Learning materials for your health  Learn

በእርግዝና ወቅት የአስም በሽታ

  • April 6, 2022
  • የጤና እክሎች

በእርግዝና ወቅት የአስም በሽታ

አስም በእርግዝና ወቅት ሳንባን ከሚያጠቁ በሽታዎች ዋነኛው ሲሆን፤  ከ 3 እስከ 8 በመቶ የሚሆኑ ነፍሰ ጡር ሴቶች ላይ ይታያል፡፡

አብዛኛዎቹ ነፍሰ ጡር ሴቶች የእርግዝና ለውጦች በአስማቸው ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድር ይሆን? እና ለአስም  የሚደረጉ ሕክምናዎች ፅንሱን ይጎዱ ይሆን? በማለት ይጨነቃሉ፡፡ ተገቢው የአስም ሕክምና የተደረገላቸው ሴቶች በቀላሉ ምልክቶችን መቆጣጠር እና ጤናማ ልጅ መውለድ ይችላሉ፡፡ 

📌በደንብ ቁጥጥር ያልተደረገበት የአስም በሽታ፣ የአስም በሽታን ለመቆጣጠር የሚሰጡት መድኃኒቶችን በመውሰድ  ከሚፈጠረው አደጋ እጅግ ይበልጣል፡፡

አስም ያለባቸው ሴቶች ነፍሰ ጡር ከመሆናቸው በፊት ስለ ሁኔታቸው ከጤና ባለሙያ ጋር መወያየት አለባቸው፡፡ በአጋጣሚ ነፍሰ ጡር መሆናቸውን ያወቁ ሴቶች የአስም መድኃኒታቸውን  ሳያቋርጡ መቀጠል አለባቸው፡፡ በድንገት የአስም መድኃኒቶችን ማቆም ለእርስዎ እና ለልጅዎ ጎጂ ሊሆን ይችላል፡፡

በእርግዝና ወቅት የአስም በሽታ ይከብድብኛል?

በእርግዝና ወቅት የአስም በሽታ አደገኝነት የአንዷ ሴት  ከሌላዋ ይለያያል፡፡ በመጀመሪያ እርግዝና ወቅት የአስም በሽታ አንድ ነፍሰ ጡር ላይ ምን ያህል ከባድ በሽታ እንደሚያስከትል ለመተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ በእርግዝና ወቅት አስም  አንድ ሦስተኛ በሚሆኑት ሴቶች ላይ እየባሰ ይሄዳል፡፡ በአንድ ሦስተኛዎቹ ላይ  ይሻሻላል፤ በቀሩት አንድ ሦስተኛዎቹ ላይ ደግሞ ምንም ለውጥ አያሳይም፡፡

•  የአስም በሽታ ከተባባሰባቸው ሴቶች መካከል የበሽታ ምልክቶች መጨመር ብዙውን ጊዜ በ 29 እና 36 የእርግዝና ሳምንታት ( ከ7 እስከ 9 ወር)  መካከል ይታያሉ፡፡

•  በመጨረሻዎቹ  ወራት አካባቢ የአስም በሽታ ምልክቶች ቀለል ይላሉ፡፡

•  ምጥ ብዙውን ጊዜ የአስም በሽታን አያባብስም፡፡

•  በመጀመሪያው እርግዝና  ወቅት የሚታዩት የአስም ምልክቶች ከባድነት ብዙውን ጊዜ   በሚቀጥሉት እርግዝናዎች ውስጥም ተመሳሳይ ነው፡፡

የአስም በሽታ በፅንሱ ላይ ምን ችግር ያስከትላል?

ግልፅ ባልሆኑ ምክንያቶች አስም ከሌለባቸው ሴቶች ጋር ሲነጻጸር፤ የአስም በሽታ ያለባቸው ሴቶች በሚከተሉት የእርግዝና ችግሮች የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡

•  ከፍተኛ የደም ግፊት 

•  ያለጊዜው መውለድ

•  በቀዶ ሕክምና መውለድ

•  ለዕድሜው ትንሽ የሆነ ሕፃን

ሆኖም በእርግዝና ወቅት የአስም በሽታን በጥሩ ሁኔታ መቆጣጠር ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮችን የመከሠት ስጋት ይቀንሰዋል 

በእርግዝና ወቅት የአስም በሽታ ሕክምና  ምንድነው?

በእርግዝና ወቅት የሚደረግ ሕክምና በርካታ ቁልፍ  ክፍሎች  አሉት፡፡ እነሱም አብረው  ሲተገበሩ ስኬታማ የመሆን ዕድሉን ያሰፉታል። ከእነዚህም ወስጥ፡-

📌  የአስም በሽታ ምልክቶችን ለይቶ ለማወቅ፤ የአስም ጥቃቶችን ከሚፈጥሩ  ምክንያቶች ለመራቅ እና አስም ተቆጣጣሪ መድኃኒቶችን በትክክል የመጠቀም ስልቶችን መማር፡፡

📌የእናትን የሳንባ ሁኔታ መከታተል፤ እንደ ስፓይሮሜትሪ (spirometry) ያሉ የሳንባ ተግባር ምርመራዎችን (lung function tests) በመጠቀም፤ 

📌የፅንሱን ደኅንነት መከታተል፡፡

📌 የአስም ሕመም ቀስቃሾችን (triggers)  ማስወገድ፡፡ ለምሳሌ እንደ የቤት እንስሳ፣የቤት ውስጥ አቧራ እና ጠንካራ ሽቶ የመሳሰሉትን፡፡

📌  ነፍሰ ጡር ሴቶች በቤታቸው ውስጥ ሲጋራ ማጨስን መፍቀድ የለባቸውም፡፡

📌ጉንፋን እንዳይይዝ ራስን መጠበቅ፡፡

📌 መድኃኒቶችን በአግባቡ መጠቀም፡፡ ምንም እንኳን  በእርግዝና  ወቅት ብዙ የአስም  መድኃኒቶች ጉዳት ባይኖራቸውም፤ ምን ዓይነት መድኃኒቶችን መውሰድ እንዳለብዎ ሐኪምዎን ያማክሩ፡፡

በምጥ፣ በወሊድ እና ከወሊድ በኋላ ባለው ጊዜ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አለ?

አስም ያለባቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች የምጥ እና የመውለድ ዕቅዳቸውን ከጤና ባለሙያ ጋር መወያየት አለባቸው፡፡ አስም ብዙውን ጊዜ በምጥ ወቅት፣ በወሊድ ጊዜ እና በድኅረ ወሊድ ወቅት የሚጠቀሙባቸውን መድኃኒቶች ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡

ጡት ማጥባት በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ሕፃኑ በተደጋጋሚ የአየር ቱቦ ኢንፌክሽን የሚያመጣበትን ስጋት ስለሚቀንስ፤  አስም  ያለባቸው ሴቶች ጡት እንዲያጠቡ ይበረታታሉ።

 

Share the post

scroll top