከሠቱ ለውጦች ምክንያት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ሁለተኛው የተለመደ የካንሰር መንሥኤ ሲሆን በማደግ ላይ በአሉ ሃገራትም  እየጨመረ የመጣ  አሳሳቢ የጤና እክል ነው።  እ.ኤ.አ. በ 2018 የተደረገ ጥናት ወደ 2.1 ሚሊዮን  የሚጠጉ ሴቶች የጡት ካንሰር በሽታ እንደተገኘባቸው ያሳያል።  ከ 8 ሴቶች መካከል አንዷ (13%) በሕይወት ዘመኗ  በጡት ካንሰር በሽታ የመያዝ ዕድል ሲኖራት፤ ከ 39 ሴቶች መካከል አንዷ (3%) ደግሞ በዚህ በሽታ ምክንያት ለሞት ትዳረጋለች፡፡

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እ.ኤ.አ በ2018 እንደአወጣው  ዘገባ፣ በኢትዮጵያ  ውስጥ የጡት ካንሰር  በፈጣን ሁኔታ እያደገ ነው፡፡ ከሁሉም የካንሰር ዓይነቶች 22.6 በመቶ የሚሆነውን የሚያካትት ቀዳሚ የካንሰር መንሥኤም ሲሆን ከ100 ሺሕ ሕዝቦቿ  ውስጥ 22.9 የሚሆኑትን በዚህ በሽታ ምክንያት ታጣለች።

የጡት ካንሰር በአብዛኛው በሴቶች ላይ የሚከሠት በሽታ ቢሆንም፤ በወንዶችም ላይ የመከሠት ዕድል አለው።

የጡት ካንሰር ምልክቶች

የጡት ካንሰር  ምልክቶች በሁሉም ሰው ላይ ተመሳሳይ አይደሉም፡፡ አንዳንድ  ሰዎች  የከፋ ደረጃ እስከሚደርስ ምንም  ምልክቶች ላያሳዩ ይችላሉ። ስለዚህም መደበኛ የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ በተገቢው ማድረግ ጥቅሙ የላቀ ነው።

አንዳንድ  የጡት  ካንሰር ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

  • በጡት ወይም በብብት ውስጥ የሚወጣ እብጠት 

  • የሁለቱ ጡቶች መጠን መለያየት 

  • የጡት ቆዳ መቆጣት፣ መሰርጎድ፣ መቁሰል ወይም ነጠብጣቦች መኖር

  • በጡት ጫፍ አካባቢ  መቅላት ወይም የቆዳ መፈርፈር

  • የጡት ጫፉ ወደ ውስጥ መግባት 

  • የጡት ጫፍ አካባቢ ሕመም  

  • ከጡት ጫፍ የሚወጣ ፈሳሽ 

  • በጡት መጠን ወይም  ቅርፅ ላይ የሚኖር ማንኛውም ለውጥ።

እነዚህ ምልክቶች የወር አበባ በሚታይበት ወቅት፣ ልጅ በመውለድ፣ ክብደት በመቀነስ ወይም በመጨመር፣  የተወሰኑ መድኃኒቶችን በመውሰድ እና ሌሎች ካንሰር ባልሆኑ የጡት እክሎች ምክንያት ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ምልክቶች አሉ ማለት ካንሰር ነው ማለት እንዳልሆነ መረዳ ይገባል፡፡ የሚያሳስብዎትን ማንኛውም ምልክት ከአስተዋሉ ግን ሐኪሞዎን ማነጋገር ያስፈልጋል። 

ለጡት ካንሰር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምን ምንድን ናቸው?

ለጡት ካንሰር የሚያጋልጡ፤ የሚሻሻሉም ሆነ የማይሻሻሉ ብዙ አጋላጭ ሁኔታዎች አሉ። ይህ ማለት ግን እነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች ያለበት ሰው ሁሉ የጡት ካንሰር ተጠቂ ይሆናል ማለት አይደለም። ይልቁንም እነዚህን አጋላጭ ሁኔታዎች ቀድመን ማወቅ በዋነኝነት የሚጠቅመን፤ ሊሻሻሉ የሚችሉትን አጋላጭ ሁኔታዎች ለመከላከል እና መቼ የቅድመ ምርመራ ማድረግ እንዳለብን ለማወቅ ነው። የጤና ባለሙያዎችም ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለይቶ ቅድመ ምርመራ ወይም ሌሎች የመከላከያ እርምጃዎችን ለመጠቆም ይጠቀሙበታል። 

ሌላው ማወቅ ያለብን ነገር እነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች ሳይኖራቸው በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች እንዳሉ ነው፡፡ ስለዚህም ለጡት ካንሰር ዝቅተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ እንኳን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እና ቅድመ ምርመራን መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡

ለዚህም እንዲያመች በሚል እነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች መሻሻል የሚችሉ እና የማይችሉ ተብለው በ ሁለት ይከፈላሉ።

መሻሻል የማይችሉ አጋላጭ ሁኔታዎች የሚባሉት 

  • ዕድሜ - ለአብዛኛዎቹ ሴቶች ዋነኛው አጋላጭ ሁኔታ ዕድሜ ነው፡፡  ከ 45 እስከ 50 ዓመት ድረስ የጡት ካንሰር በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፡፡ በአንፃሩ ከ 80 ዓመት በኋላ የመከሠቱ ሁኔታ ማሽቆልቆል ይጀምራል።
  • ፆታ - የጡት ካንሰር ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ የመከሠት ዕድሉ በ 100 እጥፍ ይበልጣል፡፡
  • ዘር / ቀለም - በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ነጭ ሴቶች በከፍተኛ ደረጃ የጡት ካንሰር ተጠቂ ናቸው። በአንፃሩ በ ጥቁር አሜሪካውያንና ሕንዶች ላይ የጡት ካንሰር መጠን ዝቅተኛ ነው፡፡ 
  • ክብደት - የክብደት መጨመር እና ከመጠን በላይ ውፍረት ብዙውን ጊዜ ከወር አበባ ማረጥ በኋላ የሚመጣውን የጡት ካንሰር ይጨምረዋል፡፡ 

ከዚህ በፊት የጡት ካንሰር ይዞዎት ከነበረ ድጋሚ የመያዝ ዕድልዎ ከፍተኛ ነው።

በቤተሰብ ውስጥ (እናት ወይም ሴት ልጅ) የጡት ካንሰር ተጠቂ ከሆኑ / ከነበሩ - በጡት ካንሰር ከተያዙ ሴቶች ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር የተጠቃ እናት ወይም እኅት አላቸው። ለዚህም ዋና ምክንያቱ BRCA1 እና BRCA2 በመባል የሚታወቀው በዘር የሚተላለፍ የዘረመል ለውጥ ነው፡፡ BRCA1 ወይም BRCA2 የዘረመል ለውጥ ያላቸው ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከ 50 እስከ 85 በመቶ ይደርሳል።

መሻሻል የሚችሉ አጋላጭ ሁኔታዎች የሚባሉት 

የወር አበባ ማየት ቀድመው የጀመሩ እና ቆይተው ያረጡ ሴቶች የጡት ካንሰር ተጋላጭነታቸው ይጨምራል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ኤስትሮጅን ለሚባል ሆርሞን ለረጅም ዕድሜ ስለሚጋለጡ ነው። 

  • ያልወለዱ ሴቶች - እርግዝና እና ጡት ማጥባት የጡት ካንሰርን ይቀንሳል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ ልጅ መውለድ እና የመጀመሪያ ልጅ የወለድንበት ዕድሜ ማነስም እንዲሁ በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልን ይቀንሳል። 
  • ከማረጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ምልክቶችን ለመቀነስ ተብለው የሚሰጡ የሆርሞን መድኃኒቶች በጡት ካንሰር የመያዝን ዕድል ይጨምራሉ። 
  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ 
  • ትምባሆ ማጨስ 
  • አልኮል አብዝቶ መጠቀም
  • የአመጋገብ ዘይቤ - አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አትክልት መመገብ በጡት ካንሰር የመጋለጥ ዕድልን የሚቀንስ ሲሆን፤ በአንፃሩ ሥጋ እና ስብ (ጮማ፣ ቅባት) አብዝቶ መጠቀም ደግሞ ይጨምራል።
  • ለአዮናይዚንግ ጨረር መጋለጥ - በተለያየ ምክንያት በተለይ በሕፃንነት ዕድሜያቸው ለአዮናይዚንግ ጨረር የተጋለጡ ሰዎች በጡት ካንሰር የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ ለሌላ የካንሰር ሕክምና ወይም ደግሞ ከአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ የተረፉ ሰዎች በማንኛውም ካንሰር የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው።

የጡት ካንሰር እንዴት ይታከማል?  

የጡት ካንሰር ያለባቸው ሰዎች  ከሚከተሉት ሕክምናዎች ውስጥ በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑት ይታከማሉ፡፡

ቀዶ ጥገና -  የጡት ካንሰር አብዛኛውን ጊዜ ካንሰሩን ለማስወገድ በቀዶ ሕክምና ይታከማል፡፡ ብዙ ዓይነት የጡት ካንሰር  ቀዶ ጥገና ሕክምናዎች ቢኖሩም በአጠቃላይ በሁለት   ይከፈላሉ፡፡ 

  • ማስቴክቶሚ (mastectomy) ካንሰር የተገኘበትን ጡት ሙሉ በሙሉ ቆርጦ በማስወገድ የሚካሄድ ቀዶ ጥገና፡፡  

  • ለምፔክቶሚ (lumpectomy) እና ኳድራንቴክቶሚ (quadrantectomy) ካንሰር ያለበትን ኅብረሕዋስ ወይም የተወሰነ የጡት ክፍል ብቻ በማውጣት የተቀረው ክፍል የማይነካበት የቀዶ ጥገና አማራጭ ነው፡፡ ይህንን አማራጭ የሚመርጡ ሴቶች ብዙውን ጊዜ ከቀዶ ጥገናው በኋላ የጨረር ሕክምና ሊኖራቸው ይገባል።

የጨረር ሕክምና (radiation therapy) -  ጨረር የካንሰር ሕዋሶችን  ይገድላል፡፡ 

ኬሞቴራፒ (chemotherapy) - ኬሞቴራፒ የካንሰር ሴሎችን የሚገድሉ መድኃኒቶችን በቡድን ለመግለጽ የሚጠቅም ቃል ነው፡፡ አንዳንድ ሴቶች የካንሰር መጠንን ለመቀነስ፣  ለማስወገድ እና ቀለል እንዲል ለማድረግ ከቀዶ ጥገናው በፊት እነዚህን መድኃኒቶች ይወስዳሉ፡፡ አንዳንድ ሴቶች ደግሞ ካንሰር እንዳያድግ፣ እንዳይሰራጭ ወይም ተመልሶ እንዳይመጣ ከቀዶ ጥገናው በኋላ እነዚህን መድኃኒቶች ይወስዳሉ፡፡

የሆርሞን ሕክምና (hormonal therapy) - አንዳንድ የጡት ካንሰር ዓይነቶች በተለያዩ ሆርሞኖች ምክንያት ይባባሳሉ፡፡ እነዚህን ሆርሞኖች ለማገድ ወይም ሰውነት አንዳንድ ዓይነት ሆርሞኖችን እንዳያመርት ለመከላከል የሚሰጡ ሕክምናዎች አሉ፡፡

ከሕክምናው በኋላ ማወቅ የሚያስፈልጉ ነገሮች 

ከሕክምናው በኋላ ካንሰሩ ተመልሶ ይከሠት እንደሆነ ለማወቅ በየጊዜው ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል። 

እንዲሁም  ካንሰሩ ተመልሷል ለማለት የሚያስችሉ ምልክቶችን አስተውሎ መከታተል  ይገባል፡፡ ከእነዚህ  ምልክቶች  መካከል የተወሰኑት፤ 

  • በጡት አካባቢ አዳዲስ ጉብታዎች 

  • ሕመም (በአጥንቶች፣ በደረት ወይም በሆድ ውስጥ) 

  • የመተንፈስ ችግር እና 

  • ራስ ምታት ናቸው ፡፡ 

ማንኛውንም አዲስ ምልክት ካስተዋሉ ለሐኪም ማማከር ያስፈልጋል፡፡

ካንሰር ከተመለሰ ወይም ከተስፋፋ ምን ዓይነት የሕክምና አማራጮች አሉ?  

ካንሰሩ የተመለሰበት ወይም የተሰራጨበት የአካል ክፍል ይወስነዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ሰዎች የሆርሞን ሕክምና ወይም ኬሞቴራፒ ይደረግላቸዋል፡፡ የተቀሩት ደግሞ አዳዲስ ዕጢዎችን ለማስወገድ የቀዶ ጥገና ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡

የጡት ካንሰርን እንዴት መከላከል ይቻላል?

ቅድመ ምርመራ ማድረግ - ይህም በጡት ካንሰር የመያዝ አደጋን ባይቀንስ እንኳን በሽታው ቶሎ ታውቆ ተገቢውን ሕክምና ለመስጠት ስለሚያስችል በጡት ካንሰር የመሞትን አደጋ በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ 

የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች

በርካታ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ለጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ሊቀንሱ ይችላሉ።

  • 30 ዓመት በፊት የመጀመሪያ ልጅ መውለድ
  • ቢያንስ ለስድስት ወር ጡት ማጥባት
  • ከወር አበባ ማረጥ በኋላ የሆርሞን ሕክምናን አለመጠቀም፤ ወይም ለተወሰነ ጊዜ ብቻ መጠቀም 
  • ከአላስፈላጊ ጨረር ራስን መጠበቅ፤ ለምሳሌ የማያስፈልግ የ ሲቲ ስካን ምርመራ ከማድረግ መቆጠብ፡፡
  • ሲጋራ አለማጨስ
  • የአልኮል መጠጥን መገደብ
  • ጤናማ ክብደት መኖር
  • ንቁ የአኗኗር ዘይቤን መከተል፡፡ ይህም የአካል እንቅስቃሴ መሥራትን ያጠቃልላል።

የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ (Breast cancer screening)

የጡት ካንሰር ሕመም ቀደም ብሎ ከታወቀ በሕክምና የመፈወስ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ የቅድመ ምርመራ ዓላማ የጡት ካንሰር በመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንዳለ ሳይስፋፋ ለማወቅና አስፈላጊውን የሕክምና መፍትሔ ለማወቅ ነው። 

በአሜሪካ ውስጥ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ፤ የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ለአለፉት ጥቂት ዓሥርት ዓመታት በጡት ካንሰር የመሞት ዕድልን በአንድ ሦስተኛ ያህል ቀንሷል፡፡ 

ለጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ የተለያዩ የሕክምና ዘዴዎች አሉ። እነዚህም፡-

1 - ማሞግራፊ (Mammography)

ማሞግራፊ ማለት በሌላ አገላለፅ የጡት ራጅ ማለት ነው፡፡ ይህ ምርመራ በጡት ካንሰር የመሞትን አደጋ ለመቀነስ የተሻለ የቅድመ ምርመራ ዓይነት ነው፡፡ ምርመራው ሁለቱንም ጡቶች የሚያካትት ሲሆን፤ የሚወስደውም ለጥቂት ሴኮንዶች ብቻ ነው። 

ምርመራው የወር አበባ በመጣበት ሰሞን ባይደረግ ይመከራል። ይህም በምርመራው ምክንያት የሚያጋጥም የጡት ሕመምን ለመቀነስ ነው። በተጨማሪም በምርመራው ወቅት የብብት ዲኦድራንቶች ወይም ክሬሞችን ባያደርጉ ይመረጣል።

የራጁ ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርስ ሲሆን፤ ስለውጤቱ ከጤና ባለሙያ ጋር በመነጋገር ስለጡቶቹ የጤና ሁኔታ መረጃ ማግኘት እጅግ ጠቃሚ ነው።

አንዳንድ ጊዜ የራጁ ውጤት ጡት ላይ ችግር እንዳለ ሊያሳይ ይችላል። ነገር ግን ይህ ምርመራ በወጣቶች ላይ ብዙም ተግባራዊ አይሆንም። በአሜሪካ ውስጥ በተደረገ ጥናት 90 በመቶ የሚሆኑት ችግር የሚያሳዩ የራጅ ውጤቶች የጡት ካንሰር የላቸውም። ነገር ግን እንደሁኔታው ተጨማሪ ምርመራ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

ቅድመ ምርመራው በየትኛው ዕድሜ መጀመር አለበት?

በአጠቃላይ ዕድሜአቸው 50 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሴቶች ቢያንስ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ይህን ምርመራ ቢያደርጉ ይመከራል።

ዕድሜአቸው ከ 40 - 49 ዓመት የሆኑ ሴቶች የሚከተሉትን ነጥቦች በማመዛዘን ቅድመ ምርመራውን እንዲጀምሩ ይደረጋል።  

                - ሴቷ ቅድመ ምርመራ መጀመር የምትፈልግ ከሆነ

                - ስለቅድመ ምርመራው ጥቅምና ጉዳት በቂ ግንዛቤ አላት ወይ?

ስለሆነም ስለምርመራው ከጤና ባለሙያ ጋር ተገቢ ምክክር ከተደረገ በኋላ መቼ ምርመራ መጀመር እንዳለበት ውሳኔ ቢደረስ ጠቃሚ ይሆናል።

ልብ ይበሉ፤ ለጡት ካንሰር የሚያጋልጥ የዘረመል ችግር (BRCA1,BRCA2) ያለባቸው ሴቶች ወይም ተመሳሳይ የቤተሰብ ሕመም ያላቸው፣ ከ 30 ዓመታቸው በፊት የደረት ጨረር ሕክምና የወሰዱ፤ ከላይ ከተጠቀሰው ዕድሜ ቀደም ብለው የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ መጀመር ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ወጣቶች ከፍተኛ የጡት መጠን ስለአላቸው ኤም አር አይ እና አልትራሳውንድ መጠቀም የተሻለ ይሆናል።

2 - በጤና ባለሙያ የሚደረግ የጡት ምርመራ

ይህ በጤና ባለሙያ ማለትም በሐኪም ወይም በነርስ ጡትን በመዳሰስ የሚደረግ የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ዓይነት ነው። 

በመደበኛነት የጤና ባለሙያዎች እንደዚህ ዓይነት የጡት ምርመራ እንዲያደርጉ አይመከርም። ነገር ግን በጡት ራጅ ወቅት ከሆነ ምርመራው የተደረገው ስለጡት ጤና የሚሰጡት መረጃ እጅግ ጠቃሚ ይሆናል።

3 - የራስን ጡት መመርመር (Self - breast examination)

ይህ የራስን ጡት በመዳሰስ እና በመፈተሽ ጡት ላይ ከወትሮ ለየት ያለ ለውጥ ከመጣ ለማወቅ ይረዳል። ራስን መፈተሽ በራስ ጡቶች ላይ ለውጦችን የማግኘት መንገድ ነው ፡፡ 

ጡታችንን እንዴት አድርገን እየዳበስን እንመርምር?

የወር አበባ የምታይ ሴት ከሆነች የወር አበባዋ ከተጠናቀቀ በሳምንቱ ምርመራውን ብታደርግ ይመረጣል። 

  • ሁለቱንም እጆች ከጎን በማድረግ ቀጥ ብለው መስታወት ፊት ለፊት በመቆም ምርመራውን መጀመር ይመረጣል፡፡ ከዚያም የጡትን ቆዳ ቀለም መቀየር ወይም ቆዳ ላይ የተለየ ለውጥ መኖሩን ለማስተዋል መሞከር፡፡ በመቀጠልም የጡት ጫፎች ወደ ውስጥ መግባታቸውን ወይም ወደላይ  መሳባቸውን ለማየት መሞከር፡፡ 

  • ቀጥሎም በጀርባ በመተኛት የግራ እጅን ከጭንቅላት በላይ ማኖር። በቀኝ እጅ የመሐል ሦስት ጣቶች  የግራ ጡትን ከብብት ጀምሮ ከላይ ወደታች ክብ በሆነ አኳኋን መዳሰስ። ይህም የእጃችንን ኃይል እየቀያየርን ጡታችንን ሦስት ጊዜ በደንብ መዳሰስ ያስፈልጋል።  ከዚያም የጡት ጫፍን በመደሳስ ለውጥ መኖሩን ወይም የሚወጣ ፈሳሽ ካለ ማየት ይኖርብናል። በመጨረሻም እጅን በመቀየር  በሌላኛው ጡት ላይ ተመሳሳይ  ምርመራን ማድረግ

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የራስን ጡት በመመርመር ብቻ በጡት ካንሰር የመሞት ዕድልን መቀነስ አይቻልም፡፡ ስለሆነም የራስ ጡት ምርመራ ከሌሎች እንደ ጡት ራጅ ካሉ ቅድመ ምርመራዎች ጋር አብሮ  መጣመር ይኖርበታል።

Share the post

scroll top