Learning materials for your health  Learn

ከፍተኛ የቅሪት ትውከት

  • April 11, 2022
  • የጤና እክሎች

ከፍተኛ የቅሪት ትውከት (Hyperemesis gravidarum)

  • በእርግዝና ወቅት ከ 50 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑ ነፍሰ ጡር እናቶች የተወሰነ የማቅለሽለሽ እና የትውከት ስሜት ይኖራቸዋል። ይህ ብዙውን ጊዜ ከ 5 እስከ 18 ሳምንታት በአሉት የእርግዝና ወቅቶች ላይ የሚከሠት ነው፡፡

 

ከፍተኛ የቅሪት ትውከት እና የቅሪት ትፋት ልዩነታቸው ምንድነው?

የቅሪት ትፋት (Morning sickness) 

  • ይህ አብዛኛውን ጊዜ በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የሚከሠት መለስተኛ የማቅለሽለሽ እና የማስታወክ  ስሜት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ከ16 ወይም ከ18 የእርግዝና ሳምንታት በኋላ ምልክቶቹ እየተሻሉ ይሄዳሉ። 

ከፍተኛ የቅሪት ትውከት (Hyperemesis gravidarum)

  • ከፍተኛ የቅሪት ትውከት በእርግዝና ወቅት የሚከሠት፣ መደበኛ እንቅስቃሴን የሚያውክ ከባድ የሆነ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ ነው። ይህ በሽታ ከ 0.5 እስከ 2 በመቶ የሚሆኑ ነፍሰ ጡር እናቶችን ያጠቃል። 

 መንሥኤው ምንድነው?

  • አሁን ባለው ሳይንሳዊ ጥናት መሠረት ከእንግዴ ልጅ የሚመረቱ የምግብ ፍላጎትን የሚቆጣጠሩ ሆርሞኖች መዛባት እና የዘረ መል (Genetic predisposition) ተጽዕኖ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳሉ። 

  • በተጨማሪም ምንም እንኳን የተረጋገጠ ጥናት ባይኖርም የጨጓራ ምግብ አለመፍጨት፣ የጨጓራ ባክቴሪያ (H. pylori)፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና የሥነ ልቦና ችግር የራሳቸው ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይገመታል።  

ለከፍተኛ የቅሪት ትውከት ተጋላጭ የሆኑ ነፍሰ ጡር እናቶች እነማን ናቸው?

  • በቀድሞ እርግዝና ተመሳሳይ ሕመም ያላቸው

  • በቤተሰብ ውስጥ ተመሳሳይ ሕመም መኖር

  • በማሕፀን ውስጥ ከአንድ በላይ ፅንስ መኖር ( ለምሳሌ መንታ)

  • ያልተለመደ የእንግዴ ልጅ እና የእርግዝና ዓይነት (Molar pregnancy)

  • የጨጓራ ሕመም

  • ከኢስትሮጅን ሆርሞን የተሠሩ መድኃኒቶችን ሲወስዱ የሚያማቸው ሴቶች (ለምሳሌ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል)

  • በመኪና ጉዞ ወቅት የሚያማቸው (Motion sickness)

  ምልክቶቹ ምንድናቸው?

አብዛኛውን ጊዜ ምልክቶቹ የሚከሠቱት ከ 20 የእርግዝና ሳምንታት በፊት ነው። እነዚህም

  • በቀን ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሠት ማቅለሽለሽ እና ትውከት

  • የድካም ስሜት

  • የትንፋሽ ሽታ መቀየር (ketone breath) 

  • የልብ ምት መጨመር

  • አንዳንድ ጊዜ ፋታ የማይሰጥ ትውከት፣ ደም ሊቀላቅል ይችላል፡፡

  • የሽንት መጠን መቀነስ እና የሽንት ቀለም  መጥቆር ናቸው፡፡ 

በአጠቃላይ እነዚህ ምልክቶች በሚኖሩበት ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሔድ ያስፈልጋል።

በአግባቡ ያልታከመ ከፍተኛ የቅሪት ትውከት ምን ዓይነት የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል?

 በአግባቡ ያልታከመ ከፍተኛ የቅሪት ትውከት በእናት እና በፅንስ ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። እነዚህም 

  • የእናት ክብደት መቀነስ፣ ይህም እናቶች 5 በመቶ የሚሆነውን የቅድመ ወሊድ ክብደታቸውን ሊቀንሱ ይችላሉ።

  • የሰውነት ፈሳሽ ድርቀት (Dehydration)

  • አጣዳፊ የኩላሊት ጉዳት

  • የሰውነት ንጥረ ነገር መዛባት (Electrolyte imbalance)

  • ምራቅ መብዛት፤ ይህም ምልክቶቹን ሊያባብሰው ይችላል።

  • በተጨማሪም ነፍሰ ጡር እናቶችን ለተደጋጋሚ ጊዜ በሆስፒታል ለመተኛት ሊዳርጋቸው ይችላል።

ሕክምና

  • አብዛኛውን ጊዜ ሕመሙ ከ20 ሳምንት የእርግዝና ወቅት በኋላ በራሱ እየጠፋ ይሄዳል። ስለዚህ የሕክምናው ዋና ዓላማ ሕመሙን ማዳን ሳይሆን ምልክቶቹን በማስታገስ  እናትየው በቂ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ በአፏ እንድትወስድ ማስቻል ነው።

  •  ሕክምናው የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ እና መድኃኒቶችን ያካትታል።

የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ

የአመጋገብ ለውጥ

  • የሚወስዱትን ምግብ እና ፈሳሽ መጠን ማሳነስ፤ ነገር ግን ቶሎ ቶሎ (ቢያንስ በቀን 6 ጊዜ) ትንሽ ትንሽ መውሰድ ይመከራል።

  • ምግብን አቀዝቅዞ መመገብ፤ በተለይም ትኩስ ነገር ሕመሙን የሚቀሰቅሰው ከሆነ ምግቡን አቀዝቅዞ  መመገብ ያስፈልጋል። 

  • በፕሮቲን እና በካርቦሃይድሬት የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ እና ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች መቀነስ፡፡

  • በምግብ መሐል ጎምዘዝ ያሉ መጠጦችን መጠቀም፤ ለምሳሌ የዝንጅብል ወይም የሎሚ ጭማቂ፤ 

  • የዝንጅብል ዱቄት ወይም ሻይ በእርግዝና ወቅት መጠቀም የትውከት ምልክቶችን ለማስታገስ ይረዳል።

  • ሎሚ፣ ሚንት ወይም ብርቱካን ማሽተት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

  • ከምግብ በኋላ ጥርስን ማፅዳት (Tooth brushing)

  • ከምግብ በኋላ ምግብ ሳይንሸራሸር  አለመተኛት፡፡

ምልክቶቹን የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ማስወገድ

ይህ ለሕክምና እጅግ አስፈላጊ ነገር ሲሆን፤ የሚከተሉትን በማስወገድ የማቅለሽለሽ እና የትውከት ስሜትን መቀነስ ይቻላል። 

  • ሽታ ( ለምሳሌ ሽቶ፣ ኬሚካል፣ ቡና፣ ምግብ፣ ጭስ)

  • ጣፋጭነት ያላቸው ምግቦች  

  • ቅመም እና ቅባት የበዛባቸው ምግቦች 

  • የተጨናነቁ ወይም ጫጫታ የበዛባቸው አካባቢዎች

  • ከፍተኛ ሙቀት ወይም ቅዝቃዜ

  • ከመጠን ያለፈ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ 

  • ከመጠን በላይ የሆነ ምራቅ (Ptyalism)

  • ከመጠን ያለፈ የድካም ስሜት ናቸው።

 

በጤና ተቋም ውስጥ የሚደረጉ ሕክምናዎች

በደም ሥር የሚሰጥ ፈሳሽ እና አልሚ ምግብ

  • ምልክቶቹ በጣም ከባድ በሚሆኑበት ጊዜ  በደም ሥር (IV) ቫይታሚን እና ንጥረ ነገር የያዘ ፈሳሽ እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ በተጨማሪም ለአጭር ጊዜ (ከ 24 እስከ 48 ሰዓታት) 

  • በአፍ ምንም ዓይነት ነገር መውሰድ ሊከለከል ይችላል።

  • አስፈላጊ ከሆነ ምግብ ቱቦን (በአፍንጫ በኩል ወደ ሆድ  የሚገባ ቱቦ) በመጠቀም ምግብ እንዲወስዱ ይደረጋል። በተጨማሪም የሚቻል ከሆነ በደም ሥር( IV) በኩል አልሚ ምግብ ሊሰጥ ይችላል ፡፡

መድኃኒቶች

  • አንዳንድ ጊዜ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክን የሚያስታግሱ ደኅንነታቸው የተጠበቀ መድኃኒቶች በጤና ባለሙያዎች ሊታዘዙ ይችላሉ። ነገር ግን በእርግዝና ወቅት ማንኛውንም ዓይነት መድኃኒት ከመወሰዱ በፊት ስለደኅንነቱ  ሐኪምን ማናገር ያስፈልጋል።  


 

Share the post

scroll top