Learning materials for your health  Learn

ክትባት ምንድነው?

 • November 3, 2021
 • የጤና እክሎች

ክትባት በሽታ አምጪ የሚባሉ ተሕዋስያንን በማዳከም ወይም በመግደል አለያም መርዙን በመውሰድና ፕሮቲኑን በማዳቀል የሚሠራ ነው። የክትባት ዋና ሥራው በሽታ ከመከሠቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል ነው።

የክትባት ዓይነቶች

1. ንቁ ክትባት (Active immunization)

ይህ ክትባት ሰውነታችን የራሱን የሆነ የበሽታ መከላከል ዐቅም ሥርዓት እንዲገነባ የሚያደርግ ነው። 

2. ንቁ ያልሆነ ክትባት (Passive immunization)

ይህ ደግሞ ቀድሞውኑ የተመረተውን በሽታ መከላከል ወይም አንቲቦዲ በመስጠት ሰውነታችን  ለጊዜው ከበሽታው እንዲጠበቅ ያደርጋል።

ልጅዎትን ለምን ያስከትባሉ?

ክትባት በተለይም ለሕፃናት ምን ጠቀሜታ አለው?

ሕፃናት እንደተወለዱ ለአካባቢያቸው አዲስ ስለሚሆኑ ለብዙ በሽታ አምጪ ተሕዋስያን የተጋለጡ ናቸው።

በሽታ እንዳይበረታባቸውም የሰውነታቸውን የመከላከል ዐቅም ማሳደግ ይገባል፡፡ ስለዚህ  ክትባት ለልጆች በጣም አስፈላጊ ይሆናል።

የሕፃናት ክትባት አሰጣጥ ፕሮግራም በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ የራሱ የሆነ የተዘጋጀ መመሪያ አለው። 

 • በዚህም መሠረት በጤና ተቋማት ውስጥ የሚከተሉት የክትባት ዓይነቶች ለልጆች ይሰጣሉ።

  • ሕፃናት እንደተወለዱ ቢሲጂ (BCG)

  • በ 6 ሳምንት (45 ቀን)   ፖሊዮ፣ ፔንታቫለንት፣ ፒሲቪ እና ሮታ ( OPV,PCV,Penta,Rota)

  • በ 10 ሳምንት ፡ በ6 ሳምንት ከሚሰጠው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

  • በ14 ሳምንት ከ 6 ፡ ሳምንት ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ነገር ግን ሮታ አይሰጥም፡፡

  • በ 9 ወሩ ፡ የኩፍኝ ክትባት፣ ቪታሚን ኤ

  • ቪታሚን ኤ በየ 6 ወሩ እስከ አምስት ዓመታቸው ድረስ ክትባቱን ቢወስዱ ይመረጣል።

በተለያዩ ጊዜያት ወረርሽኞች ሲከሠቱ ለምሳሌ እንደ ማጅራት ገትር፣ ፖሊዮ፣ ኩፍኝ እና ትክትክ፤ በዓለምና በሀገር አቀፍ ደረጃ  እነዚህን በሽታዎች ለመቆጣጠር ከላይ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በጅምላ ለሕፃናት ክትባት ይሰጣል።

ክትባቱ የትኛዎቹን በሽታዎች  ይከላከላል?

 • በቲቢ  የሚመጣ ማጅራት ገትር፣ ሳንባ ነቀርሳ፣ የተሰራጨ ቲቢ

 • ፖሊዮ (poliomyelitis)

 • ዘጌ አናዳ (ዲፍቴሪያ ወይም ከባድ የጉሮሮ ኢንፌክሽን)

 • ትክትክ  እና ከባድ ሳል

 • መንጋጋ ቆልፍ (tetanus)

 • ሄፓታይተስ ቢ (የጉበት ቫይረስ ኢንፌክሽን)

 • ኢንፍሎዌንዛ

 • ሳንባ ምች (Pneumonia)

 • ማጅራት ገትር (meningitis)

 • ኩፍኝ (measles)

 • ተቅማጥ በሽታ

ቫይታሚን ኤ ለምን ይጠቅማል?

 • ለሕፃናት በሽታ የመከላከል ዐቅማቸውን ይጨምራል፡፡

 • ለጥርስ፣ ለአጥንትና ለቆዳ ዕድገት ይጠቅማል፡፡

 •  ለዐይን ጥራትና ጤንነት አስፈላጊ ነው፡፡

የክትባት ጎንዮሽ ጉዳት?

 • በአጠቃላይ ክትባቶቹ ጤና ላይ የሚያመጡት ከባድ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ የለም።

 • በሀገራችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት በየዓመቱ ክትባቱን ያለምንም ጎንዮሽ ጉዳት ይወስዳሉ፡፡ 

በጣም የተለመዱት የጎንዮሽ ጉዳቶች ቀላል የሚባሉ ናቸው።

 • ክትባት በወሰደበት ቦታ ላይ የሕመም ስሜት ወይም እብጠት፤

 •  እንደ ንፍፊት መውጣት፤

 •  ቀለል ያለ ትኩሳት፣ መነጫነጭ ናቸው፡፡

እነዚህም ችግሮች በጥቂት ቀናት ውስጥ ይጠፋሉ።

ለጎንዮሽ ጉዳቱ ምን ማድረግ ይገባል?

 • የልጁን ምግብ መቀጠል፣ ጡትም ከሆነ ማጥባት፤

 • ሕመሙን  ለማስታገስ ክትባቱን በወሰደበት አካባቢ ላይ ቀዝቀዝ ወይም ረጠብ ያለ ጨርቅ ማድረግ፡፡ 

 • አለመረበሽ

የጎንዮሽ ጉዳቱ እየባሰ ከመጣስ?

 • ክትባት የተሰጠበት አካባቢ ተለቅ ያለ መግል መቋጠር ከጀመረ 

 • ትኩሳቱ እየጨመረ ከመጣ

 • ከወትሮ የተለየ ነገር ሕፃኑ ላይ ከተስተዋለ ፈጥኖ ወደ ጤና ጣቢያ መውሰድ ይገባል። 

ክትባት የማይሰጥባቸው ሁኔታዎች ምንድናቸው?

 •  ከዚህ በፊት በነበረው ክትባት ላይ ከፍተኛ የአለርጂ ችግር ከአጋጠመ

 •  በሽታ የመከላከል ዐቅምን የሚያዳክም በሽታ ከአለበት 

ልብ ይበሉ :- በሽታ የመከላከል ዐቅምን የሚያዳክም በሽታ ያለባቸው ሕፃናት መከተብ የሌለባቸው ተሕዋሲያን ለማዳከም (live attenuated vaccines) የተሠራ ክትባት ብቻ ነው፡፡  

 • ከዚህ ቀደም ክትባት መውሰድ ለአልጀመረ፣ የታቀደለትን የክትባት መጠን  ወይም ክትባት ተከታትሎ ለአላጠናቀቀ ሕፃን ልጅስ ምን መደረግ አለበት? (catch up vaccination)

 • እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በሚገጥምበት ሰዓት ሕፃኑን ወደ ጤና ጣቢያ በመውሰድ ዕድሜውን መሠረት ያደረገ ሕክምና፤ የሚቻል ከሆነና ጥቅሙ ከፍ ያለ  ከሆነ  ክትባቱን እንዲጀምር፣ እንዲቀጥል እና እንዲጨርስ ይደረጋል።

ክትባትና ኦቲዝም የሚያገናኛቸው ነገር አለን?

 • እየተደረጉ ባሉ ሳይንሳዊ ጥናቶች እና ምርምሮች መሠረት በክትባትና እና በኦቲዝም መካከል ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከሦስት ዓመት  በፊት የተጨመሩ አዳዲስ የክትባት ዓይነቶች እነማን ናቸው?      

 • ሁለት አዳዲስ ክትባቶች በመደበኛ የክትባት ፕሮግራም ውስጥ ተካተዋል።

 1. ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ (H.P.V) 
 2. ዙር ሁለት የኩፍኝ ክትባት 
 • መርሐ ግብሩም በየዓመቱ ከ 3 ሚሊዮን በላይ ልጆችን የመከተብ ዕቅድ አካቷል።

 1. የኤች.ፒ.ቪ (H.P.V)

 • ሁሉም የኤች.ፒ.ቪ ክትባቶች የማሕፀን በር ካንሰርን ከሚያመጡ ኤች.ፒ.ቪ 16 እና 18 ቫይረስ ኢንፌክሽንን ይከላከላሉ።

 • በአጠቃላይ  የኤች.ፒ.ቪ (H.P.V) ክትባቶች የሚከተሉትን በሽታዎች ይከላከላሉ።

          - የማሕፀን በር ካንሰር 70% 

          - የፊንጢጣ ካንሰር   80%  

         - የሴት ብልት ካንሰር 60% እና

         - የአፍና የጉሮሮ ካንሰር 90%  በመከላከል ውጤታማ ናቸው።

አሰጣጡስ እንዴት ነው?

 • በሀገራችን ከ 9 - 14 ዓመት የሆናቸው ሴት ተማሪዎች የኤች.ፒ.ቪ ክትባት በትምህርት ቤቶች እንዲሁም በጤና ተቋማት ውስጥ ክትባቱን ማግኘት ችለዋል። 

 • ክትባቱ በሁለት ዙር የሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛው ዙር  የመጀመሪያው ክትባት ከተሰጠ ከ 6 - 12 ወራት በኋላ ይሰጣል።     

2. የኩፍኝ ክትባት ዙር ሁለት

 • ከላይ እንደተገለፀው ሕፃናት በ 9 ወራቸው ዙር አንድ የኩፍኝ ክትባት ይወስዳሉ።

 • ከ 3 ዓመት ወዲህ ዙር ሁለት የኩፍኝ ክትባት ተጀምሯል። ሁለተኛው የኩፍኝ ክትባት ከመጀመሪያው ክትባት ቢያንስ በ 4 ሳምንት መራራቅ አለበት።

 • በአገራችን ክትባት ፕሮግራም መሠረት ሁለተኛው ዙር የኩፍኝ ክትባት ሕፃናት 15 ወራቸው ሲሆን እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡

Share the post

scroll top