Get detailed information about your health.  Learn

ለጡት ካንሰር የሚያጋልጡ ሁኔታዎች እና መከላከያ መንገዶች

 • October 19, 2021
 • የጤና እክሎች

ለጡት ካንሰር የሚያጋልጡ፤ የሚሻሻሉም ሆነ የማይሻሻሉ ብዙ አጋላጭ ሁኔታዎች አሉ። ይህ ማለት ግን እነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች ያለበት ሰው ሁሉ የጡት ካንሰር ተጠቂ ይሆናል ማለት አይደለም። ይልቁንም እነዚህን አጋላጭ ሁኔታዎች ቀድመን ማወቅ በዋነኝነት የሚጠቅመን፤ ሊሻሻሉ የሚችሉትን አጋላጭ ሁኔታዎች ለመከላከል እና መቼ የቅድመ ምርመራ ማድረግ እንዳለብን ለማወቅ ነው። የጤና ባለሙያዎችም ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ለይቶ ቅድመ ምርመራ ወይም ሌሎች የመከላከያ እርምጃዎችን ለመጠቆም ይጠቀሙበታል። 

ሌላው ማወቅ ያለብን ነገር እነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች ሳይኖራቸው በበሽታው የሚጠቁ ሰዎች እንዳሉ ነው፡፡ ስለዚህም ለጡት ካንሰር ዝቅተኛ ተጋላጭነት ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ እንኳን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እና ቅድመ ምርመራን መተግበር ይኖርባቸዋል፡፡

ለዚህም እንዲያመች በሚል እነዚህ አጋላጭ ሁኔታዎች መሻሻል የሚችሉ እና የማይችሉ ተብለው በ ሁለት ይከፈላሉ።

መሻሻል የማይችሉ አጋላጭ ሁኔታዎች የሚባሉት 

 • ዕድሜ - ለአብዛኛዎቹ ሴቶች ዋነኛው አጋላጭ ሁኔታ ዕድሜ ነው፡፡  ከ 45 እስከ 50 ዓመት ድረስ የጡት ካንሰር በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፡፡ በአንፃሩ ከ 80 ዓመት በኋላ የመከሠቱ ሁኔታ ማሽቆልቆል ይጀምራል።
 • ፆታ - የጡት ካንሰር ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ የመከሠት ዕድሉ በ 100 እጥፍ ይበልጣል፡፡
 • ዘር / ቀለም - በአሜሪካ ውስጥ ያሉ ነጭ ሴቶች በከፍተኛ ደረጃ የጡት ካንሰር ተጠቂ ናቸው። በአንፃሩ በ ጥቁር አሜሪካውያንና ሕንዶች ላይ የጡት ካንሰር መጠን ዝቅተኛ ነው፡፡ 
 • ክብደት - የክብደት መጨመር እና ከመጠን በላይ ውፍረት ብዙውን ጊዜ ከወር አበባ ማረጥ በኋላ የሚመጣውን የጡት ካንሰር ይጨምረዋል፡፡ 
 • ከዚህ በፊት የጡት ካንሰር ይዞዎት ከነበረ ድጋሚ የመያዝ ዕድልዎ ከፍተኛ ነው።
 • በቤተሰብ ውስጥ (እናት ወይም ሴት ልጅ) የጡት ካንሰር ተጠቂ ከሆኑ / ከነበሩ - በጡት ካንሰር ከተያዙ ሴቶች ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር የተጠቃ እናት ወይም እኅት አላቸው። ለዚህም ዋና ምክንያቱ BRCA1 እና BRCA2 በመባል የሚታወቀው በዘር የሚተላለፍ የዘረመል ለውጥ ነው፡፡ BRCA1 ወይም BRCA2 የዘረመል ለውጥ ያላቸው ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከ 50 እስከ 85 በመቶ ይደርሳል።

መሻሻል የሚችሉ አጋላጭ ሁኔታዎች የሚባሉት 

 • የወር አበባ ማየት ቀድመው የጀመሩ እና ቆይተው ያረጡ ሴቶች የጡት ካንሰር ተጋላጭነታቸው ይጨምራል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ኤስትሮጅን ለሚባል ሆርሞን ለረጅም ዕድሜ ስለሚጋለጡ ነው። 
 • ያልወለዱ ሴቶች - እርግዝና እና ጡት ማጥባት የጡት ካንሰርን ይቀንሳል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ ልጅ መውለድ እና የመጀመሪያ ልጅ የወለድንበት ዕድሜ ማነስም እንዲሁ በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድልን ይቀንሳል። 
 • ከማረጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ምልክቶችን ለመቀነስ ተብለው የሚሰጡ የሆርሞን መድኃኒቶች በጡት ካንሰር የመያዝን ዕድል ይጨምራሉ። 
 • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ 
 • ትምባሆ ማጨስ 
 • አልኮል አብዝቶ መጠቀም
 • የአመጋገብ ዘይቤ - አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አትክልት መመገብ በጡት ካንሰር የመጋለጥ ዕድልን የሚቀንስ ሲሆን፤ በአንፃሩ ሥጋ እና ስብ (ጮማ፣ ቅባት) አብዝቶ መጠቀም ደግሞ ይጨምራል።
 • ለአዮናይዚንግ ጨረር መጋለጥ - በተለያየ ምክንያት በተለይ በሕፃንነት ዕድሜያቸው ለአዮናይዚንግ ጨረር የተጋለጡ ሰዎች በጡት ካንሰር የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ለምሳሌ ለሌላ የካንሰር ሕክምና ወይም ደግሞ ከአቶሚክ ቦንብ ፍንዳታ የተረፉ ሰዎች በማንኛውም ካንሰር የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው።

የጡት ካንሰርን እንዴት መከላከል ይቻላል?

ቅድመ ምርመራ ማድረግ - ይህም በጡት ካንሰር የመያዝ አደጋን ባይቀንስ እንኳን በሽታው ቶሎ ታውቆ ተገቢውን ሕክምና ለመስጠት ስለሚያስችል በጡት ካንሰር የመሞትን አደጋ በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ 

የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች - በርካታ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ለጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ሊቀንሱ ይችላሉ።

 • 30 ዓመት በፊት የመጀመሪያ ልጅ መውለድ
 • ቢያንስ ለስድስት ወር ጡት ማጥባት
 • ከወር አበባ ማረጥ በኋላ የሆርሞን ሕክምናን አለመጠቀም፤ ወይም ለተወሰነ ጊዜ ብቻ መጠቀም 
 • ከአላስፈላጊ ጨረር ራስን መጠበቅ፤ ለምሳሌ የማያስፈልግ የ ሲቲ ስካን ምርመራ ከማድረግ መቆጠብ፡፡
 • ሲጋራ አለማጨስ
 • የአልኮል መጠጥን መገደብ
 • ጤናማ ክብደት መኖር
 • ንቁ የአኗኗር ዘይቤን መከተል፡፡ ይህም የአካል እንቅስቃሴ መሥራትን ያጠቃልላል።

ስለ ጡት ካንሰር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ

Share the post

scroll top