Learning materials for your health  Learn

መካንነት በሴቶች ላይ

  • March 21, 2022
  • የጤና እክሎች

 

  • መካንነት ከሕክምና አንፃር እንዴት ይገለፃል?

  •  መካንነት፤ ጥንዶች ያለምንም ተአቅቦ ወይም የወሊድ መከላከያ ቢያንስ ለ1 ዓመት ሩካቤ ከፈጸሙ በኋላ፣ መፀነስ አልቻሉም ማለት ነው። ከ 35 - 40 ዓመት በላይ ያሉ ሴቶች ላይ ግን ለ 6 ወር ማርገዝ ከአልቻሉ መካንነት እንለዋለን። በዓለማችን ላይ በግምት ከ 10 - 15 በመቶ የሚሆኑ ጥንዶች ለዚህ ችግር ተጋላጭ ናቸው።

  • አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የመካንነት ችግር በሴቶች ምክንያት፣ እንዲሁም አንድ ሦስተኛ የሚሆነው በወንዶች ምክንያት ይከሠታል፡፡ ቀሪው ደግሞ በሁለቱም ፆታዎች ችግር ወይም መንሥኤው የማይታወቅ ሊሆን ይችላል።

  •  

    በሴቶች ላይ ለመካንነት የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

  •    ዕድሜ

  • የሴቷ ዕድሜ እየጨመረ ሲሔድ (በተለይም ሠላሳዎቹ አጋማሽ ስትደርስ)፣ የሴቷ ዕንቁላል በመጠን እና በጥራት እየቀነሰ ይሔዳል፡፡ ይህም መፀነስ ከባድ እንዲሆን ወይም ፅንስ እንዲጨነግፍ ሊያደርግ ይችላል።

  • ሲጋራ ማጨስ

    • የማኅፀን ጫፍ እና ቱቦ እንዲጎዱ ያደርጋል።

    • ውርጃ እና ከማኅፀን ውጪ ፅንስ እንዲፈጠር ያደርጋል።

    • እንቁልጢ (Ovary) አለጊዜው ሥራ እንዲያቆም ያደርጋል፡፡

  •   ጤናማ የአልሆነ ክብደት

  • ከጤናማ በላይ ወይም በታች የሆነ የሰውነት ክብደት የሆርሞን መዛባት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህም በሴቷ ዘር ፍሬ ላይ እክል ሊፈጥር ይችላል።

  •    የማኅፀን የውስጥ ሽፋን ወይም ቱቦ የሚጎዱ በሽታዎች

    • የአባላዘር በሽታ

  • በሩካቤ የሚተላለፉ እንደ ጨብጥ እና ክላሚዲያ ዓይነት ኢንፌክሽኖች፣ የማኅፀን ቱቦ እንዲጎዱ በማድረግ መፀነስን ከባድ ሊያደርጉት ይችላሉ።  

  • የማኅፀን ጠባሳ

  • ኢንዶሜትሮሲስ (Endometriosis)

  •     የአልኮሆል መጠጥ

  • መካንነትን በሴቶች ላይ የሚያመጡ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

    ስለ መካንነት በደንብ ለመረዳት በመጀመሪያ እርግዝና እንዴት እንደሚፈጠር ማወቅ አስፈላጊ ነው። እርግዝና የሚፈጠረው የሴቷ ዕንቁላል ከወንዱ ዘር ፍሬ ሕዋስ ጋር ተዋሕዶ በሴቷ የማኅፀን ግርግዳ ላይ ሲጣበቅ ነው።

    ነገር ግን ሂደቱ ከመፈጸሙ በፊት የሴቷ ዕንቁላል በእንቁልጢ ውስጥ ተመርቶ እና አድጎ በዕንቁላል መተላለፊያ ቧንቧ በማለፍ ወደ ማኅፀን መምጣት ይኖርበታል። ለዚህም የተለያዩ ሆርሞኖች ዓይነተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ።

    ስለዚህ ማንኛውም

  •  በሆርሞኖች መመረትን

  •  በዕንቁላል የማምረት ሂደትን

  • ዕንቁላሉ ወደ ማኅፀን የመውጣት ሂደትን እንዲሁም

  • ዕንቁላሉ ከወንድ ዘር ጋር ከተዋሐደ በኋላ በማኅፀን ግርግዳ ጋር እንዳይጣበቅ የሚያስተጓጉል ነገር በሴቶች ላይ መካንነት ሊያስከትል ይችላል። ይህን ስንል ግን አልፎ አልፎ ያለምንም ምክንያት መካንነት ሊከሠት እንደሚችል ማሰብ ያስፈልጋል።  እስኪ እያንዳንዱን በዝርዝር እንያቸው።

  •  

  • ዕንቁላል የመመረቱን ሂደት የሚያስተጓጉሉ በሽታዎች
  • 25% የሚሆኑ ሴቶች ላይ መካንነት የሚከሠተው የሴቷ ዕንቁላል በመደበኛነት ከአለመመረቱ የተነሣ ነው። የተለያዩ በሽታዎች ይህን ችግር ሊያመጡ ይችላሉ። ለምሳሌ

  •  ፖሊሲስቲክ ኦቫሪያን ሲንድረም (Polycystic ovary syndrome) - ይህ በሽታ በሆርሞን መዛባት አማካኝነት የሚመጣ ነው፡፡ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሴቶች የሚያሳዩት ምልክቶች፤

    • ከመደበኛ የአጠረ ወይም የአነሰ የወር አበባ ወይም ሙሉ በሙሉ የወር አበባ አለማየት፡፡

    • ፊት እና ደረትን ጨምሮ በሰውነት ላይ የሚወጣ ፀጉር፡፡

    • ከመጠን በላይ ክብደት መጨመር፡፡

    • ለድባቴ፣ ጭንቀት እና ለስኳር በሽታ የተጋለጡ ናቸው።

  •  

  • የሆርሞኖች መዛባት

  • የተለያዩ የሆርሞን ዓይነቶች ሲዛቡ ዕንቁላል በየወሩ እንዳይመረት ምክንያት ይሆናሉ። ከፍተኛ ጭንቀት፣ ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ ከመጠን ያለፈ ወይም ከመጠን ያነሰ የሰውነት ክብደት የመሳሰሉት ነገሮች ለእነዚህ ሆርሞኖች መዛባት እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ።

    በተጨማሪም እንደ ፕሮላክቲን ያሉ ሆርሞኖች ከተዛቡም ተመሳሳይ ችግር ሊፈጠር ይችላል።

  • ከማረጫ ዕድሜ ቀድሞ የዕንቁላል መመረት ማቆም

  • ይህ በሽታ በሕክምናው አጠራር ፕሪማቹር ኦቫሪያን ፌይለር (Premature ovarian failure) ይባላል። ይህም በተለያየ ምክንያት እንቁልጢ ዕንቁላል አያመርትም። ይህም የማረጥ ዕድሜ ሳይደርስ (40 ዓመት በፊት) ዕንቁላል የማምረት ሥርዐት ስለሚቆም መካንነት እንዲከሠት ምክንያት ይሆናል።

    2.  የዕንቁላሉን ወደ ማኅፀን የመውጣት ሂደት የሚያስተጓጉሉ በሽታዎች

    ማንኛውም የዕንቁላል መተላለፊያ ቱቦ የሚዘጉ በሽታዎች መካንነትን ሊያመጡ ይችላሉ። ለምሳሌ

  • የዕንቁላል መተላለፊያ ቧንቧን የሚጎዱ የአባላዘር በሽታዎች፤

  • እንደ ጨብጥ እና ክላሚዲያ ያሉ ማኅፀንን እና የዕንቁላል መተላለፊያ ቱቦን የሚጎዱ በሽታዎች በጊዜ ሂደት ጠባሳን ይፈጥራሉ፡፡ በዚህ የተነሣ ዕንቁላል ከተመረተ እና ከዳበረ በኋላ ወደ ማኅፀን በመውጣት ከወንድ የዘር ፍሬ ጋር እንዳይገናኝ ስለሚያደርጉ መካንነት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናሉ።

  • የታችኛው የሆድ ክፍል እና ማኅፀን አካባቢ የሚደረጉ ቀዶ ጥገናዎች ወይም ከዚህ በፊት ከማኅፀን ውጪ ለተፈጠረ እርግዝና የተደረገ ቀዶ ጥገና ጠባሳን ይፈጥራሉ፡፡ ከዚያም መተላለፊያ ቱቦውን በመጉዳት እርግዝና እንዳይፈጠር ያግዳሉ።

  • በተጨማሪም እንደ ቲቢ ያሉ በሽታዎች ቱቦውን ሊጎዱ እና ጠባሳን ሊፈጥሩ ይችላሉ።

  •  

    3.  ዕንቁላሉ ከወንድ ዘር ጋር ከተዋሐደ በኋላ በማኅፀን ግርግዳ ላይ እንዳይጣበቅ የሚያስተጓጉሉ ችግሮች

    ማንኛውም የማኅፀን ግርግዳ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች መካንነትን ሊያስከትሉ ይችላሉ። ለምሳሌ

  •  የማኅፀን ዕጢ

  • የማኅፀን ዕጢ ዕንቁላል ከዕንቁላል ማስተላለፊያ ቱቦ እንዳይወጣ፤ ከወጣ እና ከወንድ ዘር ጋር ከተዋሐደም በኋላ የማኅፀን ግርግዳ ላይ ተጣብቆ እንዳያድግ ሊያግዱ ይችላሉ። ይህም እርግዝና እንዳይፈጠር ያረጋል።

  • በማኅፀን ግርግዳ ላይ የሚደርሱ እና ጠባሳ ሊያስከትሉ የሚችሉ ማንኛውም ጉዳቶች፤ ለምሳሌ የተለያዩ የአባለዘር በሽታዎች እንዲሁም የቲቢ በሽታ  

  • አብሮ የሚወለድ የማኅፀን አፈጣጠር እክል

  • የማኅፀን በር ከተገቢው በላይ የመጥበብ ችግር፤ (ይህም በማኅፀን አፍ ላይ የሚደርስ አደጋን ተከትሎ የሚመጣ ወይም አብሮ የሚወለድ እክል ሊሆን ይችላል)።

  • ምርመራው ምንድነው?

  •  የሴቷ ዘር ፍሬ ምርመራ (የዕንቁላል መመረት ሒደት ምርመራ)

  • የደም ምርመራ

  •  የማኅፀን ራጅ ምርመራ (Hysterosalpingography)

  • የማኅፀን ውስጣዊ ክፍልን ለመመልከት የሚያገለግል የምስል ምርመራ ነው። በተጨማሪም አንዳንድ ጊዜ የተዘጋ የማኅፀን ቱቦ ለመክፈት ያገለግላል።

  • የእንቁልዕጢ ምርመራ

  • ይህ የደም እና የምስል ምርመራ ሲሆን በእንቁልዕጢ ውስጥ የአለውን (የቀረውን) የሴቷን የዘር ፍሬ ለማወቅ የሚደረግ ምርመራ ነው።    

  •  ሌሎች የሆርሞን ምርመራዎች (Thyroid and pituitary hormone)

  •    የምስል ምርመራ

  • የማኅፀን አልትራሳውንድ

  •   እንደአስፈላጊነቱ የሚከተሉት ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ፡፡

  • ሂስቴሮስኮፒ (Hysteroscopy)

  • ላፓራስኮፒ (Laparoscopy) እና

  • የዘረ መል ምርመራ ናቸው።

  • በሴቶች ላይ ለሚከሠት መካንነት ምን ዓይነት የሕክምና አማራጮች አሉ?

    የመካንነት ሕክምና በመንሥኤው፣ በዕድሜ፣ የመካንነት ቆይታው ለምን ያህል ጊዜ  እንደሆነ እና የግል ምርጫ ላይ ይወሰናል፡፡ መካንነት የተወሳሰበ እክል ስለሆነ ሕክምናው ከፍተኛ የኢኮኖሚ፣ የአካል፣ የሥነ ልቦና እና የጊዜ ተግዳሮቶች ይኖሩታል፡፡

  • የመራባት ዐቅምን የሚጨምሩ መድኃኒቶች

  • እነዚህ መድኃኒቶች በተፈጥሮ የሚገኙ ሆርሞኖችን ሥራ በመምሰል የዕንቁላል ማምረት ሒደትን ለማነቃቃት ይረዳሉ። ይህ ዓይነቱ ሕክምና በዕንቁላል ምርት እክሎች ምክንያት መካን ለሆኑ ሴቶች ተመራጭ ነው።

  • ክሎሚፌን ሲትሬት Clomiphene citrate and letrozole የክሎሚፌን ሲትሬት በአፍ የሚወሰድ ክኒን ሲሆን በጭንቅላት ውስጥ ከሚገኘውን ፒቱታሪ ዕጢ ተፈጥሮአዊ ሆርሞኖች እንዲለቀቅ በማድረግ የዕንቁላል ምርት ሒደትን ያሻሽላል።  

  • ጎናዶትሮፒን Gonadotropins (Gonal F, Menopur, Merional, Fostimon) ይህ መድኃኒት በቀጥታ እንቁልጢ የበለጠ ዕንቁላል እንዲያመርት የሚያደርግ ሕክምና ነው።  

  • ሜትፎርሚን Metformin ይህ መድኃኒት ጥቅም ላይ የሚውለው ሰውነት ኢንሱሊን መቋቋም ወይም ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲያቆም (insulin resistance) ነው፡፡ ይህም አብዛኛውን ጊዜ PCOS ተብሎ የሚጠራ በሽታ የአለባቸው ሴቶች ላይ ይታያል።  

  • ብሮሞክሪፕቲን Bromocriptine ይህ መድኃኒት በፕሮላክቲን ሆርሞን መብዛት ምክንያት ለሚከሠት መካንነት ጥቅም ላይ ይውላል።   

  • የመራባት ዐቅምን የሚጨምሩ መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳቶች አላቸው?

    እነዚህን መድኃኒቶች መጠቀም የሚከተሉትን የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡

  • መንታ ወይም ከዚያ በላይ እርግዝናዎች፤ በአፍ የሚወሰዱ መድኃኒቶች እስከ 10 በመቶ ያሉ ሴቶች ላይ መንታ እርግዝናን ያስከትላሉ፡፡ በመርፌ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ደግሞ እስከ 30 በመቶ በሚደርሱ ሴቶች ላይ መንታ እና ከዚያ በላይ እርግዝናዎችን ሊያመጡ ይችላሉ፡፡

  • በአጠቃላይ በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ሽል በሚፀንሱበት ወቅት ያለጊዜው መወለድ፣ ዝቅተኛ ክብደት ያለው ፅንስ ወይም የተለያዩ የአስተዳደግ እክሎች የመከሠት ዕድል የሰፋ ነው። 

  • የእንቁልጢ ማበጥ እና መቆጣት (OHSS)፤ የሆድ ሕመም፣ የሆድ መነፋት፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ እና ተቅማጥ የመሳሰሉ ምልክቶች አሉት፡፡ ያለ ምንም ሕክምና በጊዜ ያገግማል፤ ነገር ግን እርግዝና ከተከሠተ የተወሰነ ሳምንታት ሊቆይ ይችላል። አልፎ አልፎ በፍጥነት ክብደት መጨመር፣ ሕመም ያለው የእንቁልጢ ማበጥ፣ በሆድ ዕቃ ሽፋን ውስጥ ውሃ መቋጠር እና ትንፋሽ ማጠርን ያካተተ ከባድ በሽታ ሊያስከትል ይችላል።    

  • የእንቁልጢ ካንሰር፤ ከ12 ወር ወይም ከዚያ በላይ የመራቢያ መድኃኒት ተጠቅመው እርግዝና ያልተሳካላቸው ሴቶች ለእንቁልጢ ካንሰር ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ።  

  • የቀዶ ጥገና ሕክምና

  • የቀዶ ጥገና ሕክምናዎች አካላዊ የሆኑ የመካንነት መንሥኤዎችን ለማስተካከል ይረዳሉ። ለምሳሌ የተዛባ የማኅፀን ቅርፅ፣ የማኅፀን ዕጢ እና የዕንቁላል መተላለፊያ ቱቦ በተለያዩ ምክንያቶች ቢደፈን በቀዶ ጥገና በማስተካከል የእርግዝና ዕድልን ማሻሻል ይቻላል።

  • የሥነ ተዋልዶ ድጋፍ

  • በማኅፀን ውስጥ የማዳቀል ሥራ (Intrauterine insemination) ሴቶች ዕንቁላል በሚያመርቱበት ወቅት ጤናማ የወንድ የዘር ፍሬን በማኅፀን ውስጥ ማስቀመጥን ያካትታል።  

  • በቴክኖሎጂ የታገዘ የመካንነት ሕክምና (Assisted reproductive technology)  ይህ ዕንቁላሎችን እና የወንድ የዘር ፍሬዎችን በላብራቶሪ ውስጥ በማዋሐድ የተፈጠረውን ፅንስ ወደ ማኅፀን ማስተላለፍ የሚያካትት የሕክምና ዓይነት ነው።  

  • በሴቶች ላይ የሚከሠት መካንነትን መከላከያ መንገዶች

  • ጤናማ የሰውነት ክብደት  ከመጠን ያለፈ ወይም ዝቅተኛ ክብደት ያላቸው ሴቶች ለዕንቁላል ማምረት እክሎች ተጋላጭ ናቸው፡፡ ክብደት መቀነስ ከአስፈለገ መጠነኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፡፡ በሳምንት ከአምስት ሰዓታት በላይ ከባድ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ የዕንቁላል ማምረት ሒደትን ያዘገያል፡፡

  • ሲጋራ ማጨስን ፈጽሞ መተው  

  • የአልኮል መጠጦችን ማስወገድ

  • ጭንቀትን መቀነስ

  • የሚወስዱትን የካፊን መጠን መገደብ፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በቀን ከ200 ሚሊግራም ያነሰ የካፊን መጠን የሚወስዱ ሴቶች የመፀነስ ችሎታቸው ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም።

  • የአይረን እና የፎሊክ አሲድ ኪኒኖችን መውሰድ 

Share the post

scroll top