የጆሮ መካከለኛ ክፍል ኢንፌክሽን (Acute otitis media)
- March 3, 2022
- የጤና እክሎች
የጆሮ መካከለኛ ክፍል ኢንፌክሽን (Acute otitis media) አብዛኛውን ጊዜ በልጆች ላይ የሚከሠት ሲሆን፤ የጆሮ ሕመም፣ ትኩሳት እና የመስማት ችግርን ሊያስከትል ይችላል።
የሕመሙ መነሻ ምክንያት ብዙ ጊዜ ልጆች በጉንፋን ከተያዙ በኋላ በአፍንጫ እና በጉሮሮ ውስጥ በሚገኙት ቫይረሶች እና ባክቴሪያዎች አማካኝነት ነው። አብዛኛውን ጊዜ በሽታው ከ3 - 18 ወር ባሉት ሕፃናት ላይ ይከሠታል፡፡ 50 በ መቶ የሚሆኑት ሕፃናት አንድ ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ቢያንስ አንድ ጊዜ በዚህ በሽታ ይጠቃሉ።
አጋላጭ ሁኔታዎች ምንድናቸው?
- ሕፃናት፣ በተለይም ጊዜአቸው ሳይደርስ የተወለዱ ወይም የክብደታቸው መጠን ትንሽ ሆነው የተወለዱ ሕፃናት
- የአለርጂ ችግር፣ በቤተሰብ ውስጥ ተመሳሳይ ሕመም ከአለ
- የሰውነት በሽታን የመከላከል ሥርዓት ላይ ችግር ከአለ እና
- ሌሎች ተጓዳኝ የጤና ችግሮች እንደአጋላጭ ሁኔታ መወሰድ ይችላሉ።
የጆሮ በሽታ ምልክቶች ምንድ ናቸው?
-
በሕፃናት ላይ የሚከተሉት ምልክቶች ይታያሉ።
- ትኩሳት
- ጆሮን መነካካት ወይም መጎተት
- ከጆሮ የሚወጣ መግል የመሰለ ፈሳሽ
- ከወትሮው የበለጠ መነጫነጭ ወይም
- እንቅልፍ አለመተኛት
- የምግብ ፍላጎት አለመኖር
- ማስመለስ ወይም ተቅማጥ
* ተለቅ ባሉ ልጆች ላይ ምልክቶቹ ብዙውን ጊዜ የጆሮ ሕመም ወይም ጊዜያዊ የመስማት ችሎታ መቀነስ ነው።
ልጅዎ የሚከተሉት ምልክቶች ከታዩበት በአፋጣኝ የሕክምና ርዳታ ማግኘት አለበት።
- ከባድ ትኩሳት፣ 39 °ሴ ወይም ከዚያ በላይ የሆነ የሰውነት ሙቀት
- ከጆሮ የሚወጣ መግል የመሰለ ፈሳሽ ከአለ
- ምልክቶቹ እየባሱ ከመጡ እና
- የመስማት ችግር ከአለ ልጅዎ በአፋጣኝ የሕክምና ርዳታ ማግኘት አለበት።
ምርመራው ምንድነው?
የጆሮን የውስጥ ክፍል መመልከቻ መሣሪያን (Otoscope) በመጠቀም የጆሮ ታምቡርን (Tympanic membrane) ጥሩ እይታ ማግኘት ይቻላል።
የጤና ባለሙያዎችም በዚህ መሣሪያ በመጠቀም የጆሮን የውስጥ ክፍል መመልከት እና የጆሮ ኢንፌክሽን እንዳለ ማወቅ ይችላሉ።
የጆሮ መካከለኛ ክፍል ኢንፌክሽን ሕክምና
የጆሮ ኢንፌክሽን ሕክምና የሚከተሉትን ሊያካትት ይችላል፡፡
1. በቤት ውስጥ የሚደረግ እንክብካቤ
- ዕረፍት ማድረግ፣ ተጨማሪ ውሃ ወይም ሌሎች ፈሳሾችን መውሰድ፣ ሕመምን እና ትኩሳትን የሚያስታግሱ መድኃኒቶችን (Paracetamol, Ibuprofen) መጠቀም ናቸው።
-
አንዳንድ ጊዜ መድኃኒቶች ቶሎ ላያስፈልጉ እና በቤት ውስጥ እንክብካቤ ብቻ ሕክምናው ሊቀጥል ይችላል። ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ጊዜ የጆሮ ኢንፌክሽን የሚከሠተው በቫይረሶች እንጂ በባክቴሪያዎች ስላልሆነ ነው።
2. አንቲባዮቲክስ (ፀረ ባክቴሪያ)
- እነዚህ በጣም አስፈላጊ መድኃኒቶች ቢሆኑም ቫይረሶችንን ግን አያጠፉም። ስለዚህ በአጠቃላይ ዕድሜው ከ 24 ወር በላይ ለሆነ ሕፃን፣ ከባድ የሆነ የጆሮ ሕመም እና ትኩሳት ከሌለበት እና ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች ከሌሉ አንቲባዮቲክስ (ፀረ ባክቴሪያ) ላይታዘዝ ይችላል።
3. ሕመምን እና ትኩሳትን የሚያስታግሱ መድኃኒቶች (Paracetamol, Ibuprofen)
4. ቀዶ ጥገና
-
አንዳንድ ጊዜ የጆሮ ኢንፌክሽን ከዳነ በኋላ በጆሮ መካከለኛ ክፍል ውስጥ ፈሳሽ ሊከማች ይችላል፡፡
-
ይህ ፈሳሽ ሊበከል ወይም የጆሮ ታምቡርን በመጫን መለስተኛ እና ጊዜያዊ የመስማት ችግርን ሊያመጣ ይችላል።
-
የመስማት ችግሩም ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ከሆነ በቀዶ ጥገና ሕክምና ፈሳሹ እንዲወገድ ይደረጋል። ይህ ካልሆነ ግን በቋንቋ እና በንግግር ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል።
በአግባቡ ያልታከመ የጆሮ ኢንፌክሽን ምን ያስከትላል?
- የጆሮ ታምቡር መበሳት
- የመስማት ችግር
- በጆሮ አካባቢ ያሉ አጥንቶች ኢንፌክሽን (Mastoiditis)
- ያልተለመደ ቢሆንም የፊት ነርቭ ችግር (Facial palsy) የጭንቅላት ውስጥ ኢንፌክሽን፣ ማጅራት ገትር
የጆሮ መካከለኛ ክፍል ኢንፌክሽንን ለመከላከል ምን ማድረግ አለብን?
-
ልጅዎን ክትባት በወቅቱና በአግባቡ ማስከተብ
-
የግል እና የአካባቢን ንጽሕና መጠበቅ
-
ልጅዎ 6 ወር እስኪሞላው ድረስ የእናት ጡት ብቻ ማጥባት እና ቢያንስ 24 ወራት እስኪሆነው ድረስ ጡት መጥባቱን መቀጠል አለበት።
-
ሲጋራን አለማጨስ እና ለጭሱም አለመጋለጥ
-
ከውሃ ዋና በኋላ ጆሮዎን በደንብ ማድረቅ ናቸው ፡፡