Learning materials for your health  Learn

በእርግዝና ወቅት መደረግ ያለባቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

 • December 15, 2021
 • የጤና እክሎች

የእርግዝና ጊዜ በሰላም አልፎ ሙሉ ጤነኛ ልጅ ለመውለድ እንዲሁም የእናት እና የልጅ ጤንነት እንደነበረ እንዲቀጥል የሚረዱ የተለያዩ ነገሮች አሉ። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ነገሮች በእርግዝና ወቅት የሚከናወኑ ቢሆኑም፤ አንዳንዶቹ ግን እርግዝና ከመፈጠሩ በፊት የሚደረጉ ናቸው።

እስኪ አንዲት እርጉዝ እናት (ለማርገዝ እየሞከረች ያለች እናት) ማድረግ ያለባትን ነገሮች እንመልከት።

1. የቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረግ

2. እንደ አይረን እና ፎሌት ያሉ ንጥረ ነገሮችን መውሰድ 

አይረን የሚሰጠው እርጉዝ እናቶች ለደም ማነስ የተጋለጡ ስለሆኑ ነው። በዋነኛነት አይረን በመውሰድ በወሊድ ጊዜ በሚፈስሰው ደም ምክንያት የደም ማነስ እንዳይከሠት ይከላከላል። ከአይረን በተጨማሪ አንዲት እርጉዝ እናት ፎሌት የሚባል ንጥረ ነገር ትወስዳለች። ይህም ንጥረ ነገር በዋነኛነት የሚያገለግለው ደግሞ ለፅንሱ ዕድገት ነው። በመሆኑም ከተቻለ እናቲቱ ከማርገዟ ከሳምንታት በፊት መውሰድ ብትጀምር ጥሩ ነው። ከአልሆነ ግን ልክ ማርገዟ እንደታወቀ መጀመር ይጠበቅባታል።

3. የመንጋጋ ቆልፍ ክትባት መከተብ 

ይህም ለእናትዬዋ የተሰጠው ክትባት በእትብት በኩል ለፅንሱ ስለሚተላለፍ በጨቅላ ዕድሜ ከሚከሠት መንጋጋ ቆልፍ በሽታ ይከላከልለታል። ከዚህ በፊት ክትባቱን ከአልተከተቡ በእርግዝናው ወራት ውስጥ ሦስት ጊዜ፤ እንዲሁም ለሚቀጥሉት እርግዝና እንዲያገለግል ሕፃኑ ከተወለደ በኋላ ሁለት ጊዜ መከተብ ከእናቶች ይጠበቃል።

4. ነፍሰ ጡሯ እርግዝናዋ ከገፋ በኋላ (ከ6 ወር ጀምሮ) በጎኗ እንድትተኛ ይመከራል፡፡ ከ6 ወር በኋላ በጀርባ ተንጋሎ መተኛት የደም ቧንቧን ስለሚጫን ለጤና ጥሩ አይደለም።

5. ማንኛውም ዓይነት መድኃኒቶችን ከመውሰድ በፊት ሐኪምን ማናገር፡፡ መድኃኒቶቹ የተጀመሩት ከእርግዝናው በፊት ቢሆንም እንኳን መድኃኒቱን ለመቀጠል ሐኪምን ማናገር አስፈላጊ ነው፡፡ ሐኪሙ ጉዳት እና ጥቅሙን አመዛዝኖ መድኃኒቱን እንዲቀጥሉ ወይም እንዲቀየር ይመክርዎታል።

6. በእርግዝና ወቅት ከማጨስ፣ አልኮል ከመጠጣት እንዲሁም አደንዛዥ ዕፅ ከመጠቀም ይቆጠቡ። ከእነዚህ በተጨማሪ እንደ ቡና፣ ቸኮሌት እና ኮካ ኮላ ያሉ በውስጣቸው ካፊን የሚባል ንጥረ ነገር የያዙ ምግብ እና መጠጦችን መቀነስ። በእርግዝና ወቅት ከፍተኛ የሆነ ካፊን መጠቀም ለውርጃ ሊዳርግ ይችላል።

7. በእርግዝና ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ መውሰድ እና ተገቢ የሆነ የክብደት መጨመር መኖሩን ማረጋገጥ

8. በተቻለ መጠን አደጋን መቀነስ 

ይህንንም ምቹ ጫማ በማድረግ እንዲሁም ጉልበት የሚጠይቁ እና አደጋ ሊፈጥሩ የሚችሉ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ በመቆጠብ ማሳካት ይቻላል።

9. በእርግዝና ወቅት አሳሳቢ የሚባሉ ምልክቶችን ለይቶ ማወቅ እና ችግሮቹ ከተከሠቱ ቶሎ ወደ ሐኪም ቤት መሔድ ያስፈልጋል። እነዚህም ምልክቶች የሚባሉት፤

 • ከማሕፀን የሚፈስ ደም

 • የእንሽርት ውሃ መፍሰስ

 • ትኩሳት፡ ብርድ ብርድ ማለት

 • ከብልት የሚወጣ መጥፎ ሽታ ያለው ፈሳሽ

 • ራስ ምታት

 • የእይታ መደብዘዝ

 • የሚያቃጥል የደረት ሕመም

 • ማንቀጥቀጥ

 • ራስን መሳት

 • የእጅና የፊት ማበጥ 

 • የፅንሱ እንቅስቃሴ መቀነስ እንዲሁም

 • ወደ ታች የሚገፋ ሕመም ናቸው።

10. በተጨማሪም በእርግዝና ጊዜ እንዲሁም ከወለደች በኋላ በአሉት ጥቂት ወራት ውስጥ የስሜት መለዋወጥ እና መረበሽ ሊኖር ይችላል። ከዚህም አልፎ ተርፎ እንደ ድባቴ ያሉ የሥነ ልቦና ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ይህንን ከወዲሁ በመረዳት ለእናቲቱ ተገቢውን እንክብካቤ እና ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል።

ከላይ የተጠቀሱትን 10 ዐበይት ምልክቶች በሚገባ ከተከተሉ ጤናማ የእርግዝ ወራት ማሳለፍ፤ እንዲሁም ጤናማ ሕፃን የማግኘትን ዕድልዎን ይጨምራሉ። 

 

Share the post

scroll top