Learning materials for your health  Learn

በእርግዝና ወቅት የሚታዩ ተፈጥሮዓዊ ለውጦች ምን ምንድናቸው?

 • December 7, 2021
 • የጤና እክሎች

በእርግዝና ወቅት በጣም ብዙ የሚታዩ እና የማይታዩ አካላዊ ለውጦች ይከሠታሉ። እነዚህ ተፈጥሮአዊ ለውጦች የሚኖሩት በተለያየ ምክንያት ነው። ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ

 1. ለእናትየው እና ለሚያድገው ፅንስ በቂ ምግብ እንዲኖር ለማድረግ፤ (ግሉኮስ፣ አሚኖ አሲድ፣ ኦክስጅን) 

 2. ከወሊድ በኋላ ለልጁ የሚሆን የጡት ወተት ለማዘጋጀት፤ 

 3. አላስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን ለማስወገድ፤ ለምሳሌ ካርቦንዳይኦክሳይድ

 4. እናት እና ልጅን ከበሽታ እና ከአደገኛ ንጥረ ነገሮች ለመጠበቅ፤ ለምሳሌ የእንግዴ ልጅ ከፅንሱ በተጨማሪ እናትየውን ከፅንሱ የወንድ ልጅ ሆርሞን ይጠብቃታል፡፡

 5. ለፅንሱ ተስማሚ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር፤

 6. ማሕፀንን እና የዳሌ መገጣጠሚያዎችን ለምጥ እና ለወሊድ የተዘጋጁ ማድረግ ናቸው።

እነዚህ ለውጦች እንዴት ይከሠታሉ?

በሚከተሉት ዐበይት  ለውጦች  ምክንያት ይከሠታሉ። 

የሆርሞን ለውጦች (hCG,hCC,hCS Progesterone,Oestrogens, Prolactin...)

ሆርሞኖቹ የሚመረቱትም፤

 • በእንግዴ ልጅ

 • በእናት እና በፅንሱ ነው፡፡

በአጠቃላይ የእነዚህ ሆርሞኖች ሥራ ልጁ ተፀንሶ እስኪወለድ ድረስ ተስማሚ ሁኔታን መፍጠር  ነው፡፡ በዚህም ለፅንሱ ዕድገት እና በእርግዝና ወቅት ለሚፈጠሩ ሁለንተናዊ  የእናት አካል ለውጦች ሐላፊነትን ይወስዳሉ።

የእናት በሽታን የመከላከል ሥርዓት

የእናት በሽታን የመከላከል ሥርዓት ፅንሱን ለመቀበል እና ለመላመድ የተለያዩ ለውጦችን ያደርጋል።

በተፈጥሮ የነበረው (Innate immune) የመከላከል ሥርዓት ዐቅሙን ሳይቀንስ ይቀጥላል፡፡ 

በመላመድ የሚገኘው (Cell mediated immune) የመከላከል ሥርዓት ፅንሱን እንዳያጠቃው ዐቅሙን እንዲቀንስ ይደረጋል፡፡

ይህም ለውጥ እናትዬዋን በቫይረስ ምክንያት ለሚከሠቱ አንዳንድ በሽታዎች ተጋላጭ ሲያደርጋት፤ ከአንዳንድ በሽታዎች ግን ይጠብቃታል። ለምሳሌ አውቶኢምዩን (autoimmune disease) የሚባል በሽታን ሊያስታግስላት ይችላል።

አመጋገብ እና የክብደት ለውጦች (Nutritional & weight change)

በእርግዝና ወቅት አንዲት እናት የሰውነት ክብደቷ እንዲጨምር ይጠበቃል። ምን ያህል ይጨምር የሚለው ከእርግዝናዋ በፊት በነበረው የሰውነት ክብደቷ ላይ ይወሰናል ። 

 • ዝቅተኛ ክብደት (ቢ ኤም አይ < 18.5 ኪ.ግ. / ሜ 2) ከነበራት፤ 12.5 - 18 ኪ.ግ. መጨመር አለባት፡፡

 • መደበኛ ክብደት (ቢ ኤም አይ 18.5 - 24.9 ኪ.ግ. / ሜ 2)፤ 11.5 - 16 ኪ.ግ. 

 • ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው ሴቶች (ቢ ኤም አይ 25 - 29.9 ኪ.ግ. / ሜ 2)፤ - 7 - 11.5 ኪ.ግ.

 • ውፍረት (ቢ ኤም አይ > 30 ኪ.ሜ / ሜ 2)፤ 5 - 9 ኪ.ግ. 

አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ብዙ ጊዜ ክብደት የምትጨምረውም ከ 20 ሳምንታት (5 ወር) የእርግዝና ወቅት በኋላ ነው። 

የአመጋገብ ለውጦች

 • በቀን ውስጥ ከምግብ የምታገኘው የኃይል መጠን ከእርግዝናዋ በፊት ከነበረው ቢያንስ በ 14% ቢጨምር ይመከራል።

 • በአጠቃላይ ነፍሰ ጡር ከመሆኗ በፊት ጤናማ ክብደት የነበራት እናት በቀን ከ2,200 -2,900 ካሎሪ ያስፈልጋታል፡፡ እርግዝናው እየገፋ በሄደ ቁጥር የሚያስፈልጋት የኃይል መጠንም እየጨመረ ይሄዳል።

 • ይህም በእናትዬዋ ደም ውስጥ ያሉትን የካርቦሃይድሬት እና የፕሮቲን መጠንን በመጨመር ግሉኮስ ወደ ፅንስ በእንግዴ ልጅ በኩል እንዲያልፍ ያደርጋል።

ምንም እንኳን በእናትየው ደም ውስጥ የአለው የግሉኮስ መጠን ቢጨምርም በደሟ ውስጥ ያሉት ሆርሞኖች  እናትየው  ግሉኮስን  እንዳትጠቀም  በመከልከል  ለፅንሱ  ያስቀራሉ። ይህም በእርግዝና ምክንያት ለሚመጣው የስኳር በሽታ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል።

በጨጓራ - አንጀት ላይ የሚከሠቱ ለውጦች (Gastrointestinal change)

 • በደረት ወይም በጉሮሮ ላይ የማቃጠል ስሜት 

 • የሆድ ድርቀት፣ የምግብ አለመንሸራሸር

ይህም በፕሮጄስትሮን እና በሪላክሲን ሆርሞኖች ምክንያት ለስላሳ ጡንቻዎችን መኮማተር ስለሚቀንሱ ነው።

የማቅለሽለሽ፣ የማስታወክ ስሜት (Morning sickness)

ይህ ብዙ ጊዜ በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት አካባቢ ይከሠታል። አንዳንድ ጊዜ እርግዝና ከመታወቁ  በፊት እነዚህ  ምልክቶች ሊታዩ ይችላሉ። ነገር ግን ይኽ ስሜት የሚቆየው በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወሮች ብቻ ነው።

 የአተነፋፈስ ሥርዓት ለውጦች (Respiratory system)

በእርግዝና ወቅት ነፍሰ ጡር እናት የኦክስጅን ፍላጎቷ ይጨምራል። ከወትሮው የበለጠ የድካም ስሜት እና የአየር እጥረት እንዳለ ይሰማታል። 

የአተነፋፈስ ሥርዓቷ ስለሚዳብር ካርቦንዳይኦክሳይድ ከሰውነቷ የማስወገድ ዐቅሟም ይጨምራል።

 የልብና የደም ቧንቧ ለውጦች (Cardiovascular changes)

 • በእርግዝና ወቅት የደም ዝውውር መጠን እና የልብ ምት ይጨምራል። 

 • የልብ ምት ከ 10 - 15 ደቂቃ ይጨምራል። ልብም ከቀድሞ በ 250 % በበለጠ ሁኔታ ደምን ወደ ማሕፀን ያደርሳል።

 • የደም ቧንቧዎች ይሰፋሉ፡፡ ይህም በእርግዝና ጊዜ የደም ግፊት እንዲቀንስ ያደርጋል።

ሌሎች የሚከተሉትን ያጠቃልላል። 

 • በእግር  ወይም በቁርጭምጭሚት አካባቢ ቀላል እብጠት 

 • እጅ፣ እግር አካባቢ መደንዘዝ ወይም መንቀጥቀጥ 

 • ኪንታሮት (በፊንጢጣ ውስጥ ያበጡ የደም ሥሮች) 

 • በታፋ እና በእግር አካባቢ ያሉት የደም ሥሮች ማበጥ እና መገታተር (Varicose vein) 

ነፍሰ ጡር እናት በጀርባዋ ሳይሆን በጎኗ እንድትተኛ ለምን ይመከራል? (Supine hypotension)

ከ 24 ሳምንታት የእርግዝና ወቅት በኋላ እናትየው በተለይም በጀርባዋ ቀጥ ብላ የምትተኛ ከሆነ ማሕፀን በቀኝ በኩል ያለውን ዋና የደም ሥር ሊጫን ይችላል። ይህም ወደ ልብ የሚመለሰውን የደም መጠን በመቀነስ የማዞር፣ የማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ እና ራሷን ሊያስታት ይችላል። 

በደም ውስጥ ያለው ፈሳሽ እና የደም ሕዋሳት ለውጥ 

በደም ውስጥ ያለው ፈሳሽ እና የደም ሕዋሳት ይጨምራሉ። ቀይ እና ነጭ የደም ሕዋሳት ሲጨምሩ ፕላቴሌቶች ግን ይቀንሳሉ።

ነፍሰ ጡር እናት የአይረን እንክብልን ለምን ትወስዳለች?

የደም ፈሳሽ መጠን በ 40 - 45% የሚጨምር ሲሆን፤ ቀይ የደም ሕዋስ ግን በ 18% ብቻ ይጨምራል። ስለዚህም ይህንን ልዩነት ለማካካስ እና ደም ማነስን ለመከላከል ቀይ የደም ሕዋስ መጨመር አስፈላጊ ይሆናል። በዚህም ምክንያት ደም ማነስ ባይኖራት እንኳን አይረን እንድትወስድ ይደረጋል።

እርግዝና ለደም መርጋት ሕመም አጋላጭ ነውን?

እርግዝና ለደም መርጋት ሕመም አጋላጭ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ደም በአንድ አካባቢ ረግቶ እንዲቆይ፣ በወሊድ ጊዜ የደም ሥሮች እንዲጎዱ እና በደም ውስጥ ያሉ ደም እንዲረጋ የሚያደርጉ ንጥረ ነገሮች እንዲጨምሩ በማድረግ የደም መርጋትን ሊያመጣ ይችላል፡፡

የኩላሊት እና የሽንት ቧንቧ ሥርዓት (Renal & urinary tract change)

የኩላሊት ደምን የማጣራት ዐቅም ይጨምራል። የሽንት ቧንቧ መኮማተርን ስለሚቀንሱ መጠነኛ ሽንት ኩላሊት እና የሽንት ፊኛ ውስጥ ሊጠራቀም ይችላል።

በተለይም በመጀመሪያ እና በመጨረሻው የእርግዝና ወቅቶች ሽንት ከተለመደው በበለጠ ብዙ ጊዜ ለመሽናት መፈለግ ይኖራል። ምክንያቱ ደግሞ እያደገ የሚመጣው ማሕፀን እና ፅንስ የሽንት ከረጢትን ስለሚጫነው ነው።

የፀጉር እና የቆዳ ለውጦች (Hair and skin changes)

 • የፀጉር መፋፋት እና ማደግ

 • የቆዳ ቀለም መለወጥ 

  • መዳፍ ሐምራዊ ወይም ቀይ መሆን 

  • ፊት ላይ ማድያት መውጣት

  • የሰውነት ቆዳ  እና የጡት ጫፎች መጥቆር  

  • ከሆድ አንሥቶ እስከ ብልት በዠድ አጥንት (Pubic symphysis) ድረስ እንደ ጥቁር ያለ መስመር መውጣት 

  • በሆድ፣ በጡት እና በጭን ላይ እንደ ቀይ ያሉ ሸንተረሮች መውጣት  ናቸው።

የሴት የመራቢያ ሥርዓት (Reproductive system)

 • ማሕፀን በመጠኑ በአማካኝ ከ 50 – 1000 ግራም ይጨምራል።

 • የማሕፀን እና የዳሌ አካባቢ የደም ፍሰታቸው ይጨምራል። 

 • የሴት የመራቢያ አካላት ጡንቻቸው ይጨምራል፤ ይለሰልሳሉ እናም ለወሊድ የተዘጋጁ ይሆናሉ።

 • ጡት በመጠን ይጨምራል፤ ሕመም ሊኖራቸውም ይችላል።

እርግዝና እየገፋ ሲሄድ ከላይ የታዩት ለውጦች  በቀስታ እየተባባሱ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ እነዚህም

 • የድካም ስሜት

 • ወገብ አካባቢ ሕመም፣ እግርን እንደመቆርጠም ያለ ሕመም፣ የመተኛት ችግር 

 • ከተለመደው በላይ ወይም በሌሊት ብዙ ጊዜ ለመሽናት መሞከር

 • የውሸት ምጥ (Braxton hicks) ይህ አልፎ አልፎ የሚከሠት ከበድ ያለ የሆድ ሕመምን የሚያመጣ የሆድ ቁርጠት ነው። 

ነገር ግን በእርግዝና ወቅት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት  አደገኛ ምልክቶችን ከታዩ በአፋጣኝ ወደ ጤና ጣቢያ መሄድ ያስፈልጋል።  

 • በማሕፀን በኩል የደም መፍሰስ  ወይም  የሚፈስ ፈሳሽ  ከአለ

 • የፅንሱ እንቅስቃሴ ከወትሮው ከቀነሰ

 • በማስታገሻ የማይሻል የወገብ  ወይም የሆድ ሕመም  

 • ዕረፍት በማድረግ ወይም በመድኃኒት የማይሻል የራስ ምታት

 • ሽንት በሚሸኑበት ጊዜ ማቃጠል፣ በሽንት ውስጥ ደም፣ እንዲሁም ትኩሳት ከአለ ፈጥኖ ወደ ጤና ጣቢያ መሄድ አስፈላጊ ነው።

Share the post

scroll top