Learning materials for your health  Learn

ከምጥ በፊት የሽርት ውሃ መፍሰስ

 • April 12, 2022
 • የጤና እክሎች

ከምጥ በፊት የሽርት ውሃ መፍሰስ

(Premature rupture of membranes /PROM/)

ብዙውን ጊዜ የሽርት ውሃ የሚፈስሰው ምጥ ከጀመረ በኃላ ቢሆንም፤ ከ 8 እስከ 10 % የሚሆኑ ነፍሰ ጡሮች ላይ ምጥ ከመጀመሩ በፊት ሊፈስስ ይችላል። ይህም ፕሮም ይባላል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ላይ እርግዝናው 37 ሳምንት ከመሆኑ በፊት ይከሠታል። ይህም ማለት ፅንሱ ሙሉ በሙሉ ዕድገቱን ከመጨረሱ በፊት ምጥ እንዲጀምር ምክንያት ይሆናል። ለዚህም ነው አንድ ሦስተኛ ለሚሆኑት ያለጊዜያቸው ለሚወለዱ ሕፃናት እንደ ምክንያት የሚቀርበው ከ37 ሳምንት በፊት የሚፈጠረ የሽርት ውሃ መፍሰስ የሆነው።

ከፕሮም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ብዙ ችግሮች አሉ። ይህም ለእናትዬዋም ሆነ አዲስ ለተወለደው ሕፃን የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል። 

ፕሮምን ሊያስከትሉ የሚችሉ አጋላጭ ሁኔታዎች ምን ምንድን ናቸው?

 • ከዚህ ቀደም ያለ እርግዝና ላይ ተመሳሳይ ችግር (ፕሮም) አጋጥሞ ከነበረ

 • ከዚህ በፊት እናትዬዋ ከመውለጃዋ ቀን በፊት ያለጊዜው የጀመረ ምጥ ከነበራት

 • የሽንት ቧንቧ እና የማሕፀን ኢንፌክሽን

 • በእርግዝና ጊዜ የሚፈጠር የደም መፈሰስ (antepartum hemorrhage)

 • ሲጋራ ማጨስ

 • የሽርት ውሃ ከሚገባው መጠን በላይ የአላቸው እናቶች

 • እናቲቱ መንታ ከአረገዘች 

 • የፅንሱ ክብደት ከመደበኛው በላይ ከሆነ

 • እናቲቱ የተመጣጠነ ምግብ የማትመገብ ከሆነ እና ክብደቷ ከመደበኛው በታች ከሆነ

 • የሽርት ውሃ ከረጢቱን የሚያሳሱ በሽታዎች

የፕሮም ምልክቶች ምንድን ናቸው?

አንዲት ነፍሰ ጡር የሽርት ውሃ በተለያየ መልኩ ሊፈስሳት ይችላል። ለምሳሌ አንድ አንድ ሴቶች ላይ የሽርት ውሃው ቷ ብሎ ሊፈነዳ ይችላል። ብዙውን ጊዜ ግን የእርጥበት ሰሜት ወይም ቀስ ብሎ የሚወጣ ፈሳሽ ሊኖራት ይችላል። 

ይህ ማለት ግን እርጥበት ያላቸው ነፍሰ ጡር ሴቶች በሙሉ ፕሮም አላቸው ማለት አይደለም። ከሽርት ውሃ ውጪ ከብልት የሚወጡ ፈሳሾች እንዲሁም ሽንትን ያለመቆጣጠር ችግር ተመሳሳይ ምልክቶች ሊሰጡ ይችላሉ።

ከፕሮም ጋር ተያይዞ የሚመጣ ኢንፌክሽን (Chorioamnionitis) ከአልተፈጠረ ፈሳሹ ሽታ የሌለው ንጹሕ ወይም ነጣ ያለ ቢጫ ቀለም ይኖረዋል። የፈሳሹ ቀለም ወይም ሽታ ከተቀየረ ግን ኢንፌክሽን ተፈጥሮ ሊሆን ስለሚችል አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ የተለያዩ የኢንፌክሽን ምልክቶች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ የእናትዬዋም ሆነ የልጁ የልብ ምት መፍጠን እና ትኩሳት የመሳሰሉትን ምልክቶች መጥቀስ ይቻላል።

ከዚህም በተጨማሪ እናትዬዋ ምጥ ሊጀምራት ይችላል። ይህም የሚታወቀው እየጨመረ የሚሔድ የሆድ ቁርጠት እና የማሕፀን በር ለውጦች ከአሉ ነው። 

እናትዬዋ ምጥ የጀመራት እርግዝናው 37 ሳምንት ከመሙላቱ በፊት ከሆነ ደግሞ ሕፃኑ ያለጊዜው ከመወለድ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ችግሮች ተጠቂ ይሆናል። ይህም ሙቀቱን መጠበቅ አለመቻል፤ በደም ውስጥ የስኳር መጠን ማነስ፤ የመተንፈስ ችግር፤ ጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ፤ የአንጀት ቁስለት እንዲሁም በጨቅላነት ጊዜ የሚፈጠር ኢንፌክሽንን ያጠቃልላል።

ከዚህ በተጨማሪ ከ 37 ሳምንት በፊት የእንሽርት ውሃ ከፈሰሳቸው እናቶች ውስጥ ከ 2 እስከ 5 በመቶ የሚሆኑት ላይ የእንግዴ ልጅ ከማሕፀን ግርግዳ ጋር መለያየት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ለዚህም የተጋለጡ እናቶች የደም መፍሰስ እና የልጁ በማሕፀን ውስጥ መሞት ሊያጋጥማቸው ይችላል።

ከላይ የተጠቀሱትን ምልክቶች ከአዩ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ሕክምና እና ክትትል ማግኘት ያስፈልጋል።

ፈሳሹ የሽርት ውሃ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የሚረዱ ምርመራዎች ምንድን ናቸው?

ወደ ጤና ተቋም እንደሄዱ ሐኪምዎ የሚከተሉትን ጥያቄዎችን ሊጠይቅዎ ይችላል። 

 • የሽርት ውሃ መፍሰስ መቼ እንደጀመረዎት?

 • የፈሳሹ ቀለም እና ሽታ

 • ፈሳሹ ደም ከቀላቀለ

 • ትኩሳት፣ ላብ፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የልብ በፍጥነት መምታት እና የመሳሰሉት የኢንፌክሽን ምልክቶች ከአሉ

 • የሆድ ቁርጠት እና ሌሎች የምጥ ምልክቶች ከአሉ

በመቀጠልም ሐኪምዎ የእስፔኩለም ምርመራ (speculum exam) ያረግልዎታል። ይህም ምርመራ የሚደረገው በጀርባዎ ከተኙ በኋላ እግርዎን በመክፈት ከጀርም ንክኪ ነፃ የሆነ እስፔኩለም በተባለ መሣሪያ በመጠቀም የሚደረግ ምርመራ ነው። ይህም ምርመራ ዋና ጥቅሙ ከማሕፀን በር የሚወጣ ፈሳሽ እንዳለ ለማረጋገጥ እና የፈሳሹ መጠን በስንት ጊዜ እንደሚጨምር ለማየት ነው፡፡ ከእስፔኩለም ምርመራ በተጨማሪ ሐኪምዎ የአልትራሳውንድ ምርመራ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህም ምርመራ የፅንሱን ጤንነት እና የእንሽርት ውሃን መጠን ይመረምራል። ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች እያለዎት በተጨማሪም የአልትራሳውንድ ውጤቱ ላይ የእንሽርት ውሃ ማነስ ከአሳየ ፕሮም እንዳለ ሊያመላክት ይቻላል።

ከዚህ በተጨማሪ የናይትራላይዚን ፔፐር ምርመራ ሊደረግ ይችላል። ይህ ምርመራ የሚሠራው ቤዛማ የሆነው የሽርት ውሃ ከናይትራላይዚን ወረቀቱ ጋር ሲገናኝ ወረቀቱን ወደ ሰማያዊ ይቀይረዋል።

በተጨማሪም እንደ ፈርን እና አሚኑሹር የሚባሉ ሌሎች ተጨማሪ  ምርመራዎች ሊደረጉ ይችላሉ።  

ከበሽታው ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ምን ምንድን ናቸው?

ከፕሮም ጋር ተያይዘው የሚመጡ ብዙ ችግሮች አሉ። ይህም ለእናትዬዋም ሆነ አዲስ ለተወለደው ሕፃን የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል። ለምሳሌ :-

 • ፅንሱ ከመወለጃ ቀኑ በፊት ቀድሞ ሊወለድ ይችላል። ይህም ከላይ እንደተጠቀሰው ሕፃኑ ሙቀቱን መጠበቅ አለመቻል፣ በደም ውስጥ የስኳር መጠን ማነስ፣ የመተንፈስ ችግር፣ ጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ፣ የአንጀት ቁስለት እንዲሁም በጨቅላነት ጊዜ የሚፈጠር ኢንፌክሽንን ሊያስከትል ይችላል።

 • ከዚህ በተጨማሪ የእትብቱ ገመድ ከሕፃኑ ቀድሞ ከወጣ ሕፃኑ እናቱ ሆድ ውስጥ እንዳለ ሊታፈን እና ሊሞት ይችላል።

 • በሌላ በኩል ከፕሮም ጋር ተያይዞ የሚመጣ ኢንፌክሽን (Chorioamnionitis) ሊከሠት ይችላል። ይህም የሚገለፀው የእናቲቱ የሙቀት መጠን መጨመር እንዲሁም የፅንሱ እና የእናቲቱ የልብ ምት መጠን መጨመር ሊያስከትል ይችላል። ቶሎ ምጥ እንዲጀምር ከአልተደረገ በእናቲቱ እና በፅንሱ ላይ ችግር ያስከትላል።

 • በተጨማሪም በሽታው የሽርት ውሃ ማነስ እና የፅንሱ ሳንባ አለማደግ ያስከትላል።

ፕሮም እንዴት ይታከማል?

ከምጥ በፊት የሽርት ውሃ የፈሰሳቸው ነፍሰ ጡሮች ልጃቸው እስኪወለድ ድረስ በሆስፒታል ውስጥ መቆየት አለባቸው፡፡ እርግዝናው እንዳለበት ወር ቢወሰንም ብዙውን ጊዜ እናቶቹ ምጥ የሚጀምራቸው በ አንድ ሳምንት ውስጥ ነው፡፡

በአጠቃላይ ስናየው ሕክምናው ሦስት ነገሮች ላይ ያተኩራል።

 • የፅንሱ አጠቃላይ ዕድገት በተለይ የሳንባ ዕድገት

 • ኢንፌክሽን እንዳይፈጠር መከላከል፤ እንዲሁም ሌሎች ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች እንደሌሉ ማረጋገጥ

 • ምጥ የሚጀምርበትን ሰዓት መጠበቅ ወይም መወሰን

ለምሳሌ እርግዝናው ከ 34 ሳምንት በፊት ከሆነ የፅንሱን የሳንባ ዕድገት የሚጨምር መድኃኒት ለእናትየው በመርፌ መልክ ተሰቷት ምጥ እስኪጀምራት ይጠበቃል። ነገር ግን እናትየው የኢንፌክሽን ምልክቶች ከአሏት የፅንሱን የሳንባ ዕድገት የሚጨምረው መድኃኒት እንደተሰጣት ልጁ በተቻለ መጠን ቶሎ ቢወለድ ይመከራል። ስለዚህም ከላይ በተጠቀሰው መሠረት እነዚህን ሦስት ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት ሐኪሙ ለእርስዎ የሚሆነውን ሕክምና ይመርጥልዎታል። 

 

Share the post

scroll top