Learning materials for your health  Learn

የጡት መግል ምንድን ነው?

 • November 10, 2021
 • የጤና እክሎች

ከስሙ መረዳት እንደምንችለው በጡት ውስጥ መግል ሲጠራቀም የጡት መግል ይፈጠራል። ይህ በሽታ በብዛት የሚከሠተው የጡት ደዌ (mastitis) ሳይታከም ሲቀር ነው።

የጡት መግል ሕመም ያለው የጡት እብጠት የሚያመጣ ሲሆን፤ እብጠቱ አካባቢ ያለው ቆዳ ይቀላል፤ ያቃጥላል፡፡ ይህ በሽታ በሚያጠቡትም የማያጠቡትም ሴቶች ላይ ሊከሠት ይችላል።

የጡት መግል የሚፈጠረው እንዴት ነው?

ጡት የሚያጠቡ ሴቶችን የሚያጠቃው የጡት መግልን የሚያስከትለው እስታፍሎኮከስ አውረስ (Staphylococcus aureus) የሚባለው ተሕዋስያን በጡቱ ቆዳ ወይም በጡት ጫፍ ስንጥቅ በኩል ወደ ውስጥ ገብቶ በመጀመሪያ የጡት ደዌ (mastitis) ያመጣል፡፡ ደዌ ጡት ካልታከመ ቁስለቱ መግል ይፈጥርና ጡት ውስጥ ይጠራቀማል። በአንጻሩ ጡት የማያጠቡ ሴቶችን የሚያጠቃው የጡት መግል አብዛኛውን ጊዜ በአኔሮቢክ (anaerobic) ተሕዋስያን ይከሠታል። 

የሚያጠቡ ሰዎችን የሚያጠቃው የጡት መግል የሚፈጠረውም በብዛት የሚከሠተው የሚከትሉት አጋላጭ ሁኔታዎች ያላቸው እናቶች ላይ ነው። እነዚህም ፡ -

 • ከ30 ዓመት በላይ የሆናቸው ሴቶች ላይ

 • ለመጀመሪያ ጊዜ አርግዘው የወለዱ ሴቶች ላይ

 • ትክክለኛ የሆነ የጡት አያያዝ እና አጠባብ መንገድ የማትከተል ከሆነ እና ቶሎ ቶሎ ሳታጠባ ጡቷ በወተት ከተወጠረ ለዚህ በሽታ ያጋልጣታል።

 • እርግዝናቸው ከ 41 ሳምንት በላይ ሆኗቸው የወለዱ ሴቶች ላይ እና

 • የሚደጋገም ወይም በቅርብ የተፈጠረ የደዌ ጡት ያለባቸው እናቶች ላይ ሲሆን፤ በሽታ የመከላከል ዐቅማቸው የደከመ ሰዎች ላይ በብዛት ይከሠታል። 

ምልክቶቹስ ምን ምንድን ናቸው?

 • ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ማንቀጥቀጥ

 • የቀላ፣ የሚያተኩስና ሕመም ያለው የጡት እብጠት

 • የሚታይ መግል ከጡት ጫፍ ሊወጣ ይችላል፡፡

 • ማሳከክ

 • በተጨማሪም ያበጡ ፍርንትቶች (swollen lymph nodes) በብብት ሥር ሊታዩ ይችላሉ። እነዚህ ፍርንትቶች ሊቆስሉ ወይም ሊፈነዱ ይችላሉ።

ብግነቱ (infection) ወደ ሰውነት ከተሰራጨ ደግሞ ራስን መሳት፣ መተንፈስ ማቃት፣ የሽንት መጠን መቀነስ እና ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት ሊኖር ይችላል።

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ከታዩ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራ ማድረግ ይገባል፡፡

በሽታውን ለማወቅ ምን ዓይነት ምርመራ ይደረጋል?

ሐኪሙ በሽታውን ለማወቅ በዋነኝነት የሚጠቀመው ታካሚው የበሽታውን ሁኔታ ከሚነግሩት በመረዳት እና እብጠቱን በመመርመር ነው። ከዚያ ባለፈ ግን እንደ አልትራሳውንድ ያሉ ምርመራዎችን መጠቀም ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪም ከ ደም ወይም ከ መግሉ ላይ በመርፌ ናሙና ተወስዶ በላብራቶሪ ምን ባክቴሪያ እንዳለው ማወቅ ይቻላል።

ምን ምን የሕክምና አማራጮች አሉ?

የጡት መግል ዋና ሕክምናው መግሉን ማስወገድ እና የ ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት መጀመር ነው።

ሐኪሙ መግሉን ለማስወገድ ሁለት መንገዶችን ሊጠቀም ይችላል። 

 1. የመጀመሪያው መንገድ መግሉን በ መርፌ ስቦ ማውጣት ነው፡፡ የመግሉን ቦታ በትክክል ለማወቅ እንዲረዳ ሐኪሙ አልትራሳውንድ ሊጠቀም ይችላል። ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት ሥራ ላይ የሚውለው ቀጣዩ መንገድ ነው፡፡ እሱም

 2.  መግሉ በአለበት ቦታ ላይ በቀዶ ጥገና ማውጣት ነው። ይህም እብጠቱ ትልቅ ከሆነና በተደጋጋሚ ከተከሠተ ሐኪሙ ይኽን መንገድ ሊመርጥ ይችላል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት በብዛት ሥራ ላይ የሚውለው መንገድ ይሄ ነው።

መግሉን ከማስወገድ ሕክምና ባሻገር በሽታውን በአመጡት ተሕዋስያን ላይ በመመርኮዝ ተገቢው የፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት ይታዘዛል። ከዚህ በተጨማሪ ሕመም ካለ ሕመም ማስታገሻ እንዲሁም ሌሎች ምልክቶችን ለማስታገስ መድኃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ። 

ከላይ በተጠቀሰው መሠረት ሕክምናውን ከጨረሱ የሚድን በሽታ ስለሆነ፤ ከታካሚዋ የሚጠበቀው ምልክቶቹን እንዳዩ ወዲያው ወደ ሕክምና መሄድ፣ የታዘዘውን መድኃኒት በተገቢው ጊዜና ሰዓት መውሰድ እና የሐኪም ክትትሉን በሚገባ መከታተል ነው። 

ከዚህ በተጨማሪ መረዳት የሚገባቸው ነጥቦች

 • ከጡት ማጥባት ጋር በተያያዘ እናቲቱ ትክክለኛ የሆነ የጡት አያያዝ እና አጠባብ መንገድ መከተል አለባት፡፡ ይኽ ከአልሆነ እና ቶሎ ቶሎ ሳታጠባ ጡቷ በወተት ከተወጠረ ለዚህ በሽታ ያጋልጣታል። ስለዚህ ይህን በሽታ ለመከላከል እናቲቱ ትክክለኛውን የጡት አያያዝ ማወቅ ይኖርባታል። ይህም፤ 

  • በተቻለ መጠን ሕፃኑን ከፍ አድርጎ ወደ እናቲቱ አስጠግቶ መያዝ

  • የሕፃኑ ጆሮ፣ ትከሻ እና ዳሌ በእናቲቱ እጅ ላይ አርፎ፣ ሕፃኑ ሙሉ በሙሉ ወደ እናቲቱ መዞር አለበት። ድጋፍ ከአስፈለገ እናቲቱ ከእጇ ሥር ትራስ ማድረግ ትችላለች።

  • ከዚያም ሕፃኑ አፉን ሙሉ ለሙሉ መክፈቱን ማረጋገጥና  የጡቱን ጫፍ አፉ ውስጥ መክተት። ከሥር በኩል ያለው የልጁ ከንፈር መገልበጡን ማረጋገጥ። ሲጠባ አፉ መራሱ፣ ወተቱን ሲስብ የሚያሰማው ድምፅ እና ከጠባ በኋላ መተኛቱ ሕፃኑ በደንብ እንደጠባ ማረጋገጫ መንገዶች ናቸው።

 • ምንም እንኳን ጡት መግል ቢኖረውም ሐኪምዎ ማጥባት እስከአልከለከለዎት ድረስ ማጥባትዎን መቀጠል ይችላሉ።

 • ቁስሉ ላይ የባህል መድኃኒት ከማድረግ ይቆጠቡ።

 • ከቀዶ ጥገና በኋላ መግሉ በደንብ እንዲወጣ እና ቁስሉ እንዲድን (ድጋሚ መግል እንዳይይዝ) ተብሎ አይዘጋም። እንደ ቁስሉ ሁኔታ ለተወሰኑ ቀናት ሊጸዳ ይችላል።  

Share the post

scroll top