Learning materials for your health  Learn

የቤል ፓልሲ    

  • April 20, 2022
  • የጤና እክሎች

መጋኛ ?

 የቤል ፓልሲ (Bell’s Palsy)                 

RyrlvaCKNhreCjjQ_wz4VpsBXnoz2fDeUIeCWei31ttSw_OiZ4IpKiSQmYM68Z1WCfHDxJpJPo5jxtO1rqq1208-wqBHOi8qfFQEGwhEwdcozzjE6f37bLTwK0L4T3HNvjwHFkik

     የቤል ፓልሲ በተለምዶ ‹‹መጋኛ›› እየተባለ የሚጠራው በሽታ የፊት ጡንቻዎችን የሚቆጣጠረው ነርቭ (facial nerve) ጉዳት ሲደርሰበት ወይም ሙሉ በሙሉ መሥራት ሲያቆም የሚከሠት ነው፡፡ ይህ በሽታ የፊት ጡንቻዎች እንዲዳከሙ ወይም ሽባ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ፡፡

የቤል ፓልሲ በሽታ የያዛቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ይድናሉ፡፡ የተቀሩት ላይ ግን አንዳንድ ምልክቶች እስከ ዕድሜ  ልክ ይቀጥላሉ። የቤል ፓልሲ ምልክቶች ከአለብዎ ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይመከራል።

  • ለየቤል ፓልሲ በሽታ የሚያጋልጡ ምክንያቶች ምን ምን ናቸው?

የቤል ፓልሲ በሽታ ሁሉንም  የዕድሜ ክልል እና ሁለቱንም ፆታዎች በእኩልነት የሚያጠቃ በሽታ ነው፡፡

  • የስኳር በሽታ

  • እርግዝና 

  • ከዚህ በፊት በዚህ በሽታ የተጠቃ የቤተሰብ አባል ከአለ

  • የደም ግፊት በሽታ

  • አደጋ ከአጋጠመዎ

  • አንዳንድ የባክቴሪያ ኢንፌክሽኖች

  • የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽን  እንደ አጋላጭ ሁኔታዎች ይጠቀሳሉ፡፡

የቤል ፓልሲ በሽታ መንሥኤዎች

የቤል ፓልሲ የሚከሠተው የፊት ጡንቻዎችን የሚቆጣጠረው ነርቭ በሚያብጥ እና በሚቆጣበት ጊዜ ነው፡፡ ለዚህም የተለያዩ  ቫይረሶች እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል፤

  • ምች የሚያመጣው ቫይረስ (herpes simplex virus) 

  • ኤች አይ ቪ ቫይረስ (HIV)

  • አልማዝ ባለ ጭራ የሚያስከትለው (herpes zoster virus) 

  • ሳይቲሜጋሎ ቫይረስ  (cytomegalovirus) 

  • ኤፕስቲን ባር ቫይረስ (epstein bar virus) ይጠቀሳሉ፡፡

 

 4Rbdx306sjndAzIa1YoLOylRQgtjJnHvA3L8OsYSDDZsY2ziRk52iq1JnjfaANFcNwioeQBZWwCwC65KIijrVAEUA9triiWkC60Qn0BwSl7_wMwQXm3QK96YisiBi3Ood9ac6MhU

 

የቤል ፓልሲ ምልክቶች

የቤል ፓልሲ በሽታ በከፊል የፊት ጡንቻዎችን የሚያሰንፍ ሲሆን፤ ችግሩ የሚከተሉትን ምልክቶች በግማሽ የፊት ገጽታ ላይ ያስከተላል።

  •  የቅንድብ፣ የዐይን ሽፋን እና የአፍ ጥግ መውደቅ

  • አንድ ዐይን ሙሉ በሙሉ የመዘጋት መደበኛውን ችሎታ ማጣት። ይህም የዐይን ንጣፍ (ኮርኒያ) እንዲደርቅ ሊያደርግ ይችላል፡፡

  • መሳቅ፣መኮሳተር ወዘተ ዓይነት ስሜቶችን በፊት መግለጽ አለመቻል፡፡ 

  • የምራቅ እና የእንባ መጠን መቀነስ

  •  ራስ ምታት

  •  የምራቅ መዝረብረብ

  • ከፍ ያሉ ድምፆች በተጎዳው ጎን ያለው ጆሮ ላይ ምቾት መንሣት (dysacusis)

  •  አንዳንድ ሰዎች ላይ በምላስ የፊተኛው ክፍል የጣዕም ስሜትን ማጣት

  • በተጨማሪም በድንገት የሚከሠት ስለሆነ የጭንቀት እና የደንጋጤ ስሜት ሊኖር ይችላል፡፡

የቤል ፓልሲ በሽታ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ በአንድ ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ መታየት ሲጀምሩ  አብዛኛዎቹ  ሕመምተኞች በሦስት ሳምንታት ውስጥ መሻሻል ያሳያሉ፡፡ ሙሉ በሙሉ ለማገገም  ከሶስት እስከ  ስድስት ወር ሊቆይ ይችላል ፡፡

ለቤል ፓልሲ የሚደረጉ  ምርመራዎች

የቤል ፓልሲ በሽታ የሚታወቀው በአካል ምርመራ ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡ ምናልባት አንዳንድ ጊዜ የደም እና ሌሎች ምርመራዎች ሊደረጉ ይችላሉ። ለምሳሌ የሲቲ ስካን (CT scan)፣ ኤም አር አይ (MRI) ምርመራዎች።

የቤልስ ፓልሲ ሕክምና

የቤል ፓልሲ በሽታ ፈውስ የለውም፡፡ ነገር ግን ሕክምናው በፍጥነት ለመዳን ይረዳል፡፡ በተለይም ሕክምናው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ የተጀመረ ከሆነ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል። ሕክምናው የሚከተሉትን ክፍሎች ይይዛል።

የዐይን እንክብካቤ 

ዐይንዎን መዝጋት ከአልቻሉ የዐይን ሕክምና ያስፈልግዎታል፡፡ ለዐይን ግልፅ የመከላከያ ሽፋን የሆነው ኮርኒያ ከመጠን በላይ ደረቅ ከሆነ ዘላቂ የሆነ የዐይን ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡ 

ይህንንም ለመከላከል የዐይን እርጥበት እንዲኖር  ሰው ሠራሽ እንባ (የዐይን ጠብታ) መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ የዐይን ጠብታውን የእይታ መደብዘዝ እንዳያመጣ ማታ ላይ መጠቀም የተሻለ ነው። ቀን ላይ ዐይንዎን ከአቧራ እና የመሳሰሉት ለመጠበቅ መነጽር መጠቀም አለብዎት፡፡

 በእንቅልፍ ሰዓትም የዐይን ሽፋን ማድረግ ተገቢ ነው።

መድኃኒቶች 

 በቤል ፓልሲ በሽታ መያዝዎ በቶሎ ከታወቀ (ከመጀመሪያዎቹ ከ 2 እስከ 3 ቀናት ውስጥ)

  • በስትሮይድስ (steroids) ለአንድ ሳምንት ያህል ይታከማሉ፡፡ ይህም መድኃኒት የነርቭ እብጠትን ሊቀንስ እና ሙሉ በሙሉ የመዳን ዕድልን ያሻሽላል ተብሎ ይታመናል።

  • የፀረ-ቫይረስ መድኃኒቶች (ለምሳሌ  valacyclovir) አንዳንድ ጊዜ  ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ ነገር ግን   እነዚህን  መድኃኒቶች  መጠቀም ተጨማሪ ጥቅም ማስገኘቱን ጥናቶች አላረጋገጡም፡፡

  • የሕመም ማስታገሻ መድኃኒቶች 

የቅርብ ክትትል -

ሕክምና ከጀመሩ በኋላ ከሐኪምዎ  ጋር ክትትል የሚደረግበት ቀጠሮ  ያስፈልግዎታል፡፡ በዚያን ጊዜ ምርመራ ይደረግልዎታል፤ ማንኛውንም ጥያቄ ወይም ችግር መወያየት ይችላሉ፡፡

  •  አኩፓንቸር (Acupuncture)

  • የኤሌክትሪክ ንዝረት ሕክምና (Electrical stimulation)

  • አካላዊ ሕክምና (physical therapy)

ለቤል ፓልሲ ሕመም በቤት ውስጥ የሚደረግ እንክብካቤ

  • የዐይን መሸፈኛ መጠቀም 

  • ለብ ባለ ውሃ የተነከረ ፎጣ በተጎዳው ፊት ላይ ማድረግ 

  • የተጎዳውን ፊት ማሸት ወይም ማሳጅ ማድረግ 

  • በብርጭቆ ለመጠጣት አስቸጋሪ ከሆነ በመምጠጫ (straw) መጠቀም

ከቤል ፓልሲ ሕመም ማገገም 

በአጠቃላይ ቀላል የፊት ጡንቻዎች መስነፍ ያለአጋጠማቸው ሰዎች ሙሉ በሙሉ የማገገም አዝማሚያ አላቸው፡፡ ምልክቶቹ በመጀመሪያዎቹ 21 ቀናት ውስጥ መሻሻል ከጀመሩ መልሶ የማገገም እና በፊቱ ጡንቻዎች ላይ ቀሪ ድካም ያለመኖር ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ሆኖም በጥቂት ሰዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ ያሉ የፊት ጡንቻ ድክመቶች በቋሚነት ይከሠታሉ፡፡ 

የቤል ፓልሲ በሽታ ውስብስብ ጉዳቶች

በበሽታው ምክንያት የደረሰው ጉዳት ከባድ ከሆነ እና ነርቭ በአልተስተካከለ መንገድ ሲያድግ የተለያዩ የፊት እንቅስቃሴዎችን የመቆጣጠር ችሎታ ሊጠፋ ይችላል፡፡ ለምሳሌ፤

  •  የዐይን ሽፋን ሲርገበገብ አፍ አብሮ ይንቀጠቀጣል፡፡

  •  ዐይን ሲከደን ከንፈር ፈገግ ይላል፡፡

  •  አፍ በምራቅ ሲሞላ እንባ ይፈስሳል፡፡

የቤል ፓልሲ በሽታ ለሁለተኛ ወይም ለሦስተኛ ጊዜ ደግሞ መከሠት አልተለመደም፡፡ ሆኖም ከ 7 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ላይ ሊያጋጥም ይችላል። 

 

Share the post

scroll top