Learning materials for your health  Learn

የትንሹ አንጀት መታጠፍ/ መዘጋት

 • November 8, 2021
 • የጤና እክሎች

የትንሹ አንጀት እግደት ወይም መዘጋት ማለት አየር፣ ፈሳሽ እና ምግብ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በትንሹ አንጀት ውስጥ ማለፍ አልቻሉም ማለት ነው። በዚህ ምክንያት አንጀት ከያዘው አየር፣ ፈሳሽ እና ምግብ የተነሣ ሊያብጥ ይችላል፡፡ ይህ እብጠት የአንጀትን ምግብ እና ፈሳሽ የመምጠጥ ዐቅምን በማሳነስ የሰውነት ፈሳሽ ማነስ (Dehydration) እና የኩላሊት ሥራ መዳከም ሊያስከትል ይችላል።   

የአንጀት እግደት በሚኖርበት ጊዜ ወደ አንጀት ኦክስጅንን እና የበለፀገ ምግብ የሚያመጡ ደም ሥሮች ሊስተጓጎሉ ይችላሉ፡፡ ይህም የአንጀት ክፍሎች እንዲጎዱ (Strangulate) እና እንዲሞቱ (Gangrenous) ሊያደርግ ይችላል፡፡

የአንጀት ግድግዳ መጎዳት ወይም መሞት ምንን ያስከትላል?

የአንጀት ግድግዳ ከተጎዳ ወይም ምውት ከሆነ በውስጡ ያለው ፈሳሽ እና በሽታ አምጪ ተሕዋስያን ሊወጡ እና የሆድ ዕቃን ሊበክሉ ይችላሉ። ይህም የሆድ ሽፋን ብግነት እና ኢንፌክሽንን ያስከትላል (Peritonitis)፡፡

ሁለት የአንጀት እግደት አይነቶች አሉ።

 1. የአንጀት በድንነት (Paralytic ileus)

ይህ የሚፈጠረው የትንሹን አንጀት እንቅስቃሴ ወይም መኮማተርን የሚቀንሱ ማንኛውም ሁኔታዎች ሲከሠቱ ነው።

ለምሳሌ

 • የሆድ ዕቃ ቀዶ ጥገና

 • የንጥረ ነገር መዛባት (Electrolyte imbalance)

 • አንዳንድ የሕመም ማስታገሻዎች (Narcotics)

 • የሆድ ዕቃ ኢንፌክሽን ወይም መግል መቋጠር

 • የሰውነት ፈሳሽ ማነስ (Dehydration)

2. መካኒካዊ የአንጀት እግደት (Mechanical SBO)

 የሚከተሉት የአንጀት ወይም የአንጀት አካባቢ ሕመሞች መካኒካዊ የአንጀት እግደትን ያመጣሉ።

   እነዚህም፡-

 • የአንጀት መጠምዘዝ (Volvulus) - ይህ በአገራችን ቀዶ ጥገና ባላደረጉ ሰዎች የሚከሠት ዋነኛው የትንሹ አንጀት እግደት መንሥኤ ነው። 

 • አንዱ የአንጀት ክፍል በሌላው የአንጀት ክፍል ውስጥ ሲታጠፍ (Intussusception)

 • የሆድ እቃ ቀዶ ጥገና ከተደረገ በኋላ ሆድ ውስጥ ጠባሳ ተፈጥሮ ከነበረ (Adhesion)። ይህ ጠባሳ ትንሹ አንጀትን በመጫን እግደትን ሊያመጣ ይችላል፡፡

 • ቡአ (Hernia) -  የሆድ ዕቃን በሚሸፍኑት የሆድ ጡንቻዎች ወይም አካላት ላይ ክፍተት ሲፈጠር እና በዚህ ክፍተት ውስጥ የአንጀት ክፍል በመሽሎክ ሲወጣ ቡአ (Hernia) ይባላል። ቡአ (Hernia) የአንጀት እግደትን ሊፈጥር ይችላል።

 • አንዳንድ የአንጀት ብግነትን የሚያመጡ በሽታዎች (IBD,Diverticulitis) የአንጀት መጥበብን በማስከተል እግደት እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ።

 • የአንጀት ዕጢ ወይም ካንሰር እና ሌሎች አንጀት አካባቢ የሚነሡ ዕጢዎች ወይም ካንሰሮች የአንጀት መዘጋት ችግርን ሊያመጡ ይችላሉ።

የአንጀት መታጠፍ/ መታገድ ምልክቶች  ምንድናቸው?

ምልክቶቹ  የትኛው የትንሹ አንጀት ክፍል ነው የተጠቃው? እና በከፊል ወይስ ሙሉ በሙሉ ነው የተዘጋው? በሚለው ላይ ይወሰናሉ። በጣም የተለመዱት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 • ማቅለሽለሽ  እና ማስታወክ

 • በመሐል ዕረፍት የሚሰጥ ሆድ ቁርጠት

 • የሆድ እብጠት ወይም መነፋት

 • ሰገራ እና ፈስ ማውጣት መቸገር  

 • እየቆየ ሲመጣ ደግሞ ትኩሳት እና የማያቋርጥ የሆድ ሕመም ናቸው።  

ምን ዓይነት ምርመራዎች አሉ?

በአጠቃላይ ከላይ እንደተጠቀሱት ዓይነት ምልክቶች በሚኖሩበት ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሔድ ያስፈልጋል።

የጤና ባለሙያ ምልክቶችን በመጠየቅ እና አካላዊ ምርመራዎችን በማድረግ ስለሕመሙ ለመረዳት ይሞክራል። በተጨማሪም የሚከተሉትን ምርመራዎች ሊያዝዝ ይችላል ።

 • የምስል ምርመራዎች 

   የሆድ ራጅ፣ ሲቲ ስካን፣ አልትራሳውንድ

 • በተጨማሪም የተለያዩ  የደም ምርመራዎች ሊደረጉ ይችላሉ።

የአንጀት መታጠፍ/ መታገድ ሕክምና

የጤና ባለሙያው የትንሹ አንጀት እግደት ሕመም እንዳለብዎት ከጠረጠረ ሆስፒታል ተኝተው እንዲታከሙ ያደርጋል።

በሆስፒታል ውስጥ ምን ይደረጋል?

 • የድንገተኛ ሕክምና እርዳታ ይደረጋል።

 • የሰውነትን ፈሳሽ ለመተካት በደም ሥር በኩል ፈሳሽ ይሰጣል።

 • በአፍ ምንም ዓይነት ምግብ እና ፈሳሽ መውሰድ አይቻልም።

 • በአፍንጫ እና በጉሮሮው በኩል ወደ ሆድ የሚደርስ ስስ ቱቦ (NGT) ይደረጋል።

ይህም በአንጀት ውስጥ የተጠራቀመውን ፈሳሽ እና አየር ለማስወጣት፣ ትውከትን እና የሆድ መነፋትን ለማስታገስ ይረዳል።

በተጨማሪም የሽንት መጠንን ለመከታተል የሽንት ቱቦ ሊገባ ይችላል።

ቀዶ ጥገና

ለአንጀት እግደት ቀዶ ጥገና ዋነኛ የሕክምና አማራጭ ነው። ነገር ግን ከፊል የአንጀት መዘጋት፣ ከቀዶ ሕክምና በኋላ የሚከሠት እግደት፣ የእግደቱ መንሥኤ ቲቢ ወይም ካንሰር ከሆነ እንዲሁም ሌሎች ለጤና አስጊ የሆኑ ምልክቶች ከሌሉ ከላይ በተዘረዘሩት ሕክምና ብቻ ሊድን ይችላል፡፡

አንጀቱ ሙሉ ለሙሉ ከሆነ የተዘጋው እና ከላይ የተጠቀሱት ሕክምናዎች ዉጤት አልባ ከሆኑ የቀዶ ጥገና ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል።

 ቀዶ ጥገና ሕክምና

 • ቀዶ ጥገና ሕክምና አስጊ ምልክቶች ከተከሠቱ በድንገተኛ ወይም ከላይ የተጠቀሱት ሕክምናዎች ዉጤት አልባ ከሆኑ ሊደረግ ይችላል።

 • የጤና ባለሙያው በቀዶ ጥገናው ወቅት አንጀቱን የዘጋውን ነገር እና ጤናማ ያልሆነውን የአንጀቱን ክፍል ያስወግዳል፡፡ ቀጥሎም ጤናማ የሆኑትን የአንጀት ክፍሎች በማያያዝ ከአስፈለገም አንጀቱ በደንብ እሲኪያገግም ድረስ ኢሎስቶሚ (ileostomy) ይሠራል።.

ኢሎስቶሚ (ileostomy) ምንድነው? ኢሎስቶሚ ማለት አብዛኛውን ጊዜ በጊዜያዊነት የአንጀትን ጤናማ ጫፍ በሆድ ግድግዳ ላይ በመተው ሰገራ በእሱ በኩል እንዲወጣ ማድረግ ነው። ይህም አንጀት እንዲያገግም ጊዜ ለመስጠት ሲሆን ሕክምናው ከአለቀ በኋላም ወደ ቦታው ይመለሳል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ሳይመለስ  በቋሚነት ሊቀር ይችላል። 

ከቀዶ ጥገናው በኋላ ምን ይደረጋል?

 • ከቀዶ ጥገናው በኋላ ታካሚው ሆስፒታል የሚቆይበትን ጊዜ፣  ምግብ እና ውሃ መቼ መጀመር እንዳለት እና አጠቃላይ ስለአለው ሁኔታ ከጤና ባለሙያው ጋር ይነጋገራሉ።

 • የቁስል ኢንፌክሽን እንዳይፈጥር በባለሙያዎች የቁስል ንጽሕና አጠባበቅ ይደረጋል (Wound care)። በተጨማሪም  መድኃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ።

 • በሆድ ላይ ጎጂ የሆኑ ባህላዊ ሕክምናዎችን መተግበር አያስፈልግም። ለምሳሌ ሆድን በጋለ ብረት ማቃጠል፣ የሆድ ሕመምን እና ቡአን (Hernia) ማሸት ናቸው።

Share the post

scroll top