Learning materials for your health  Learn

የታይፎይድ በሽታ

 • March 30, 2022
 • የጤና እክሎች

የታይፎይድ በሽታ (Typhoid Fever)

የታይፎይድ በሽታ  ሳልሞኔላ ታይፊ በሚባል የባክቴሪያ ዓይነት የሚመጣ በሽታ ነው፡፡ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች በብዛት የሚያሳዩት ምልክት ትኩሳት ሲሆን፤ ከትኩሳቱ በተጨማሪ ብዙውን ጊዜ የሆድ ሕመም እና ብርድ ብርድ ማለት ሊኖራቸው ይችላል፡፡

ይህ በሽታ እንደ አሜሪካ ባሉ ባደጉ ሃገራት ላይ እንብዛም አይገኝም። ይህ በሽታ አሜሪካ ውስጥ በዓመት ከ 300 ያነሱ ሰዎችን ብቻ ነው የሚያጠቃው። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በጣም የተለመደ በሽታ ነው።

ከ 1 እስከ 5 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በሽታውን እስከ አንድ ዓመት ለሚሆን ጊዜ ምንም ምልክት ሳያሳዩ ያስተላልፋሉ።

የታይፎይድ በሽታ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው እንዴት ነው?

በዋነኝነት ይህ በሽታ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው በንጽሕና ጉድለት ነው። በዚህ ምክንያት ሰዎች የተበከለ ምግብ እና መጠጥ በመመገብ በበሽታው ይያዛሉ።

ተሕዋስያኑ በተለያዩ መንገዶች ወደ ምግቦች እና መጠጦች ሊገቡ ይችላሉ።

 • በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ምግቡን ከመንካታቸው ወይም ከማዘጋጀታቸው በፊት በውኃና በሳሙና እጃቸውን ካልታጠቡ፤

 • በበሽታው የተያዙ ሰዎች የሚጸዳዱበት ቦታ ለአካባቢው ውሃ አቅርቦት ቅርብ ከሆነ እና ውሃው ሳይታከም (ሳይጣራ) ምግብ ለማብሰል ወይም ዕቃ ለማጠብ የምንጠቀምበት ከሆነ ተሕዋስያኑ በቀላሉ ሊሰራጭ ይችላል፡፡

ይህ በሽታ በብዛት ወደሚገኝበት ሀገር ቅድመ ክትባት ሳይወስዱ የሚደረግ ጉዞ ሌላኛው መንገድ ነው። አሜሪካ ውስጥ 80% የሚሆኑት በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ምክንያታቸው ይሄ ነው።

የታይፎይድ በሽታ ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?

ተሕዋስያኑ ወደ ሰውነታችን በገባ ከ 5 እስከ 21 ቀን ባለው ጊዜ ውስጥ ምልክቶችን ማየት እንጀምራለን። ምንም ዓይነት ሕክምና ካላገኘን በ 3 ክፍሎች የሚመደብ ምልክቶች ይኖሩናል። 

 1. በመጀመሪያ ሳምንት እየጨመረ የሚሄድ ትኩሳት ይኖረናል። በተጨማሪም ብርድ ብርድ ማለትና የልብ ምት መቀነስ ሊታይ ይችላል። በዚህ ጊዜ ተሕዋስያኑ በደም ውስጥ ይገኛል። 

 2. ሁለተኛ ሳምንት ላይ የሆድ ቁርጠት፣ ድርቀት (አንድ አንድ ሰዎች ላይ ደግሞ ተቅማጥ) ይኖራል። ከዚህ በተጨማሪም ደረት እና ሆድ ቆዳ ላይ የሚወጣ “ሮዝ ስፖት” የሚባል ቀይ ሽፍታ ሊታይ ይችላል።

 3. ሦስተኛው ሳምንት ላይ የጉበት እና ጣፊያ እብጠት፣ የአንጀት መድማት እና መበሳት እንዲሁም ወደ ሆድ የተሰራጨ ኢንፌክሽን (Peritonitis) ሊከሠት ይችላል። ከዚህም አልፎ በሽታው እየተባባሰ ሲሄድ ወደ ደም መመረዝ (sepsis)፣ ራስን መሳት እና ሞት ሊያስከትል ይችላል። 

በተጨማሪ በሽታው ራስ ምታት፣ የእንቅልፍ መዛባት፣ ሰውነትን ማዘዝ አለመቻል፣ ግራ መጋባት እና ራስን መሳት ሊያስከትል ይችላል።

 

የታይፎይድ በሽታ ምርምራዎች ምን ምንድን ናቸው?

ካልቸር (culture) - ይህ ምርመራ ከደም፣ ከሰገራ ወይም ከሽንት በሚወሰድ ናሙና ይሠራል፡፡ የተወሰደው ናሙና ውስጥ ያሉ ተሕዋስያን በላብራቶሪ ውስጥ እንዲራቡ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር በተወሰኑ ቀናት ውስጥ ባክቴሪያው መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ የሚደረግ ምርመራ ነው።

ዋይዳል (widal) - ይህ ምርመራ ሰውነታችን የታይፎይድ በሽታን ለመከላከል የሚያመነጫቸው አንቲቦዲ የሚባሉ ንጥረ ነገሮችን የሚመረምር ነው፡፡ የአንቲቦዲ መጠኑ ከተወሰነ ደረጃ ሲያልፍ በበሽታው እንደተጠቃን ያመላክታል። በሀገራችን ውስጥ በብዛት የምንጠቀምበት ምርመራ ነው።

ተጨማሪ ምርመራዎች - ለምሳሌ፡- ጉበት መጎዳት አለመጎዳቱን ለማረጋገጥ የሚደረግ ምርመራ፡፡ 

የታይፎይድ በሽታን እንዴት ማከም ይቻላል?

ታይፎይድ ተገቢውን ህክምና ካገኘ በቀላሉ የሚድን በሽታ ነው። በዋነኛነት ሕክምናው እስከ 2 ሳምንታት ድረስ የሚቆይ የፀረ ባክቴሪያ (አንቲባዮቲክ) መድኃኒቶችን መውሰድ ያካትታል ፡፡ እነዚህን መድኃኒቶች በሐኪሙ ትእዛዝ መሠረት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ በሽታው ተመልሶ ሊመጣ ይችላል፡፡

ከበሽታው ጋር ተያይዘው የመጡ ችግሮች ካሉ ተጨማሪ ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል። ለምሳሌ፡- የአንጀት መበሳት ከአጋጠመ የቀዶ ጥገና ሕክምና ሊያስፈልግ ይችላል።

 

የታይፎይድ በሽታን መከላከል ይቻላል?

አዎ ይቻላል። በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ ብዙ መንገዶች አሉ። እነዚህም 

 • ምግብ ከመሥራት (ከማዘጋጀት) ወይም ከመመገብ በፊት እጅን በሳሙና እና በውሃ መታጠብ፡፡

 • በሚገባ የበሰለ እና ትኩስ የሆነ ምግብ መመገብ፡፡

 • አትክልቶችን ወይም ፍራፍሬዎችን በሚገባ ካጠቡ በኋላ መመገብ፡፡

 • የታሸገ ውሃ ወይም ፈልቶ የቀዘቀዘ (የታከመ) ውሃ መጠቀም፡፡

 • የሚኖሩት በአሜሪካ ወይም አውሮፓ ከሆነ ለጉብኝት በሽታው በከፍተኛ ደረጃ የተንሰራፋባቸው አካባቢ ከመሔድዎ በፊት ክትባቱን መውሰድ።

 

Share the post

scroll top