ሄፕታይተስ ኤ (Hepatitis A)
- February 24, 2022
- የጤና እክሎች
ሄፕታይተስ ኤ በሽታ፤ ሄፕታይተስ ኤ በሚባል ቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ የጉበት በሽታ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ 2018 በአሜሪካ ውስጥ በአጠቃላይ 12,474 የሄፕታይተስ ኤ ተጠቂዎች እንደሚገኙ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ የበሽታው መጠን ከ 1995 ወደ 2011 እ.ኤ.አ. በአሜሪካ ከ 95 በመቶ በላይ ቀንሷል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ላይ ግን አሁንም በሽታው በስፋት ይገኛል።
ሄፕታይተስ ኤ ቫይረስ የሚሰራጨው እንዴት ነው?
ሄፕታይተስ ኤ (Hepatitis A) በሽታ አምጭ የሆነው ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ ይተላለፋል። ቫይረሱ በዋነኛነት በበሽታው በተጠቃ ሰው ሰገራ እና ደም ውስጥ ይገኛል፡፡ ማንኛውም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሰገራ ጋር ንክኪ ያለው ነገር ወደ አፍ ከገባ በሽታው ይተላለፋል። ለዚህም ነው ዋነኛው የመተላለፊያ መንገዱ የተበከለ ምግብ መመገብ እና የተበከለ ውሃ መጠጣት የሆነው።
የበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎች ምን ምንድን ናቸው?
-
የንጽሕና ጉድለት
-
ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እጥረት
-
በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በአንድ ቤት ውስጥ መኖር
የበሽታው ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?
ምንም እንኳን በብዛት በበሽታው የሚጠቁት ሕፃናት ቢሆኑም ብዙውን ጊዜ ምልክቶችን አያሳዩም፡፡ በአንፃሩ በዐዋቂዎች ላይ ከባድ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላል። በአጠቃላይ ግን ቫይረሱ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ ምልክቶችን እስከሚያሳይ ድረስ ያለው ጊዜ ከ14-28 ባሉት ቀናት ውስጥ ነው፡፡
የ ሄፓታይተስ ኤ በሽታ ምልክቶች ከቀላል እስከ ከባድ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ቀላል የሚባሉት ምልክቶች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ።
-
የድካም ስሜት
-
ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ
-
የምግብ ፍላጎት መቀነስ
-
ትኩሳት
-
የሆድ ሕመም (የላይኛው ሆድ ክፍል በስተቀኝ በኩል)
ከባድ የሚባሉት ምልክቶች ደግሞ
-
የዐይን እና የቆዳ ቀለም ወደ ቢጫነት መቀየር
-
የጠቆረ ሽንት መሽናት
-
ሰውነትን ማሳከክ
-
አልፎ አልፎ ለሞት ሊዳርግ የሚችል የጉበት ጉዳት ያስከትላል፡፡ በአጠቃላይ በበሽታው ከተያዙ 1000 ሕፃናት ውስጥ አንዱ ይሞታል።
አብዛኛውን ጊዜ ምልክቶቹ የሚቆዩት ከ 2 ወራት ለአነሰ ጊዜ ቢሆንም፤ ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑ ሕመምተኞች ላይ 6 ወርና ከዚያ በላይ ሊቆዩ ይችላሉ።
ከሌሎች የሄፐታይተስ ቫይረስ ዓይነቶች በተለየ የሄፕታይተስ ኤ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ሥር በሰደደ የጉበት በሽታ አይያዙም።
አንዴ በሽታው ከያዘ በኋላ ድጋሚ ሊይዝ ይችላል?
በሽታው ከያዘን በኋላ ሰውነታችን የሚያዘጋጀው ኢሚውኖግሎቡሊን ጂ (IgG) የተባለው ንጥረ ነገር በበሽታው ድጋሜ እንዳንያዝ ይረዳናል። በዚህ ምክንያት አንዴ በዚህ በሽታ የተያዘ ሰው ድጋሚ አይያዝም።
ሄፕታይተስ ኤ እንዴት ይታከማል?
ብዙ ጊዜ በሽታው በራሱ ጊዜ ይድናል፡፡ ቶሎ ለመዳን ደግሞ ከሥር የተዘረዘሩትን ነጥቦች መተግበር ይገባል።
-
በቂ ዕረፍት መውሰድ
-
አልኮል ከመጠጣት መቆጠብ
-
የተወሰኑ መድኃኒቶችን ማስወገድ፤ የትኞቹን መድኃኒቶች መውሰድ እንደማይገባ ለማወቅ ከሐኪም ጋር መነጋገር አስፈላጊ ነው።
አልፎ አልፎ በሽታው የጠናባቸው ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በሆስፒታል ውስጥ ሆነው መታከም ሊያስፈልጋቸው ይችላል፡፡
በሽታውን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ሄፕታይተስ ኤ እንዳይሰራጭ ለመከላከል የሚከተሉትን መንገዶች መከተል ይመከራል።
- ንጽሕናን በሚገባ መጠበቅ። ወደ መጸዳጃ ቤት ከሄዱ በኋላ ወይም የሕፃን ልጅን ሽንት ጨርቅ ከቀየሩ በኋላ እንዲሁም ቆሻሻ ልብሶችንና ዕቃዎችን ከነኩ በኋላ እጅን በውሃና በሳሙና መታጠብ፡፡ በተመሳሳይ ምግብ ከማዘጋጀት እና ከመመገብ በፊት እጅን በውኃና በሳሙና መታጠብ አስፈላጊ ነው፡፡
- ምግብን በሚገባ ማብሰል፤ ፍራፍሬዎችን እና አትክልቶችን ደግሞ ከመመገብ በፊት በደንብ ማጠብ፡፡
- ክትባቱን መውሰድ። ክትባቶች በሽታውን ለመከላከል ውጤታማ አማራጮች ናቸው። የ ሄፕታይተስ ኤ ክትባት በ 2 ተከፍሎ የሚሰጥ ሲሆን ከአንድ ዓመት ጀምሮ ማንኛውም ሰው መከተብ ይችላል። በተለይ በበሽታው የመያዝ ዕድላቸው ከተለመደው ከፍ ያለ ሰዎች ክትባቱን እንዲያገኙ ይመከራል፡፡ ለምሳሌ በከፍተኛ ሁኔታ የበሽታው ስርጭት ወደአለባቸው ሀገራት ለመሄድ ያቀዱ ሰዎች፤ እንዲሁም ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ክትባቱን እንዲወስዱ ይመከራል። በክትባት መልክ የሚሰጠው የሞተ ቫይረስ ስለሆነ በሽታ የመከላከል ዐቅማቸው ያነሰ ሰዎች ላይ እንኳን በሽታ አያስከትልም።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የውስጥ ደሜ ሐኪሞችን ማማከር ከፈለጉ የ wecare ET መተግበሪያን መጠቀም ይችላሉ። መተግበሪያውን ለመጫን ቀጣዩን ሊንክ ይጠቀሙ። https://play.google.com/store/apps/details?id=com.icare.patient ለተጨማሪ መረጃ 9394 ይደውሉልን።