Learning materials for your health  Learn

የኪንታሮት በሽታ (hemorrhoids)

  • November 25, 2021
  • የጤና እክሎች

ኪንታሮት በታችኛው የፊንጢጣ ክፍል ያሉ የደም መላሽ ደም ሥሮች ሲሰፉ ወይም ሲያብጡ የሚፈጠር በሽታ ነው። በሁሉም የዕድሜ ክልል እና በሁለቱም ፆታዎች ላይ የሚከሠት ቢሆንም በብዛት ከ 45 እስከ 65 ዓመት ባሉት ላይ ይታያል።  

ኪንታሮት አብዛኛውን ጊዜ ከባድ የጤና ችግር የማያመጣ ቢሆንም፤ ምቾት የሚነሣ እና የሚረብሽ ስሜት ይኖረዋል ፡፡ 

የኪንታሮት ዓይነቶች

  • ውጫዊ ኪንታሮት (external hemorrhoids) ፡- በላይኛው ቆዳ ላይ የሚገኝ  ሲሆን  ሕመምም አለው

  • ውስጣዊ ኪንታሮት (internal hemorrhoids) ፦ በፊንጢጣ ውስጥ የሚገኝ  ሲሆን  ሕመም  የለውም

ውስጣዊ ኪንታሮት አራት ደረጃዎች አሉት፡፡

የኪንታሮት ምልክቶች

የኪንታሮት በሽታ ምልክቶች እንደ በሽታው ደረጃ ይወሰናሉ፡፡

ደረጃ 1 - ሕመም የሌለው በፊንጢጣ ደም መፍሰስ፤ አብዛኛውን ጊዜ ደማቅ ቀይ በመጠኑ ትንሽ የሆነ ደም ያስተውላሉ፡፡ 

ደረጃ 2 - በሚጸዳዱበት ወቅት በፊንጢጣ በኩል የሚወጣ በራሱ የሚመለስ እብጠት  ይኖራል፡፡

ደረጃ 3 - በሚጸዳዱበት ወቅት በፊንጢጣ በኩል የሚወጣ እና በእጅዎ ካልመለሱት በስተቀር በራሱ የማይመለስ እብጠት አለው፡፡

ደረጃ 4 - ተመልሶ የማይገባ በፊንጢጣ በኩል የሚወጣ እብጠት ነው፡፡

በተጨማሪም በማንኛውም ደረጃ ላይ ያለ የኪንታሮት በሽታ የሚከተሉት ምልክቶች ሊኖሩት ይችላል፡፡  

  • የሰገራ መውጫ አካባቢ ማሳከክ  

  • የድካም ስሜት፣ ማዞር ወይም ጆሮ ላይ መጮህ የመሳሰሉ የደም ማነስ ምልክቶች፡፡

  • ፊንጢጣ አካባቢ ሕመም -  ከባድ ሕመም የሚሰማዎ  ከሆነ  ወደ ጤና ተቋም ወዲያውኑ ይሂዱ፤ ምክንያቱም ይህ የከፋ ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡

ለኪንታሮት በሽታ አጋላጭ ሁኔታዎች 

  • የሆድ ድርቀት 

  • አነስተኛ የፋይበር መጠን ያላቸው ምግቦችን ማዘውተር 

  • እርግዝና 

  • ሆድ ዕቃ ውስጥ የሚፈጠር እጢ

  • የአንጀት ንጣፍ ውሃ መቋጠር (ascites)

  • ከመጠን በላይ ውፍረት

  • ሽንት ቤት ሲጠቀሙ ማማጥ

  • ረጅም ጊዜ የቆየ ተቅማጥ (chronic diarrhea)

  • በቤተሰብ  ተመሳሳይ በሽታ ያለበት ካለ

  • ዕድሜ  መጨመር

  • የሕብለ ሰረሰር ጉዳት (spinal cord injury)

  • ኢመደበኛ/ የፊንጢጣ ወሲብ (anal intercourse)

ለኪንታሮት በሽታ የሚደረግ  ምርመራ

  • ሙሉ አካላዊ ምርመራ

  • አኖስኮፒ (anoscopy)፣ ሲግሞይዶስኮፒ (sigmoidoscopy)፣ ፕሮክቶስኮፒ (proctoscopy) የመሳሰሉ ካሜራ የተገጠመላቸው ቀጭን ቱቦዎች በፊንጢጣ በማስገባት የሚደረግ ምርመራ

  • የደም ምርመራ - የደም ማነስ ወይም ተያያዠ በሽታ መኖሩን ለማየት

የኪንታሮት  ሕክምና

የሆድ ድርቀትን መከላከል - ኪንታሮትን ለማከም በጣም አስፈላጊ ከሆኑት እርምጃዎች አንዱ የሆድ ድርቀትን መከላከል ነው፡፡ ደረቅ ሰገራ በፊንጢጣ ላይ የደም መፍሰስ እና የፊንጢጣ መሰንጠቅ (anal fissure) ያስከትላል፡፡ በተጨማሪም  ለረጀም ሰዓት ማማጥ ያለውን ኪንታሮት ሊያባብሰው ወይም በአዲስ ኪንታሮት የመያዝ ዕድልን ይጨምራል፡፡ የሆድ ድርቀትን ለመከላከል ከዚህ ቀጥሎ የተገለጹትን መንገዶች መከተል ይችላሉ፡፡

  • በፋይበር የበለጸጉ ምግቦችን መመገብ  - በቀን ከ 20 እስከ 35 ግራም  ፋይበር ያለው የአመጋገብ ሥርዓት ይመከራል። ፋይበር በአብዛኛው ፍራፍሬዎችና አትክልቶች ውስጥ ይገኛል፡፡ 

  • መደበኛ ሰዓት ያለው የመጸዳጃ ቤት አጠቃቀም ሊኖር ይገባል፡፡

  • በቂ ውሃ መጠጣት - በቀን እስከ 2 ሊትር ይመከራል፡፡

  • የሰገራ ማለስለሻ (Laxatives) - ፋይበርን  ምግብ ውስጥ መጨመር የሆድ ድርቀትን ካልቀነሰው የሰገራ ማለስለሻ መድኃኒቶች መውሰድ ጥቅም አለው፡፡ 

ብዙ ሰዎች እነዚህ መድኃኒቶች ከተቋረጡ በኋላ የሆድ ድርቀት ይከተላል በሚል ስጋት ከመውሰድ ሲቆጠቡ ይታያል፡፡ ነገር ግን  እነዚህ መድኃኒቶች “ሱስ” የማስያዝ ዐቅም የላቸውም፤ ለወደፊቱም  በሆድ ድርቀት የመያዝ ተጋላጭነትን አይጨምሩም። 

ሆኖም ማንኛውንም የሰገራ ማለስለሻ መድኃኒት ከመውሰድ በፊት ሐኪምን ማማከር አስፈላጊ ነው፡፡ 

ለብ በአለ ውሃ መዘፍዘፍ (sitz bath) -  በየቀኑ ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ ከ 10 እስከ 15 ደቂቃዎች  ከ2 እስከ 3 ኢንች ጥልቀት ባለው ለብ ያለ ውሃ ውስጥ ጨው ጨምሮ በመቀመጥ የፊንጢጣን አካባቢ መዘፍዘፍ ይመከራል፡፡ ተጨማሪ ሳሙና ወይም ሌሎች ንጥረ ነገሮችን መጠቀም አይመከረም፡፡ ይህን ማድረግ ፊንጢጣ አካባቢ ያለውን የደም ዝውውር የሚያሻሸል እና በዙሪያው የሚገኙትን ጡንቻዎች ከመኮማተር ይከላከላል።

የሚቀቡ መድኃኒቶች - ኪንታሮትን  ለማከም የተለያዩ የሚቀቡ መድኃኒቶች አሉ፡፡ ብዙዎቹ ያለ ሐኪም ማዘዣ ቢገኙም፤ ሥር የሰደደ እና የከፋ በሽታ ሊሆን ስለሚችል በቅድሚያ ሐኪም ሳያይዎ መድኃኒቶቹን አይጀምሩ፡፡ እነዚህ መድሃኒቶች ቢያንስ  ለጊዜው ሕመምን፣ እብጠትን እና ማሳከክን ለማስታገስ ሊረዱ ይችላሉ ፡፡

  • ማንኛውንም የኪንታሮት በሽታ መድኃኒቶች የጤና ባለሙያ ሳይፈቅድልዎ እንዳይጅምሩ አበክረን እንመክራለን፡፡

  • ባህላዊ መድኃኒቶችን ከመጠቀም ይቆጠቡ። እስከ ሞት ደረጃ የሚያደርስ የፊንጢጣ መጥበብ፣ መግል መያዝ፣ የተዛመተ የቆዳ ኢንፌክሽን እና ከፍተኛ ደም መፍሰስ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ባህላዊ ሕክምናዎችን እንዲያደርጉ ፈጽሞ አይመከርም። 

ቀላል ያሉ የቀዶ ጥገና  ሕክምናዎች 

ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ውስጣዊ የኪንታሮት ምልክቶችን መቆጣጠር ከአልተቻለ የሚከተሉት ቀለል ያሉ የቀዶ ጥገና አማራጮች አሉ። እነዚህም ለመለስተኛ እና በጊዜ ለተገኙ የኪንታሮት እብጠቶች የሚጠቅሙ ናችው። 

  • ኪንታሮትን  በጎማ ቀለበቶች ማሰር (rubber band ligation) - ከመደበኛ የቀዶ ጥገና ሕክምና ውጪ በሃገራችን  የሚገኘው የሕክምና አማራጭ ነው፡፡ ሂደቱም የጎማ (ላስቲክ) ቀለበቶች በውስጠኛው የኪንታሮት መሠረት ዙሪያ ይጠመጠማል፡፡ ይህም የደም አቅርቦቱ እንዲዘጋ በማድረግ ኪንታሮቱ ቀስ በቀስ በመጠን እየቀነሰ እንዲመጣ እና ተበጥሶ እንዲወድቅ ያደርገዋል፡፡ ይህ ሕክምና ከ 70 እስከ 80 በመቶ በሚሆኑት ታካሚዎች ላይ ውጤታማ ነው ፡፡

ከዚህ ሂደት በኋላ የፊንጢጣ አካባቢ ጡንቻዎችን መኮማተር ለመከላከል ለብ ባለ ውሃ መዘፍዘፍ፣ የሆድ ደርቀትን ለመከላከል ፋይበር ወይም የሰገራ ማለስለሻ መውሰድ ይመከራል።

  • የላስቲክ ማሰሪያው ብዙውን ጊዜ  ከሁለት እስከ አራት ቀናት በኋላ በሚወድቅበት ጊዜ  የደም መፍሰስ ሊከሠት ይችላል።              

      አልፎ አልፎ ከባድ ሕመም፣  የኪንታሮት የደም ሥሮች ውስጥ ደም መርጋት፣ኢንፌክሽን ወይም መግል መያዝ ሊያከትል ይችላል፡፡ ሆኖም ቢችልም አብዛኛውን ጊዜ ከባድ መዘዝ የማስከተል ዕድሉ አነስተኛ ነው፡፡

  • የጨረር ሕክምናዎች - እነዚህ ዘዴዎች የውስጥ ኪንታሮትን ለማጥፋት ጨረር፣ ኢንፍራሬድ  ወይም ሙቀት መጠቀምን ያካትታሉ፡፡ 

  • ስክሌሮቴራፒ (sclerotherapy) - ይህ ሕክምና ኬሚካል ወደ ኪንታሮት ኅብረ ሕዋስ በመርፌ በመውጋት እንዲፈርስ እና ጠባሳ እንዲፈጠር በማድረግ ይሠራል።

ለኪንታሮት የሚደረግ መደበኛ የቀዶ ጥገና

ከላይ የተጠቀሱት የሕክምና መንገዶች ውጤታማ ከአልሆኑ መደበኛ የኪንታሮት ቀዶ ጥገና ሕክምና ማድረግ ቀጣዩ አማራጭ ይሆናል፡፡ ይህ ሕክምና በኪንታሮት በሽታ ምክንያት ያበጠውን ትርፍ ሥጋ መቁረጥ ሲያካትት፤ 95 በመቶ የሚሆኑ ታካሚዎች ላይ አመርቂ ውጤት ያሳያል።

Share the post

scroll top