Learning materials for your health  Learn

መካንነት በወንዶች ላይ

  • March 23, 2022
  • የጤና እክሎች

መካንነት የሚባለው ጥንዶች ቢያንስ ለ አንድ ዓመት ያህል ሞክረው (ቢያንስ በሳምንት 3 ጊዜ ያለወሊድ መቆጣጠሪያ) ልጅ መውለድ (ማርገዝ) ከአልቻሉ ነው። ነገር ግን ሴቷ ከ 35 ዓመት በላይ ከሆነች በ6 ወር ብቻ ምርመራ ሊጀመርላት ይችላል።

በተደረገው ጥናት መሠረት 85% የሚሆኑ ጥንዶች በመጀመሪያው 12 ወር ውስጥ ሴቷ ትፀንሳለች። የተቀሩት 10% የሚሆኑት ጥንዶች ደግሞ በቀጣዩ አንድ ዓመት ውስጥ ይሳካላቸዋል።

መካንነት የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ። ከእነዚህ ውስጥ፤ 

  • አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ላይ የሴቷ ችግር፤

  • አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ላይ ደግሞ የወንዱ ችግር ሲሆን፤ 

  • የተቀሩት አንድ ሦስተኞቹ ላይ በሴቷም በወንዱም ላይ ችግር ተገኝቷል።

 

መካንነትን በወንዶች ላይ የሚያመጡ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

የተለያዩ የጤና ችግሮች በወንዶች ላይ መካንነትን ያመጣሉ። እነዚህ የጤና እክሎች እንዴት መካንነት እንደሚያመጡ ለመረዳት በመጀመሪያ ትክክለኛው የዘር ፍሬ እንዴት እንደሚሠራ እና መጠኑን መረዳት ያስፈልጋል።

የወንድ የዘር ፍሬ የሚመረተው የዘር ከረጢት ውስጥ ነው፡፡ ወንዱ ለዐቅመ አዳም ከደረሰ ጊዜ አንሥቶ በየቀኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዘር ፍሬዎች ይመረታሉ። እነዚህ የዘር ፍሬ ሕዋሳት እንዲመረቱ ቴስቴስትሮን (Testosterone) የሚባል ሆርሞን ዋነኛውን ሚና ይጫወታል። እነዚህ የዘር ፍሬ ሕዋሳት ከተመረቱ በኃላ በአምስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ያድጋሉ።  ቀጥሎም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ ሴሚናል ፈሳሽ ከሚባል ጋር በመደባለቅ በሽንት ቧንቧ አማካኝነት ወደ ሴቷ መራቢያ ክፍል ይገባሉ። 

በአማካኝ 

  • በአንድ ግዜ የሚፈስው የዘር ፈሳሽ 1.5 - 5 ሚሊ ሊትር ሲሆን

  • በአንድ ሚሊ ሊትር ውስጥ የሚኖረው የዘር ፍሬ ብዛት ከ15 ሚሊዮን ይበልጣል፡፡ በጠቅላላው ከ39 ሚሊዮን የሚበልጥ የዘር ፍሬ ሕዋሳትን በውስጡ ይይዛል።

  • በመጨረሻም ከቁጥሩ በተጨማሪ የዘር ፍሬ ሕዋሶቹ መጠናቸው እና ቅርፃቸው እንዲሁም የሚንቀሳቀሱበት ፍጥነት አስተዋጽዖ አለው።

ከላይ ከተጠቀሰው ሂደት ውስጥ አንዱ ላይ ችግር ከአለ መካንነት ሊከሠት ይችላል። በዚህ ምክንያት የወንዶች መካንነት በተለያዩ ምክንያቶች ሊመጣ ይችላል ማለት ነው። ከ 30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው የመካንነት ችግር የሚፈጠረው ቆለጥ ላይ በሚደርስ ችግር ነው፡፡ ከ 10 እስከ 20 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከ ዘር ፍሬ ከረጢት ተነሥቶ የሴቷ የመራቢያ አካል እስኪደርስ ባለው መተላለፊያ ቱቦ ላይ በሚደርስ ችግር ምክንያት የሚከሠት ነው። 

ከእነዚህ በሽታዎች ውስጥ ጥቂቶቹ
  • አንድ አንድ ጊዜ የዘር ፍሬ ከረጢትን የሚመግበው የደም መልስ ቧንቧ ሊያብጥ ይችላል። ይህም ቫሪኮሴሌ (varicocele) ይባላል። ይኽንን በሽታ አክሞ ማዳን የሚቻል ቢሆንም የወንዶች መካንነትን ከሚያስከትሉ ምክንያቶች መካከል ዋንኛው ነው። 

  • ከዚህ በተጨማሪም እንደ ጨብጥ ያሉ በልቅ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች የዘር ፍሬ የሚታልፍበትን መንገድ በጠባሳ ሊዘጉ ይችላሉ። አንዳንድ ኢንፌክሽኖች ደግሞ የዘር ፍሬ ሕዋሳት እንዳይመረቱ ሊያደርጉ ይችላሉ።

  • ስንፈተ ወሲብን ጨምሮ የተለያዩ ከግብረ ሥጋ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ለመካንነት ምክንያት ሆነው ይጠቀሳሉ። 

  • ሌላው ምክንያት የዘር ፍሬ ፈሳሽ ወደ ውጭ መውጣቱን ትቶ በተቃራኒው ወደ ሽንት ፊኛ ሲገባ ነው። ይህም ሬትሮግሬድ ኢጃኩሌሽን (retrograde ejaculation) ይባላል። ይህም ሁኔታ በስኳር በሽታ፣ በተለያዩ መድኃኒቶች አማካኝነት፣ ኅብለ ሰረሰር ላይ በሚደርስ አደጋ እንዲሁም በፊኛ ቀዶ ጥገና አማካኝነት ሊፈጠር ይችላል። 

  • አንዲሴንድድ ቴስቲስ (Undescended testicles) በፅንስ ዕድገት ጊዜ የወንድ የዘር ፍሬ ከረጢት ከፅንሱ ሆድ ውስጥ ወጥቶ ወደ ታች ይወርዳል። አንድ አንድ ሕፃናት ላይ ግን ይህ አይፈጠርም። በዚህ ጊዜ የዘር ፍሬን የሚያመነጨው አካል በሆድ ውስጥ ስለሚቀር እና ለከፍተኛ የሰውነት ሙቀት ስለሚጋለጥ የዘር ፍሬ ማምረቱን ይቀንሳል ወይም ያቆማል። ይህም ለመካንነትን የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል። 

  • አነስተኛ የቴስቴስትሮን ሆርሞን መጠን፤

  • መካንነትን የሚያመጡ በዘር የሚወረሱ የተለያዩ የጤና ችግሮች አሉ። ለምሳሌ ክሌንፌልተርስ ሲንድረም (Klinefelter's syndrome) የሚባል በሽታ የወንድ መራቢያ አካል በትክክለኛ መልኩ እንዳይሠራ የሚያደርግ በሽታ ነው።

  • በወንዱ መራቢያ አካል ላይ የሚሠሩ የተለያዩ የቀዶ ጥገና ዓይነቶች ጠባሳን በመፍጠር የዘር ፍሬ ወደ ውጭ እንዳይወጣ ሊያግዱ ይችላሉ።

  • ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ ለተለያዩ ጎጂ ኬሚካሎች፣ ጨረር እና ለከፍተኛ ሙቀት መጋለጥ የዘር ፍሬ ምርትን ሊቀንስ ይችላል።

  • ከዚህ በተጨማሪ አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም፣ አልኮል መጠጥ መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ እንዲሁም ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት የዘር ፍሬን መጠን ሊቀንስ ይችላል። 

ወንዶችን ለመካንነት የሚያጋልጡ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?

  • ሲጋራ ማጨስ

  • አልኮል መጠጥ መጠጣት

  • አደንዛዥ ዕፅ መጠቀም

  • ከመጠን ያለፈ ውፍረት

  • ጭንቀት

  • የአባለዘር በሽታ

  • በዘር ፍሬ ላይ የሚደርስ የኬሚካል፣ የጨረር እና የከፍተኛ ሙቀት አደጋ፤

  • በወንድ የመራቢያ አካል ላይ የሚሠራ የቀዶ ጥገና፤

  • በቤተሰብ ውስጥ ተመሳሳይ ችግር ከአለ ወይም ከነበረ፤

የወንዶች መካንነት እንዴት ይታከማል?

በወንዶች ላይ መካንነትን የሚያስከትሉ ምክንያቶች እንደሚለያዩ ሁሉ ሕክምናውም ይለያያል። ጥንዶች ቢያንስ ለ 12 ወራት ያለ ወሊድ መቆጣጠሪያ በቂ ግብረ ሥጋ ግንኙነት እየፈፀሙ ልጅ ካላገኙ ወደ ሐኪም ቤት በመምጣት የሕክምና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሐኪም ቤት ከመጡ በኋላ ሁለቱም የተለያዩ ምርመራዎች ይደረግላቸዋል። ለወንዱ ከሚደረግለት ምርመራዎች ውስጥ ዋንኛው የዘር ፍሬውን መለካት እና በቂነቱን ማረጋገጥ ሲሆን ይህም ምርመራ ሴመን አናሊሲስ (semen analysis) ይባላል። የተለያዩ ምርመራዎች ከተደረጉ እና ችግሩ ከተለየ በኋላ እንደ ችግሩ የተለያዩ የሕክምና አማራጭች ይቀርባሉ። 

ለምሳሌ

  • የዘር ፍሬ ፈሳሽ እንዳይወጣ የሚያግድ ጠባሳ ካለ በቀዶ ጥገና ማስተካከል ይቻላል። በተመሳሳይ ቫሪኮሴሌ የሚባለው መካንነትን የሚያመጣው የጤና እክልም በቀዶ ጥገና መስተካከል የሚችል ነው።

  • በተጨምሪም የወንዱን የዘር ፍሬ ሕዋስ በማውጣት ላብራቶሪ ውስጥ የሴቷ ዕንቁላል ጋር ይደባልቁታል።

  • የተለያዩ መንገዶች ተሞክረው ልጅ መረገዝ ካልተቻል እንደ ጉዲፈቻ ያሉ አማራጮችን መጠቀም ይቻላል።

 

Share the post

scroll top