Learning materials for your health  Learn

የወሲብ (ተራክቦ) ችግሮች በሴቶች ላይ

  • April 8, 2022
  • የጤና እክሎች

የወሲብ (ተራክቦ) ችግሮች በሴቶች ላይ

ብዙ ሴቶች ከወሲብ (ግብረ ሥጋ ግኙነት) ጋር የተያያዙ የተለያዩ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ይታያሉ። ይህም በትዳራቸው ላይ አሉታዊ የሆነ ጫና እንዳለው ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው። በዚህ ጽሑፍ በሴቶች ላይ ስለሚፈጠሩ የተለያዩ የወሲብ (ተራክቦ) ችግሮች፣ ምክንያቶቻቸውና መፍትሔ እናብራራለን፤ ይከታተሉን።

የተለያዩ ዓይነት ከወሲብ (ግብረ ሥጋ ግኙነት) ጋር የተያያዙ ችግሮች በሴቶች ላይ ሊታዩ ይችላሉ። ከእነዚህ ውስጥ በብዛት የሚታዩት፤

  • ፍላጎት ማጣት 

  • ወሲባዊ መነቃቃት አለመኖር (unable to become aroused)

  • መጨረስ አለመቻል (difficult to achieve orgasm) እና

  • በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ ሕመም መሰማት ይጠቀሳሉ።

እነዚህ ምልክቶች ከትዳር አጋር ጋር ያለውን ግንኙነት መጉዳት ከጀመሩ ወይም ምልክቶቹ ጭንቀትን ከአስከተሉ ከሐኪም ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት መሞከር አስፈላጊ ነው።

በሴቶች ላይ የወሲብ ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ ነገሮች ምንድን ናቸው?

  • እንደ ካንሰር፣ የኩላሊት በሽታ፣ የልብ በሽታ እንዲሁም ከፊኛ ጋር የተያያዙ ችግሮች የወሲብ (ተራክቦ) ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

በተጨማሪም አንዳንድ የመድኃኒት ዓይነቶች እንዚህን ችግሮች ሲያስከትሉ ይታያሉ። 

ለምሳሌ

  • የድባቴ መድኃኒት

  • የደም ግፊት መድኃኒት

  • ለካንሰር በሽታ የሚሰጡ መድኃኒቶች 

  • የሚጥል በሽታ መድኃኒት

ዝቅተኛ የኤስትሮጂን ሆርሞን መጠን በሚኖርበት ጊዜ ወደ መራቢያ አካላት የሚሄደው የደም ፍሰት ስለሚቀንስ እንዲሁም የመራቢያ አካላት የመለጠጥ ዐቅም ስለሚቀንስ በግንኙነት ጊዜ ሕመም ሊያስከትል ይችላል። 

ለምሳሌ 

  • በማረጥ ዕድሜ ላይ የደረሰች ሴት

  • ከወሊድ በኋላ

  • ጡት የምታጠባ ሴት

የተለያዩ የሥነ ልቦና በሽታዎች የወሲብ ችግሮችን ሊያስከትሉ ይችላሉ። 

ለምሳሌ 

  • የጭንቀት በሽታ

  • ድባቴ

  • በራስ መተማመን የሌላት ሴት

  • ከትዳር አጋር ጋር አለመስማማት ከአለ

  • ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባት ሴት

በሴቶች ላይ የሚከሠት የወሲብ (ተራክቦ) ችግር እንዴት ይታከማል?

  • የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፍላጎትን የሚጨምሩ መድኃኒቶች

  • ኬግል እንቅስቃሴ (Kegle exercise) - ይህ እንቅስቃሴ ማንኛዋም ሴት በማንኛውም ቦታ መሥራት የምትችለው እንቅስቃሴ ነው፡፡ የመራቢያ አካሏ አካባቢ ያለውን ጡንቻ በማኮማተር እና ዘና በማድረግ እየደጋገሙ መሥራት ይቻላል። 

ኬግል እንቅስቃሴ የመራቢያ አካላት አካባቢ የሚገኘውን ጡንቻ ለማጠንከር የሚረዳ እንቅስቃሴ ነው። ይህም በግብረ ሥጋ ግንኙነት ጊዜ ሴቷ የእርካታ ጫፍ ላይ በቀላሉ እንድትደርስ ይረዳል፡፡ ከዚህም ባሻገር በማሕፀን እና አካባቢው የሚገኙ የሰውነት ክፍሎች በቦታቸው እንዲቆዩ ይረዳቸዋል። ይህም የማሕፀን ግርግዳ መርገብ (pelvic organ prolapse) እንዳይፈጠር ይረዳል።

  • ከትዳር አጋር ጋር የሚፈጠሩ ችግሮችን መፍታት በተጨማሪም ስለ ችግሮቹ በግልፅ ማውራት፤

  • እንደ ሲጋራ ማጨስ እና መጠጥ አብዝቶ መጠጣት ያሉ ጎጂ ልማዶችን መቀነስ እና በአንፃሩ ጤናማ ምግብ መመገብ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎ ማድረግ፤ 

  • እንደ ጭንቀት እና ድባቴ ያሉ ሥነ ልቦናዊ ችግሮችን ከባለሙያ ጋር በመነጋገር መፍታት የተሻሉ መፍትሔዎች ናቸው፡፡

Share the post

scroll top