Learning materials for your health  Learn

ስለምጥ ማወቅ ያለብን ነገር ምንድን ነው?

 • October 29, 2021
 • የጤና እክሎች

ምጥ ነፍሰ ጡር የሆኑ ሴቶች አካል ለመውለድ የሚዘጋጅበት ተፈጥሮአዊ መንገድ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ምጥ ከ 37 እስከ 42 ሳምንቶች ባለው የእርግዝና ወቅት ይጀምራል፡፡ 

በምጥ ጊዜ የሚከሠቱ የሰውነት ለውጦች ምን ምንድን ናቸው?

በምጥ ወቅት ከሚከሠቱ ነገሮች መካከል ዋነኛው እየጨመረ የሚሄድ የማሕፀን መኮማተር ነው። የዚህም ዋና ዓላማው የማሕፀን በር እንዲከፈት ማድረግ ነው። የማሕፀን መኮማተር መጠኑ እና ድግግሞሹ እየጨመረ ሲሄድ እንዲሁም የማሕፀን በር እየሳሳና እየተከፈተ ሲሄድ ወፍራም ደም የተቀላቀለበት ወፍራም ዝልግልግ ፈሳሽ (mucus) ከማሕፀን ይወጣል። የሕክምና ባለሙያዎች “ብለድ ሾው /bloody show” ይሉታል። 

ይህም በእርግዝና ጊዜ ቆሻሻ ወደ ማሕፀን እንዳይገባ ለመከላከል የማሕፀንን በር የሚሸፍን ወፍራም ፈሳሽ (mucus) ነው። 

ምጥ ሲጀምር እንዴት ማወቅ ይቻላል? 

ምጥ ጀመረ የሚባለው የሚከተሉት ምልክቶች ሲታዩ ነው። 

 • የጀርባ / የወገብ ሕመም ወይም የሆድ ቁርጠት ከአለ - እርግዝናው ከ 37 ሳምንታት በላይ ከሆነና ቁርጠት ጀምሮ ወደ ሆስፒታል ከሄዱ፣ ሐኪሙ ምጡ እውነተኛ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ምርመራ ያደርጋል። በዋነኛነት የማሕፀን በር ምን ያህል እንደከፈተ፣ የቁርጠቱ መጠንና ቁጥር መጨመሩን ያያል። እውነተኛ ምጥ መሆኑ የሚታወቀው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ከሆነና የማሕፀንን በርን መክፈት ከቻለ ነው። 

 • ወፍራም፣ ደም የተቀላቀለበት ፈሳሽ (mucus) ከታየ

 • የእንሽርት ውሃ መፍሰስ - በእርግዝና ወቅት ልጁ የሚገኘው እንሽርት ውሃን በያዘ ከረጢት ውስጥ ነው፡፡ ይህ ከረጢት በሚፈነዳበት ጊዜ በከረጢቱ ውስጥ ያለው ፈሳሽ ይፈስሳል፡፡ ይህም ቷ ብሎ ሊፈነዳ ወይም ቀስ እያለ ሊፈስስ ይችላል፡፡ በሁለቱም መንገድ ቢሆን ይሄ የሚያመለክተው ነፍሰ ጡሯን ሴት ምጥ እንደጀመራት ነው።

በአማካኝ ምጥ ስንት ሰዓት ይቆያል?

ምንም እንኳን ምጥ ቀጣይነት ያለው ሂደት ቢሆንም፤ ለክትትል እንዲያመች በሦስት ደረጃዎች ይከፋፈላል፡፡

 1. የመጀመሪያ ደረጃ (First stage)  

የመጀመሪያ ደረጃ የሚባለው ምጡ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የማሕፀን በር ሙሉ በሙሉ እስኪከፈት ያለው ጊዜ ነው። 

የማሕፀን በር ሙሉ በሙሉ ተከፈተ የሚባለው ደግሞ 10 ሴ.ሜ ሲሆን ነው። 

ከዚህ በተጨማሪ በዚህ የምጥ ደረጃ ላይ የቁርጠቱ መጠን እየጨመረ፣ እየረዘመ እና እየተቀራረበ ይሄዳል።

ይህ ደረጃ ለ 2 ክፍሎች ይከፈላል። የመጀመሪያው ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚወልዱ እናቶች እስከ 20 ሰዓታት፤ ከዚህ በፊት ለወለዱ ደግሞ እስከ 14 ሰዓታት ሊቆይ ይችላል። በዚህ ደረጃ የማሕፀን በር ከ 4 እስከ 5 ሴ.ሜ. ይከፈታል። 

ቀጥሎ ባለው ክፍል ደግሞ የማሕፀን በር ሙሉ በሙሉ ይከፍታል። 

2. ሁለተኛ ደረጃ (Second stage) 

ሁለተኛው የምጥ ደረጃ የሚባለው የማሕፀን በር ሙሉ በሙሉ ከተከፈተ በኋላ ልጁ እስኪወለድ ያለው ጊዜ ነው። 

ሁለተኛው ደረጃ መጀመሩን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። ለምሳሌ፦ 

 • የማቅለሽለሽ እና የማስመለስ ስሜት 

 • ከቁርጠቱ ባሻገር ወደ ታች የመግፋት ስሜት መጨመር፤ እንዲሁም 

 • የፅንሱ ጭንቅላት ፊንጢጣ ላይ ግፊት ስለሚያስከትል ሰገራ የመምጣት ስሜት ሊፈጠር ይችላል።  

ይህ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚወልዱ እናቶች እስከ 2 ሰዓት፤ ከዚህ በፊት ለወለዱ ደግሞ እስከ አንድ ሰዓት ሊቆይ ይችላል። ነፍሰ ጡሯ ማደንዘዣ ከተሰጣት ደግሞ ምጡ የሚወስደው ሰዓት በእጥፍ ሊጨምር ይችላል።

3. ሦስተኛው ደረጃ (Third stage) 

ሦስተኛው የምጥ ደረጃ ሕፃኑን ከተወለደ በኋላ የእንግዴ ልጁ እስከሚወጣ ያለው ጊዜ ነው። ይህም ከ 30 ደቂቃዎች በላይ መቆየት የለበትም። 

ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያለው ዋነኛው ችግር ከወሊድ በኋላ ያለ የደም መፍሰስ ሲሆን ይህም ለእናቶች ሞት ዋና ምክንያት ነው፡፡ 

ስለዚህም የደም መፍሰሱን ለመቀነስ የእንግዴ ልጁ እስኪወጣ እና ከወጣ በኋላ የሕክምና ባለሙያዎች የተለያዩ የሕክምና እርዳታዎችን ያደርጋሉ። 

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ምጥ በአማካኝ እስከ 26 ሰዓታት ሊወስድ ይችላል። በዚህ የምጥ ደረጃ ላይ የቁርጠቱ መጠን እየጨመረ፣ እየረዘመ እና እየተቀራረበ ይሄዳል።

ምጥ የሚረዝመው በምን ምክንያት ነው? ሕክምናውስ?

አንዲት እናት ልጅ ለመውለድ የሚፈጅባት የምጥ ጊዜ በተለያዩ ነገሮች ሊወሰን ይችላል። እነዚህም በዋነኝነት በሦስት ይከፈላሉ።

 1. የማሕፀን መኮማተር፣ (የቁርጠቱ) ጥንካሬ እንዲሁም በ 10 ደቂቃ ውስጥ ቁርጠቱ ምን ያህል ተመላልሷል የሚለው አንዱ ወሳኝ ነገር ነው።  በቂ የማሕፀን መኮማተር (uterine contraction) የሚባለው በ 10 ደቂቃ ውስጥ ከ 3 - 5 ጊዜ ቁርጠት ካለ ነው። አንዱ ቁርጠት ከ 40 - 60 ሰኮንድ መቆየት አለበት። ይሄ ከአልሆነ ግን ምጡ ሊረዝም ይችላል። ለዚህም የሚሰጠው መድኃኒት የምጥ መርፌ ይባላል።

 2. የልጁ ውፍረት እና አቀማመጥም ሌላው ውሳኝ ነገር ነው። ፅንሱ ትንሽ ከሆነ እና አቀማመጡ በጭንቅላቱ ከሆነ የምጥ ሂደቱ ቀላል ይሆናል።

 3. ሌላው የምጡን ፍጥነት የሚወስነው ነገር የእናትዬዋ የዳሌ አጥንት ስፋት ነው። የሕክምና ክትትል የሚያደርገው ሐኪም የእናትዬዋ የዳሌ አጥንት በቂ መሆን አለመሆኑን የሚገመግምበት የተለያዩ መንገዶች አሉ። እነዚህን መንገዶች ተከትሎ የዳሌ አጥንቱ በቂ ከሆነ ምጥ መሞከር ይቻላል።

ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ነገሮች ውስጥ አንዱ ላይ ችግር ከአለ ምጡ ይረዝማል። 

የምጥ ሕመምን ለማስታገስ የሚረዱ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

ተፈጥሮአዊ የሆኑ እንዲሁም በመድኃኒት መልክ የሚሰጡ የምጥ ሕመምን ለማስታገስ የሚረዱ ብዙ መንገዶች አሉ።

የ ምጥ ሕመምን ለማስታገስ የሚረዱ መድኃኒቶች 

በኢኮኖሚ በአደጉት ሀገራት ለምጥ ሕመም ማስታገሻ መድኃኒት ይሰጣል። በአዲስ አበባ አንዳንድ የግል ሐኪም ቤቶች ውስጥም አገልግሎቱ ይሰጣል። መድኃኒቶቹ በብዛት የሚሰጡት በሁለተኛው የምጥ ደረጃ ላይ ሲሆን፤ በዋነኛነት የሚሰጡት መድኃኒቶችም የሚከትሉት ናቸው ፡፡

 • ናርኮቲክ መድኃኒቶች - ናርኮቲክ መድኃኒቶች በምጥ ወቅት ለሕመም ማስታገሻነት ይሰጣሉ። ነገር ግን መድኃኒቶቹ ምጥን የማርዘም እና የልጁን የልብ ምት የመቀነስ አዝማሚያ ሊኖራቸው ይችላል። በጣም ከተለመዱት ናርኮቲክ መድኃኒቶች ውስጥ ሞርፊን አንዱ ነው።

 • ኤፒዱራል (Epidural) - ይህ መንገድ በምጥ እና በወሊድ ወቅት በጣም የተለመደ የሕመም ማስታገሻ ዘዴ ነው፡፡ የማደንዘዣ መድኃኒቱ የሚወጋው የታችኛው ጀርባ ላይ ባለው ኢፒዱራል ስፔስ (Epidural space) ውስጥ ነው፡፡ መድኃኒቱ የሚሠራው ደግሞ በዚያ በኩል የሚያልፉ ነርቮችን በማገድ ነው።

በተፈጥሮአዊ መንገድ ሕመምን ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት?

ተፈጥሮአዊ የሆነ የሕመም ማስታገሻ ለሚፈልጉ ሴቶች ብዙ አማራጮች አሉ፡፡ እነዚህ መንገዶች ያለ መድኃኒት ሕመምን በመቀነስ ላይ ያተኩራሉ፡፡

ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ የሚከተሉትን ያካትታሉ፡፡

 • የውሃ ሕክምና (hydrotherapy)

 • ሀይፕኖሲስ (hypnosis)

 • አኩፓንቸር (acupuncture)

 • መታሸት (massage)

ከዚህ በተጨማሪም የአተነፋፈስ ዘዴዎችን መጠቅም፣ ከሚያምኑት እና ከሚወዱት ሰው ወይም የቤተሰብ አካል የቅርብ ድጋፍ ማግኘት፣ እንዲሁም እንደ ሙዚቃ ያሉ ነገሮችን በመጠቀም ትኩረትን ከሕመሙ ላይ ለማስወገድ የሚረዱ ነገሮች መጠቀም ይቻላል ፡፡

Share the post

scroll top