Learning materials for your health  Learn

የወር አበባ ዑደት መዛባት

 • September 9, 2021
 • የጤና እክሎች

በአንጎላችን ውስጥ ያሉት የሃይፖታላመስ እና የፒቱቲሪ እጢዎች የተለያዩ ሆርሞኖችን ያመነጫሉ። ከእነዚህም ውስጥ አንዳንዶቹ በወር አንድ ጊዜ እንቁልእጢን (Ovary) ማኅፀን ለእርግዝና እንዲዘጋጅ የሚያደርጉትን ሆርሞኖች እንዲሠራ ያነሣሡታል። በዚህ መሠረትም ማኅፀን ለእርግዝና ይዘጋጃል።  እርግዝና ከአልተፈጠረ ግን በወር አበባ መልክ በወር አንድ ጊዜ ይፈስሳል ማለት ነው።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ የወር አበባ ማየት ከጀመሩ ሴቶች መካከል ከ10 – 14% (በመቶ) የሚሆኑት ችግር ያጋጥማቸዋል።  

ጤናማ የወር አበባ ዑደት የሚባለው መቼ ነው?

ይህም እንደሚከተለው በአማካኝ ተቀምጧል።

 • የሚመጣው በ21-35 ቀናት
 • የሚቆየው ከ 2 – 7 ቀናት

 • መጠኑ ከ 80 ሚ.ሊ. ያልበለጠ

 • የረጋ ደም መኖር የለበትም፤ ከአለም ከ 2.5 ሴ.ሜ. መብለጥ የለበትም፡፡

 • የወር አበባ ሲመጣ ብዙ ጊዜ ሌሊት ሌሊት  ሞዴስ መቀየር የማያስፈልግ ከሆነ፤ እነዚህ የጤናማ የወር አበባ ዑደት መገለጫዎች ናቸው።

ሆኖም በቅርብ የወር አበባ ማየት የጀመረች ኮረዳ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት የወር አበባ ዑደት መዛባት ሊያጋጥማት ይችላል። ይህ የሚሆንበት ምክንያት የወር አበባ ዑደቱን የሚያመጡት ሆርሞኖች በደንብ ተናበው መሥራት እስከሚጀምሩ ትንሽ ወራትን ስለሚፈልጉ ነው። ስለዚህ የጤና ባለሙያዎች ከላይ ከተጠቀሰው የጤናማ የወር አበባ ዑደት ውጪ የሚከሠተውን ዑደት “የወር  አበባ  ዑደት መዛባት” ይሉታል።

የወር  አበባ  ዑደት መዛባት እና መንሥኤዎቹ

 •  እርግዝና ለወር አበባ መዛባት ወይም መቅረት አንድ መንሥኤ ሊሆን ይችላል።

 •   የሆርሞን ችግር

ሃይፖታላመስ እጢ በቂ ሆርሞኖችን (GnRH) እያመረተ ከአልሆነ።

ሃይፖታላመስ በቂ ሆርሞኖችን እንዳያመርት የሚያደርጉ ነገሮች ምንድናቸው? 

 • ዝቅተኛ የሰውነት ክብደት (ከጤናማው የሰውነት ክብደት 10 ፐርሰንት በታች   

             ሲሆን)

 • አመጋገብ ችግሮች (Anorexia nervosa, Bulimia)

 • የስሜት አለመረጋጋት (ውጥረት፣ ጭንቀት)

 • ከባድ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ  እና አንዳንድ አንጎልን የሚያጠቁ  ሕመሞች ናቸው።

 • እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ መንሥኤው ላይታወቅ ይችላል።

የፒቱታሪ ሆርሞኖች ችግር

የፒቱታሪ ሆርሞኖች በበቂ ሁኔታ እንዳይመረቱ የሚያደርጉ ነገሮች ምንድናቸው? 

 • አንዳንድ የፒቱታሪ ዕጢዎች (Prolactinoma)

 • የተወሰኑ የሆርሞን ወሊድ መቆጣጠሪያ ዓይነቶች (Hormonal contraceptive)

የማኅፀን ወይም የእንቁልጢ ችግር         

 • የሆርሞን ችግር ( PCOS)

 • ያለዕድሜ ማረጥ (Early menopause)

 • የማኅፀን ቀዶ ጥገና ሕክምናዎች ወይም የማኅፀን አካልን የሚነኩ የኅክምና ሂደቶች (Gynecologic & obstetrical procedures)

ከነዚህ በተጨማሪ ሌሎች በሰውነታችን ውስጥ ያሉት የሆርሞኖች መዛባት ለተመሳሳይ ችግር ሊያጋልጥ ይችላል።

    ለምሳሌ፡- የእንቅርት ሆርሞን መብዛት ወይም ማነስ፣ ኩሺንግ ሲንድሮም (Cushing syndrome) ናቸው።

ሌሎች መንሥኤዎች ምንድናቸው?

 • የማኅፀን ዕጢ (Myoma) ወይም አርባሜ (Polyps) 

 • ጡት ማጥባት

 • የማኅፀን ውስጥ ሽፋን ባልተለመደ ሁኔታ ወፍራም ሲሆን (Endometrial hyperplasia) 

ምርመራው ምንድነው?

የጤና ባለሙያው ታማሚዋን የሚከተሉትን ጥያቄዎች በመጠየቅ ፍንጭ ለማግኘት ይሞክራል።  የወር አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየችበትን ዕድሜ፣ ከጡቶቿ ጫፍ የሚወጣ ፈሳሽ፣ ብጉር፣ የፊት ወይም የደረት ፀጉር፣  ራስ ምታት ወይም የዐይን እክል ካለ ለማወቅ ይሞክራል።

በተጨማሪም የምትወስዳቸውን መድኃኒቶች፣ ጭንቀት ከነበራት፣ የቅርብ ጊዜ የማኅፀን ሕክምና ፣ የአመጋገብ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ዘይቤዎቿን እና በቤተሰብ ውስጥ ተመሳሳይ ሕመም መኖሩን ለማወቅ ይሞክራል።

 • አካላዊ ምርመራ፡- በአካል ምርመራ ወቅት የጤና ባለሙያው  የፊት፣ የአንገት፣ የጡት እና የሆድ ክፍልን ሊመረምር ይችላል።
 • የሽንት  እና የደም ምርመራዎች - ይህ የእርግዝና እና የሆርሞኖች መጠን ምርመራን ያጠቃልላል።
 • የምስል ምርመራዎች - የማኅፀን አልትራሳውንድ ምርመራ ሊታዘዝ ይችላል። በተጨማሪም እንደአስፈላጊነቱ የጭንቅላት ኤም. አር. አይ (MRI) ወይም ሲቲ ስካን (CT scan) ምርመራ ሊታዘዝ ይችላል።

የወር አበባ ዑደት መዛባት እንዴት ይታከማል?

የሕክምናው ዋና ዓላማ የወር አበባ መዛባት ያመጣውን መንሥኤውን ማወቅ እና ማስተካከል ነው፡፡ ሕክምናው የአኗኗር ዘይቤዎችን መቀየር፣ መድኃኒቶችን መውሰድ፣ ብሎም ቀዶ ጥገናን ማድረግ ሊጨምር ይችላል።

1. የአኗኗር ዘይቤዎችን መቀየር

እነዚህም ሚከተሉትን ያጠቃልላሉ፡፡

 • ዝቅተኛ የሰውነት ክብደትን ማስተካከል እና የተመጣጠነ ምግብ መውሰድ ናቸው። በተጨማሪም  የአመጋገብ  ችግሮች (Anorexia nervosa, Bulimia) ካሉ የጤና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል።

 • አብዝቶ የሚደረግን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መቀነስ። በተጨማሪም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በምናደርግበት ወቅት የምንወስደውን የካሎሪን መጠን መጨመር  ያስፈልጋል፡፡

2. መድኃኒቶች ወይም የሆርሞን እንክብሎች

መንሥኤው የሆርሞኖች መዛባት ከሆነ፤ ይህንን  የሚያመጡ ሕመሞችን ለማከም፤  መድኃኒቶች ወይም የሆርሞኖን እንክብሎች በጤና ባለሙያዎች ለ ሦስት ወር ሊታዘዙ ይችላሉ።

3. ያለ ዕድሜ ማረጥ (Early menopause)

ይህ ከሆነ መንሥኤው በዚህ ምክንያት የሚመጡ ምልክቶችን ለማስታገስ የጤና ባለሙያው የሆርሞን ሕክምና ሊያደርግ ይችላል።

4. ቀዶ ጥገና

መንሥኤዎቹ የማኅፀን ጠባሳ ወይም ሌሎች የማኅፀንን ቱቦ የሚዘጉ ችግሮች ከሆኑ  ቀዶ ጥገና መፍትሔ ሊሆን ይችላል።

አንዳንድ ከወር አበባ መዛባት ጋር የተያያዙ የጭንቅላት ዕጢዎች በመድኃኒት ወይም በቀዶ ጥገና ሊታከሙ ይችላሉ።

Share the post

scroll top