Get detailed information about your health.  Learn

የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ

  • October 19, 2021
  • የጤና እክሎች

የጡት ካንሰር ሕመም ቀደም ብሎ ከታወቀ በሕክምና የመፈወስ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ የቅድመ ምርመራ ዓላማ የጡት ካንሰር በመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንዳለ ሳይስፋፋ ለማወቅና አስፈላጊውን የሕክምና መፍትሔ ለማወቅ ነው። 

በአሜሪካ ውስጥ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ፤ የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ለአለፉት ጥቂት ዓሥርት ዓመታት በጡት ካንሰር የመሞት ዕድልን በአንድ ሦስተኛ ያህል ቀንሷል፡፡ 

ለጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ የተለያዩ የሕክምና ዘዴዎች አሉ። እነዚህም፡-

1. ማሞግራፊ (Mammography)

ማሞግራፊ ማለት በሌላ አገላለፅ የጡት ራጅ ማለት ነው፡፡ ይህ ምርመራ በጡት ካንሰር የመሞትን አደጋ ለመቀነስ የተሻለ የቅድመ ምርመራ ዓይነት ነው፡፡ ምርመራው ሁለቱንም ጡቶች የሚያካትት ሲሆን፤ የሚወስደውም ለጥቂት ሴኮንዶች ብቻ ነው። 

ምርመራው የወር አበባ በመጣበት ሰሞን ባይደረግ ይመከራል። ይህም በምርመራው ምክንያት የሚያጋጥም የጡት ሕመምን ለመቀነስ ነው። በተጨማሪም በምርመራው ወቅት የብብት ዲኦድራንቶች ወይም ክሬሞችን ባያደርጉ ይመረጣል።

የራጁ ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርስ ሲሆን፤ ስለውጤቱ ከጤና ባለሙያ ጋር በመነጋገር ስለጡቶቹ የጤና ሁኔታ መረጃ ማግኘት እጅግ ጠቃሚ ነው።

አንዳንድ ጊዜ የራጁ ውጤት ጡት ላይ ችግር እንዳለ ሊያሳይ ይችላል። ነገር ግን ይህ ምርመራ በወጣቶች ላይ ብዙም ተግባራዊ አይሆንም። በአሜሪካ ውስጥ በተደረገ ጥናት 90 በመቶ የሚሆኑት ችግር የሚያሳዩ የራጅ ውጤቶች የጡት ካንሰር የላቸውም። ነገር ግን እንደሁኔታው ተጨማሪ ምርመራ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡

ቅድመ ምርመራው በየትኛው ዕድሜ መጀመር አለበት?

በአጠቃላይ ዕድሜአቸው 50 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሴቶች ቢያንስ በሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ይህን ምርመራ ቢያደርጉ ይመከራል።

ዕድሜአቸው ከ 40 - 49 ዓመት የሆኑ ሴቶች የሚከተሉትን ነጥቦች በማመዛዘን ቅድመ ምርመራውን እንዲጀምሩ ይደረጋል።  

  • ሴቷ ቅድመ ምርመራ መጀመር የምትፈልግ ከሆነ
  • ስለቅድመ ምርመራው ጥቅምና ጉዳት በቂ ግንዛቤ አላት ወይ?

ስለሆነም ስለምርመራው ከጤና ባለሙያ ጋር ተገቢ ምክክር ከተደረገ በኋላ መቼ ምርመራ መጀመር እንዳለበት ውሳኔ ቢደረስ ጠቃሚ ይሆናል።

ልብ ይበሉ፤ ለጡት ካንሰር የሚያጋልጥ የዘረመል ችግር (BRCA1,BRCA2) ያለባቸው ሴቶች ወይም ተመሳሳይ የቤተሰብ ሕመም ያላቸው፣ ከ 30 ዓመታቸው በፊት የደረት ጨረር ሕክምና የወሰዱ፤ ከላይ ከተጠቀሰው ዕድሜ ቀደም ብለው የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ መጀመር ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ወጣቶች ከፍተኛ የጡት መጠን ስለአላቸው ኤም አር አይ እና አልትራሳውንድ መጠቀም የተሻለ ይሆናል።

2. በጤና ባለሙያ የሚደረግ የጡት ምርመራ

ይህ በጤና ባለሙያ ማለትም በሐኪም ወይም በነርስ ጡትን በመዳሰስ የሚደረግ የጡት ካንሰር ቅድመ ምርመራ ዓይነት ነው። 

በመደበኛነት የጤና ባለሙያዎች እንደዚህ ዓይነት የጡት ምርመራ እንዲያደርጉ አይመከርም። ነገር ግን በጡት ራጅ ወቅት ከሆነ ምርመራው የተደረገው ስለጡት ጤና የሚሰጡት መረጃ እጅግ ጠቃሚ ይሆናል።

3. የራስን ጡት መመርመር (Self - breast examination)

ይህ የራስን ጡት በመዳሰስ እና በመፈተሽ ጡት ላይ ከወትሮ ለየት ያለ ለውጥ ከመጣ ለማወቅ ይረዳል። ራስን መፈተሽ በራስ ጡቶች ላይ ለውጦችን የማግኘት መንገድ ነው ፡፡ 

ጡታችንን እንዴት አድርገን እየዳበስን እንመርምር?

የወር አበባ የምታይ ሴት ከሆነች የወር አበባዋ ከተጠናቀቀ በሳምንቱ ምርመራውን ብታደርግ ይመረጣል። 

  • ሁለቱንም እጆች ከጎን በማድረግ ቀጥ ብለው መስታወት ፊት ለፊት በመቆም ምርመራውን መጀመር ይመረጣል፡፡ ከዚያም የጡትን ቆዳ ቀለም መቀየር ወይም ቆዳ ላይ የተለየ ለውጥ መኖሩን ለማስተዋል መሞከር፡፡ በመቀጠልም የጡት ጫፎች ወደ ውስጥ መግባታቸውን ወይም ወደላይ  መሳባቸውን ለማየት መሞከር፡፡ 

  • ቀጥሎም በጀርባ በመተኛት የግራ እጅን ከጭንቅላት በላይ ማኖር። በቀኝ እጅ የመሐል ሦስት ጣቶች  የግራ ጡትን ከብብት ጀምሮ ከላይ ወደታች ክብ በሆነ አኳኋን መዳሰስ። ይህም የእጃችንን ኃይል እየቀያየርን ጡታችንን ሦስት ጊዜ በደንብ መዳሰስ ያስፈልጋል።  ከዚያም የጡት ጫፍን በመደሳስ ለውጥ መኖሩን ወይም የሚወጣ ፈሳሽ ካለ ማየት ይኖርብናል። በመጨረሻም እጅን በመቀየር  በሌላኛው ጡት ላይ ተመሳሳይ  ምርመራን ማድረግ።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የራስን ጡት በመመርመር ብቻ በጡት ካንሰር የመሞት ዕድልን መቀነስ አይቻልም፡፡ ስለሆነም የራስ ጡት ምርመራ ከሌሎች እንደ ጡት ራጅ ካሉ ቅድመ ምርመራዎች ጋር አብሮ  መጣመር ይኖርበታል።

ስለ ጡት ካንሰር ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ

Share the post

scroll top