Learning materials for your health  Learn

ውርጃ

  • March 31, 2022
  • የጤና እክሎች

ውርጃ ምንድን ነው?

ውርጃ የሚባለው አንዲት እርጉዝ ሴት እርግዝናዋ 28 ሳምንት ከመሙላቱ በፊት ሲቋረጥ ነው። 

ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በዓለማችን ላይ ከሚፈጠሩ እርግዝናዎች ውስጥ ከ 8 - 20% የሚሆኑት ከ 20 ሳምንታት በፊት ይቋረጣሉ። ከእነዚህ ውስጥ 80% ውርጃ የሚፈጠረው እርግዝናው 12 ሳምንት ከመሆኑ በፊት ነው።

እ.ኤ.አ በ 2008  በኢትዮጵያ ውስጥ 382,500 የሚሆኑት ፅንስ ማስወረድ የተከናወኑ ሲሆን፤ ዕድሜያቸው ከ15 - 44 ከሆነ 1000 ሴቶች ውስጥ 23ቱ አስወርደዋል። 

በከተሞች ውስጥ የሚገኘውን የፅንስ ማስወረድ ስናይ ደግሞ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከ1000 ሴቶች ውስጥ 49ኙ ውርጃ ፈጽመዋል። 

ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ውርጃ የሚባለው ምንድን ነው?

ውርጃ ደኅንነቱ ያልተጠበቀ የሚባለው ከሚከትሉት ውስጥ አንዱን ወይም ሁለቱንም ሲያሟላ ነው።

  1. አስፈላጊው የሕክምና ባለሙያ በአልሆነ ሰው ከተከናወነ ወይም 

  2. የሕክምና ደረጃን በማይመጥን አካባቢ ከተፈፀመ ነው።

በተቃራኒው ደረጃውን በጠበቀ የሕክምና ቦታ እና አስፈላጊውን ሥልጠና እና ክህሎት ባለው የሕክምና ባለሙያ እገዛ ውርጃ ከተከናወነ ድኅንነቱ የተጠበቀ ውርጃ እንለዋለን።

ኢትዮጵያ ውስጥ ውርጃ በሕግ ይፈቀዳል ወይ?

በኢትዮጵያ ውስጥ ውርጃ በሕግ የሚፈቀድባቸው ሁኔታዎች አሉ። እነዚህም፡-

  • እናትዬዋ ለአካለ መጠን ከአልደረሰች (ከ 18 ዓመት በታች) ወይም ደግሞ በአካላዊ ወይም በአእምሮ በሽታ ምክንያት ልጇን ማሳደግ የማትችል ከሆነ፡፡

  •  እርግዝናው የተፈጠረው አስገድዶ በመደፈር ከሆነ  

  • እርግዝናው የእናትዬዋን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ 

  • ፅንሱ ከተወለደ በኋላ በሕይወት መቆየት እንዳይችል የሚያደርግ የጤና እክል ከአለው

  • እርግዝናው የተፈጠረው ከሥጋ ዘመድ ከሆነ

ስለሆነም ነፍሰ ጡር የሆነች ሴት ከላይ ከተዘረዘሩት ሁኔታዎች ውስጥ ቢያንስ አንዱን የምታሟላ ከሆነ በአቅራቢያዋ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ አገልግሎቱን ማግኘት ትችላለች፡፡  

ለውርጃ የሚያጋልጡ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

  • ዕድሜ - በዕድሜ የገፉ ሴቶች ከወጣት ሴቶች ይልቅ ፅንስ የማስወረድ ዕድላቸው ሰፊ ነው ፡፡

  • ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ክስተት ከነበረ

  • ሲጋራ ማጨስ - በቀን ከ 10 በላይ ሲጋራን ማጨስ ፅንስ የማስወረድ ዕድልን ይጨምራል፡፡

  • አልኮሆል መጠጣት - በእርግዝና ወቅት ምንም ዓይነት የአልኮሆል መጠን መውሰድ አይመከርም፡፡ አልኮሆል መጠጥ መጠጣትም የፅንስ መጨንገፍ ዕድልን   ይጨምራል፡፡  

  • ትኩሳት - ትኩሳት 37.8ºC ወይም ከዚያ በላይ ያላቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች ፅንስ የማስወረድ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

  • አደጋ - በማሕፀን ላይ የሚደርስ አደጋ  የፅንስ መጨንገፍ ዕድልን ከፍ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ አንዳንድ እንደ ቅድመ ወሊድ ያሉ ምርመራ (Amniocentesis, Chorionic villi sampling) ዓይነቶችን ያጠቃልላል።

  • ጥናቶች እንደሚያሳዩት ካፌይን (ቡና) መውሰድ  የፅንስ መጨንገፍ አደጋን አይጨምርም፡፡ ይህም በጣም ከፍተኛ ከአልሆነ በስተቀር (ማለትም 1000 ሚግ ወይም 10 ኩባያ ቡና ከ 8 - 10 ሰዓት ውስጥ ከተወሰደ) 

  • ሌሎች - ለተወሰኑ ኢንፌክሽኖች መጋለጥ፣ የጨረር ሕክምናዎች፣ ለአካላዊ እና ለአካባቢያዊ ውጥረት መዳረግ ለፅንስ  መውረድ አስተዋጽዖ ያደርጋሉ። 

ምልክቶቹስ ምንድናቸው?

  • በጣም የተለመዱት ምልክቶቹ በመጀመሪያ የእርግዝና ወቅቶች አካባቢ በማሕፀን በኩል የደም መፍሰስ እና ከእንብርት በታች የሆድ ሕመም መከሠት ናቸው። 

ይሁን እንጂ በጤነኛ እርግዝና ሒደት ላይም የደም መፍሰስ እና ምቾት ማጣት ሊከሠት ይችላል፡፡ ይህም ብዙውን ጊዜ በራሱ የሚስተካከል ሲሆን የጤና ባለሙያን ማማከር ግን አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነው። 

የተለያዩ  የውርጃ  ዓይነቶችን እና ደረጃዎችን ለመግለጽ  የጤና ባለሙያዎች የሚከተሉትን ቃላት ይጠቀማሉ ፡፡ 

  1. አስጊ የፅንስ መጨንገፍ (Threatened abortion) - በእርግዝና መጀመሪያ አካባቢ የደም መፍሰስ ቢኖርም ነገር ግን  እናትዬዋ ሌሎች አስጊ ምልክቶች አይኖሯትም ማለት ነው።  የማሕፀን በር እንደተዘጋ ይቆያል፡፡ የማሕፀን መጠንም ከፅንሱ ዕድገት ጋር ተመጣጣኝ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ፅንሱ በሕይወት አለ ማለት ነው፡፡ ( በልብ ምት ወይም በአልትራሳውንድ ምርመራ ሊታወቅ ይችላል) ፡፡ የብዙ እናቶች ዕጣ ፈንታ የሚሆነውም  የደም መፍሰሱ እየቀነሰ  ይሔድ እና እርግዝናው እስከ መጨረሻው  ሊቀጥል ይችላል፡፡ በአንዳንድ እናቶች ደግሞ  የደም  መፍሰሱ እየከበደ እና የፅንስ መውረድ ሊከሠት ይችላል፡፡

  2. የማይቀር የፅንስ መጨንገፍ (Inevitable abortion) - በዚህ ጊዜ የፅንሱ መውረድ አይቀሬ ነው ማለት ነው፡፡  ስለዚህ የማሕፀን ጫፍ በር ክፍት ይሆናል፡፡ የደም መፍሰስ ከባድ እየሆነ ወይም እየጨመረ ይሔዳል፡፡ የሆድ ቁርጠትና የእንሽርት ውኃ መፍሰስ ይኖራል ማለት ነው።

  3. ያልተሟላ የፅንስ መጨንገፍ (Incomplete abortion) - ቁርጥራጭ  የፅንስ አካል መውጣት እና የደም መፍሰስ  ይኖራል፡፡ ነገር ግን የተወሰነ የፅንስ አካል እና የእንግዴ ልጅ በማሕፀኗ ውስጥ ቀርቷል ማለት ነው፡፡ በዚህ ጊዜም የማሕፀን ጫፍ  ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡ የደም መፍሰስ ከባድ ሊሆን እና ሊቀጥል ይችላል፡፡

  4. ሙሉ የፅንስ መጨንገፍ (Complete abortion) -  ይህም ያለ ሕክምና እርዳታ ሙሉ ለሙሉ ፅንሱ ወርዷል ማለት ነው። ይህ ከ 12  የእርግዝና ሳምንታት በፊት የተለመደ የውርጃ ዓይነት ነው፡፡ ምርመራ በማድረግም  የማሕፀን በር እንደተዘጋ ማወቅ ይቻላል። በተጨማሪም በማሕፀን ውስጥ የእርግዝና ከረጢት ምልክት አይታይም፡፡ ይህንንም  በአልትራሳውንድ ምርመራ  ማረጋገጥ  ይቻላል፡፡

  5. ኢንፌክሽን የፈጠረ  የፅንስ መጨንገፍ (Septic abortion) -  አንዳንድ ሴቶች ፅንስ ከአስወረዳቸው በኋላ  ማሕፀናቸው  ኢንፌክሽን ሊፈጥር ይችላል።  ምልክቶቹም ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት ፣ የሆድ ሕመም፣ በማሕፀን በኩል ደም መፍሰስ እና  ወፍራም ደስ የማይል ሽታ ያለው የማሕፀን ፈሳሽ ናቸው።

ውርጃ መኖሩን ለማወቅ የሚደረጉ ምርመራዎች ምን ምንድን ናቸው?

  • ምልክቶችን በማየት እና አካላዊ ምርመራዎችን በማድረግ እንዲሁም በሕክምና መሣሪያዎች ምርመራ በማድረግ ሊታወቅ ይችላል፡፡  ለምሳሌ  የደም መፍሰስ፣ የማሕፀን በር ክፍት መሆን ወይም የፅንሱን አካል በማሕፀን በር ጫፍ ላይ በማየት ሊሆን ይችላል፡፡

  • አልትራሳውንድ - ይህ ምርመራ መጀመሪያ ላይ ፅንሱ በሕይወት መኖር አለመኖሩን ለማየት ይጠቅማል። ውርጃው ከተፈጸመ በኋላ ደግሞ ፅንሱ ሙሉ በሙሉ መጠረግ አለመጠረጉን ለማየትም  ያገለግላል።

ለውርጃ የሕክምና  አማራጮች ምንድንናቸው?

አብዛኛው ጊዜ ፅንስ መውረድ ከጀመረ ማስቆሚያ የሕክምና መንገድ የለውም፡፡ የፅንሱ መውረድ የማይቀር በሚሆንበት ወይም ሙሉ በሙሉ በአልተጠናቀቀበት ጊዜ የእናትዬዋ ጤና  እና ሌሎች ሁኔታዎች ላይ በመመርኮዝ የተለያዩ የሕክምና አማራጮች አሉ፡፡ 

ሦስቱ ዋና ዋና አማራጮች - ቅርብ ክትትል፣ መድኃኒት ወይም የማሕጸን መጥረግ ሕክምና ናቸው፡፡

  • የቅርብ ክትትል - ሙሉ በሙሉ ፅንሱ የወረደባቸው ሴቶች ላይ እና በሙሉ ጤንነት ላይ ያሉ ከ13ኛው የእርግዝና  ሳምንት በፊት ውርጃ የአጋጠማቸው ሴቶች በጤና ባለሙያ የቅርብ ክትትል ማድረግ ብቻውን በቂ ነው። 

ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት ባለው ጊዜ ወስጥ የማሕፀኑ ይዘቶች በራሳችው ይወጣሉ፡፡ ይህም ከሆነ በኋላ ቀሪ የሽል አካል አለመኖሩን ለማረጋገጥ የአልትራሳውንድ ምርመራ ይደረጋል፡፡

  • የመድኃኒት ሕክምና - በአንዳንድ  ሁኔታዎች ሽሉ በሙሉ እንዲወጣ  ማሕፀንን ለማነቃቃት መድኃኒቶች ይሰጣሉ፡፡ መድኃኒቱ በአፍ ወይም በሴት ብልት ሊሰጥ ይችላል፡፡ 

  • የማሕፀን መጥረግ ሕክምና - ለፅንስ መውረድ ከተለመደው ሕክምና አንዱ (manual vaccum aspiration) ቀጭን ቱቦ በመጠቀም የማሕፀኑን ይዘት ስቦ የሚያወጣ መሣሪያ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ (dilation and curettage) የማሕፀንን በር በማስፋት የሚስብ  እና  ረጋ ያለ የመቧጠጥ እንቅስቃሴ ያለው መሣሪያ በመጠቀም የማሕፀኑን ይዘቶች ለማስወገድ የሚጠቀም ሕክምና ነው፡፡ 

ይህ ዓይነቱ ሕክምና  ከባድ የደም መፍሰስ ወይም ኢንፌክሽን ለአለባቸው ሴቶች ይመከራል፡፡

ከውርጃ በኋላ መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች፤

  • ውርጃን ተከትሎ ለሚመጡት ሁለት ሳምንታት ሴቶች ከወሲባዊ ግንኙነት እንዲታቀቡ ወይም በብልት ውስጥ ማንኛውንም የንጽሕና መጠበቂያ ቁስ እንዳይከቱ ይመከራሉ።

  • ያልታቀደ እርግዝናን ለመከላከል የወሊድ መቆጣጠሪያ ወዲያውኑ መጀመር ያስፈልጋል፡፡ በማሕፀን ወስጥ የሚቀመጥ የወሊድ መቆጣጠሪያን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት ሊጀመር ይችላል።  

  • የማሕፀን መጥረግ ሕክምና ከተካኼዳ በኋላ ኢንፌክሽንን ለመከላከል የሚሰጠውን መድኃኒት በአግባቡ መውሰድ ያስፈልጋል።

  • ከውርጃ በኋላ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ከባድ የደም መፍሰስ፣ ጠንካራ የሆድ ሕመም ካለ ወደ ጤና ተቋም መሄድ።

  • እንደገና ለማርገዝ ከመሞከር በፊት  በተለምዶ ከ 2 እስከ 3 ወር መጠበቅ እንደሚገባ  ቢነገረም፤ ከዚያ በአነሰ ጊዜ ማርገዝ የተለየ አደጋ እንደሌለው ጥናቶች ያሳያሉ። ይሁንና እርግዝናው የተፈለገ እና የታቀደ መሆን አለበት፡፡

  • የደም ዓይነት Rh ኔጌቲቭ (Rh negative) ከሆነ አንታይ ዲ (anti-D) የተባለ ለቀጣይ እርግዝና ሾተላይ እንዳይከሠት የሚከላከል መድኃኒት መሰጠቱን ማረጋገጥ።

  • ሥነ ልቦናዊ  ጤንነት - የእርግዝና መጨናገፍ ከፍተኛ ሐዘን ያስከትላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህ ስሜት ጠንካራ እና ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል። አንዲት ሴት በእርግዝና ማጣት ምክንያት የሚሰማት ጥልቅ ሐዘን እና ድብርት  ለበርካታ ሳምንታት የሚቀጥል ከሆነ የሥነ ልቦና አማካሪ ማነጋገር ይመከራል።

የፅንስ መጨናገፍን መከላከል ይቻላል?

ብዙውን ጊዜ የፅንስ መጨናገፍን መከላከል ባይቻልም ጤናማ እርግዝና የመሆን ዕድሉን  ለመጨመር ጥንቃቄ ማድረግ ። ይህም የሚከተሉትን ያካትታል።

•  ፎሊክ አሲድ እና ካልሲየም ያለው ምግብ መመገብ (ፍራፍሬዎች፣ ዓሣ፣ የተጣራ ወተት የመሳሰሉት)

•  የቅድመ ወሊድ ቫይታሚኖችን መውሰድ

•  ሐኪም በሚፈቅደው ልክ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ 

•  ጤናማ ክብደት እንዲኖር ማድረግ 

•  አደንዛዥ ዕፅ፣ አልኮል እና ሲጋራ ማስወገድ

•  ያልተጣራ የወተት ተዎጽዖ፣ ጥሬ ሥጋ አለመመገብ

•  የሚወስዱትን የካፌን መጠን መገደብ

•  ከዚህ በፊት የሚወስዷቸው መድኃኒቶች ከአሉ ከሐኪም ጋር መነጋገር

•  የቅድመ ወሊድ ቀጠሮዎች እንዳያመልጡ በሚገባ መከታተል፤ ከሐኪም ጋር በማንኛውም የሚያሰጋ ወይም የሚያሳስብ ጉዳይ ላይ መወያየት

•  ትኩሳት፣ የሆድ ሕመም፣ የፅንሱ እንቅስቃሴ መቀንስ ወይም የደም መፍሰስ  ከአጋጠመ  ወዲያውኑ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይገባል፡፡

በቀጣይ እርግዝና ወቅት 

•  የቅድመ ወሊድ ክትትልን በአግባቡ ማድረግ 

•  ስለ እርግዝና የሕክምና ገጽታዎች የበለጠ ለማወቅ  ሐኪምን  ማማከር 

•  የፅንሱን እንቅስቃሴ መከታተል - ከ 18 እስከ 22 የእርግዝና ሳምንታት ጀምሮ ፅንሱ መንፈራገጥ ይጀምራል፡፡ በየቀኑ ጠዋት እና ማታ የሕፃኑን እንቅስቃሴዎች መዝግቦ መያዝ፡፡  በ 2 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 10 እንቅስቃሴዎች ሊሰማ ይገባል። የፅንሱ እንቅስቃሴ እየተሰማ  ከአልሆነ ጣፋጭ ነገር ወስዶ በጎን ጋደም በማለት ለመከታተል መሞከር። የፅንሱ እንቅስቃሴ ከቀነሰ ወይም ከጠፋ ወደ ጤና ተቋም መሄድ፡፡

•  ሁለቱ እርግዝናዎች ተመሳሳይ መሆን ስለማይችሉ፤ በዚህ እርግዝና እና በተጨናገፈው እርግዝና መካከል የአሉትን ሁኔታዎች ለማወዳደር መሞከር። ቀና የሥነ ልቦና አተያይ እንዲኖር ጥረት ማድረግ፡፡



 

Share the post

scroll top