Learning materials for your health  Learn

የፕሮስቴት ዕጢ መተለቅ

  • April 1, 2022
  • የጤና እክሎች

የፕሮስቴት ዕጢ መተለቅ (BPH)

  • ፕሮስቴት በወንዶች ላይ ብቻ የሚገኝ አነስተኛ መጠን ያለው ዕጢ ነው፡፡ ከሽንት ፊኛ በታች፣ ከፊንጢጣ ፊት ለፊት የሽንት ቧንቧን እንደ ቀለበት አቅፎ የሚገኝ ዕጢ ነው። የፕሮስቴት ዕጢ የዘር ፍሬን (Sperm cell) የሚመግብ እና የሚያጓጉዝ የዘር ፈሳሽ ያመነጫል።  

j1L3eq_I338tBe-OnCqhl_IrrqmxgONqfDlMZ21sY9hTAAPbFoz4bpnbIBkZnu9TEZQOb9LIjdBRiqajG2ZYKPMxPTEsEsUwywONIG2-eQXCcw3yQNnME7avsOwbvO8UUBHbCqGM

የፕሮስቴት ዕጢ መተለቅ ምንድነው?

  • የፕሮስቴት ዕጢ መተለቅ ወይም ማደግ የፕሮስቴት ዕጢ ሕዋሳት ሲባዙ ወይም በመጠን ሲያድጉ የሚከሠት ሲሆን፤ የሽንት መተላለፊያ ቱቦን በመዝጋት የተለያዩ የጤና ችግሮችን ሊያስከትል የሚችል ሕመም ነው። 

  • ይህ ሕመም 8 በመቶ የሚሆኑት ከ 31 እስከ 40 ዓመት ዕድሜ የአሉትን እና 80 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ 80 ዓመት በላይ በሆኑ ወንዶች ላይ ይከሠታል፡፡

አጋላጭ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

  • የዕድሜ መግፋት፤ በተለይም ከ60 ዓመት በላይ

  • በቤተሰብ ውስጥ ተመሳሳይ ሕመም መኖር

  • የስኳር ሕመም ወይም የልብ ችግር ከአለ

  • ከመጠን የአለፈ ውፍረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ

  • ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሕመም መኖር

ምልክቶቹ ምንድናቸው?

  • አንዳንድ ጊዜ የፕሮስቴት ዕጢ መተለቅ ምንም ዓይነት ምልክቶችን ላያሳይ ይችላል፡፡ ምልክቶቹ ከሰው ሰው የሚለያዩ ሲሆን፤ ከጊዜ ብዛት እየተባባሱ ሊሄዱ ይችላሉ። እነዚህም

  • ቶሎ ቶሎ ለመሽናት መፈለግ ወይም የሚያጣድፍ የመሽናት ፍላጎት መኖር፤

  • ምሽት ላይ ሽንት ቶሎ ቶሎ መምጣት (nocturia)፤

  • መሽናት ለመጀመር መቸገር፤

  • የሽንት ፍሰት ኃይል መቀነስ ወይም ሽንት ማቆራረጥ፤

  • ሽንት ሸንተው ከጨረሱ በኋላ መጨረሻ ላይ ማንጠባጠብ እና

  • በሚሸኑበት ጊዜ ማማጥ ወይም የሚቀር ሽንት እንዳለ መሰማት ናቸው።

  • የሚከተሉት አንዳንድ ጊዜ ሊከሠቱ የሚችሉ ምልክቶች ናቸው።

  • የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን

  • መሽናት አለመቻል እና

  • በሽንት ውስጥ ደም መታየት ናቸው።

በአግባቡ የአልታከመ የፕሮስቴት ዕጢ መተለቅ ምን ዓይነት 

ውስብስብ ችግሮች ያስከትላል?

  • ድንገት መሽናት አለመቻል (ሽንት አልወጣም ማለት)፤

  • የሽንት ፊኛ ኢንፌክሽን (UTIs) 

  • የሽንት ፊኛ ጠጠር 

  • የፊኛ መቆጣት እና

  • የኩላሊት ጉዳት ናቸው።

እነዚህ ችግሮች የሚከሠቱት አንዳንዴ ቢሆንም፤  አጣዳፊ ሽንት አልወጣም ማለት እና የኩላሊት ጉዳት ከፍተኛ የሆነ የጤና ስጋት ሊያሳድሩ ይችላሉ ፡፡

የፕሮስቴት ዕጢ መተለቅ የፕሮስቴት ካንሰር የመከሠት ዕድልን አይጨምርም፡፡

ምርመራ

  • የጤና ባለሙያው ስለምልክቶቹ በመጠየቅ እና የተለያዩ አካላዊ ምርመራዎችን በማድረግ ስለሕመሙ ለመረዳት ይሞክራል። 

  • ምርመራዎቹ የሚከተሉትን ያካትታሉ።

  •  በእጅ ጣት የሚደረግ የፊንጢጣ ምርመራ፤

  • የሽንት ምርመራ

  • የደም ምርመራ፤ ይህ የፕሮስቴት ፕሮቲን (PSA) ምርመራን ያጠቃልላል።

  • የሆድ ወይም በፊንጢጣ በኩል የሚደረግ የአልትራሳውንድ ምስል ምርመራ፤

  • የፕሮስቴት ናሙና ምርመራ

  • ሲስቶስኮፒ(Cystoscopy)፤ ይህ መሣሪያ በሽንት ቱቦ ውስጥ በመግባት በፊኛ እና በአካባቢው የአሉትን ነገሮች ለማየት ይጠቅማል።

  • የሽንት ፍሰት ግፊት መለኪያ፤

ሕክምና

  • የፕሮስቴት ዕጢ መተለቅን ለማከም የሚያገለግሉ የተለያዩ የሕክምና አማራጮች አሉ።

  •  የጤና ባለሙያው ትክክለኛ የሆነውን የሕክምና አማራጭ ለመጠቀም የተለያዩ  ሁኔታዎችን ያጤናል። ይህም የፕሮስቴት ዕጢ መጠን፣ ዕድሜ፣ የታማሚው ጤና ሁኔታ እና በአኗኗር ዘይቤ ላይ ስለአመጣው ተጽዕኖ ናቸው። 

መድኃኒቶች

  • እነዚህ መለስተኛ እና መካከለኛ ክብደት ለሆኑ ምልክቶች የሚሰጡ መድኃኒቶች ናቸው። እነዚህም፤

 አልፋ - ብሎከርስ (alfuzosin, doxazosin, tamsulosin) 

  • የፕሮስቴት ዕጢ እና የሽንት ፊኛ አንገት አካባቢ የሚገኙትን ጡንቻዎች ዘና እንዲሉ ያደርጋሉ፤ ይህም ሽንት በቀላሉ እንዲያልፍ ያደርገዋል።

  • የጎንዮሽ ጉዳት፤ የማዞር ስሜት እና የዘር ፍሬ ከወንድ ብልት ወደ ሽንት ፊኛ መመለስ ናቸው።

5 አልፋ ሪዳክቴስ አጋች(Finasteride, dutasteride) 

  • የፕሮስቴት ዕጢ ዕድገት የሚያመጡ ሆርሞኖችን የሚከላከሉ እና ረዘም ላለ ጊዜ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ናቸው።

  • የጎንዮሽ ጉዳት፤ የወንድ ዘር ፈሳሽ ወደኋላ መፍሰስ

አንዳንድ ጊዜ ከላይ የተጠቀሱት መድኃኒቶች አንድ ላይ በጥምረት ሊሰጡ ይችላሉ።

ታዳላፊል (Tadalafil) 

  • ስንፈተ ወሲብን ለማከም የሚያገለግል መድኃኒት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን የፕሮስቴት ዕጢ መተለቅን ለማከም ይውላል።

በሽንት ቱቦ በኩል በሚገባ መሣሪያ የሚደረግ ሕክምና

  • ይህ ሕክምና መካከለኛ ወይም ከባድ የፕሮስቴት ዕጢ መተለቅ ምልክቶች ለአሉባቸው ታማሚዎች የሚሰጥ ነው። 

  •  ይህ ሕክምና በሽንት ቱቦ ውስጥ በሚገባ መሣሪያ አማካኝነት የተለቀውን (ትክክለኛ መጠኑ የጨመረውን) የፕሮስቴት ዕጢ የሚቀንስ ሕክምና ነው።

የቀዶ ጥገና ሕክምና

  •    አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በታችኛው ሆድ እና በሽንት ፊኛ በኩል በሚደረግ የቀዶ ጥገና ሕክምና የተለቀው የፕሮስቴት ዕጢ እንዲወገድ ይደረጋል።  

 

የጎንዮሽ ጉዳቶች

  • አንዳንድ ጊዜ መለስተኛ የቀዶ ጥገና ሕክምና የሚከተሉትን ችግሮች ሊያስከትል ይችላል። 

  • የወንድ ዘር ፈሳሽ ከወንድ ብልት ወደ ሽንት ፊኛ መፍሰስ (Retrograde ejaculation)

  • የሽንት ፊኛ ኢንፌክሽን

  • ደም መፍሰስ

  • ስንፈተ ወሲብ  

በቤት ውስጥ የሚደድረግ ሕክምና

ይህ ምልክቶቹን ለማስታገስ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች ማድረግ ያካትታል።

  • ምሽት ላይ የሚጠጡትን መጠጥ መገደብ፤ ከመተኛት በፊት የአሉትን 2 ወይም 3 ሰዓታት መጠጥ አለመጠጣት፡፡

  • አልኮሆል እና ካፌይን የአላቸውን መጠጦች መቀነስ፡፡

  • መድኃኒት ከመውሰድ በፊት የጤና ባለሙያን ማማከር (Antihistamine)፡፡

  • ሽንት አለመያዝ፤ ሽንት የመሽናት ፍላጎት ሲመጣ መሽናት፡፡  

  • የመጸዳጃ ቤት መርሐ ግብር ማውጣት፤ ይህ በየ4 ወይም 6 ሰዓት ሽንት መሽናት ሲሆን የሽንት ፊኛ ሽንት እንዳይዝ ለማለማመድ ይጠቅማል።

  • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ 

  • የሰውነት ሙቀት መጠበቅ፤ ቅዝቃዜ ሽንት መያዝ እና አጣዳፊ የመሽናት ፍላጎት እንዲኖር ያደርጋል።



 

Share the post

scroll top