Learning materials for your health  Learn

የእንቅርት በሽታ

  • September 13, 2021
  • የጤና እክሎች

እንቅርት በታችኛው አንገት ውስጥ በፊት ለፊት የሚገኝ  እጢ ነው፡፡ የልብን፣ የጡንቻን  እና የምግብ መፈጨት ሥራን  እንዲሁም የአንጎል እና የአጥንት ዕድገትን የሚቆጣጠር ሆርሞኖችን ያመነጫል። በሀገራችን የእንቅርት ችግር 1.2 % ቢሆንም ከግማሽ  በላይ የሚሆነው ታማሚ ግን ይህ ችግር እንዳለበት አያውቅም።

በሴቶች ላይ ለምን ይበዛል?

ይህም የሆነው በሴት ሆርሞን ኤስትሮጅን (estrogen) አማካኝነት ነው። ይህም ኤስትሮጅን የእንቅርት ዕጢ እንዲተልቅ ያደርገዋል።

የእንቅርት  ዕጢን  የሚያተልቀው ምንድንነው?

  • የአዮዲን ንጥረ ነገር እጥረት

  • የእንቅርት ሆርሞን መብዛት

  • የእንቅርት ካንሰር (neoplastic)

  • የእንቅርት መቆጣት 

  • እርግዝና፣ የጉርምስና ዕድሜ

  • አንዳንድ መድኃኒቶች ( amiodarone,lithium) ናቸው።

የእንቅርት ዕጢ (Thyroid nodules) የተለመደ ከመሆኑም በላይ አብዛኛውን ጊዜ ለጤና ጎጂ አይደለም፡፡ ነገር ግን የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያመጣ ይችላል።

  • በአንገት ላይ የግፊት ስሜት

  • የትንፋሽ እጥረት

  • ምግብ ለመዋጥ መቸገር

  • የድምፅ መቀየር፣ ብዙ ጊዜ መጎርነን

  • ይህ ችግር የአለባቸው ሕመም  ሊኖራቸው ስለሚችል ቅርብ የሕክምና ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህም በሕክምና ተቋማት የእንቅርትን ምንነት ለመለየት ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ።

የእንቅርት ሆርሞን መብዛት (Hyperthyroidism)

አንዳንድ ጊዜ የእንቅርት ዕጢ በጣም ብዙ የእንቅርት ሆርሞን እንዲመረት  ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ለሚከተሉት ምልክቶች ይዳርጋል፡፡

  • የስሜት መረበሽ ወይም በቀላሉ መናደድ 

  • እንቅልፍ የማጣት ችግር

  • የድካም ስሜት 

  • ያልታሰበ ክብደት መቀነስ ከምግብ ፍላጎት መጨመር ጋር

  • ፈጣን የልብ ምት

  • መንቀጥቀጥ

  • ሙቀት መሰማት፣ ማላብ

  • የወር አበባ መዛባት፣ ልጅ ለመፀነስ መቸገር

  • የዐይን ኳስ ወደፊት መውጣት እና

  • ቶሎ ቶሎ መፀዳዳት ናቸው።

ምርመራዎቹ ምንድንናቸው?

  • የደም ምርመራ (TSH, T3,T4)

  • የእንቅርት የአልትራሳውንድ

  • የእንቅርት ዕጢ ምስል (Thyroid scan)

  • ኤፍ. ኤን.ኤ (F.N.A.C)

ሕክምናውስ?

ሕክምናው መድኃኒቶችን፣ ቀዶ ጥገናን እና ሬዲዮአክቲቭ አዮዲንን ሊያጠቃልል ይችላል። በአጠቃላይ ሁለት ዓይነት መድኃኒቶች ይሰጣሉ ።

  • ዕጢው የሚያመርተውን ሆርሞን የሚቀንሱ ( anti-thyroid)

  • ምልክቶችን ለመቀነስ የሚረዱ (Beta blockers) 

እነዚህም የእንቅርት ሆርሞን ሚዛን እስኪስተካከል ድረስ ምልክቶችን በመቀነስ የበለጠ ምቾት እንዲኖር ያደርጋሉ።  

  • ሬዲዮአክቲቭ አዮዲን 

መድኃኒቱ የሚወሰደው በሚዋጥ ክኒን ወይም ፈሳሽ መልክ ሲሆን  ዕጢው እንዲጠፋ ያደርጋል። ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ  ሴቶች ይህንን  ሕክምና መጠቀም የለባቸውም፡፡  ምክንያቱም የሕፃኑን የእንቅርት ዕጢ ሊጎዳ ይችላል።  ሕክምናውን የወሰዱ ሴቶችም ለማርገዝ ከመሞከራቸው  በፊት ቢያንስ 6 ወር መጠበቅ አለባቸው።

  • ቀዶ ጥገና 

ሌሎች የሕክምና ምርጫዎች ካልተሳኩ  በቀዶ ጥገና ዕጢው እንዲወጣ ይደረጋል። ነገር ግን በአብዛኛውን ጊዜ ቀዶ ጥገናው ከመደረጉ በፊት የሆርሞኑን መጠን ለማስተካከል እና ምልክቶቹን ለመቆጣጠር  የሚያግዙ በአፍ የሚወሰዱ እንክብሎች ይታዘዛሉ።

የመድኃኒቶቹ መጠን የሚስተካከለው ተከታታይ የደም ምርመራዎችን በማድረግ ስለሆነ ታማሚዎች በመደበኛነት  በጤና ተቋም ክትትል ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ በሬዲዮአክቲቭ አዮዲን  ወይም በቀዶ ጥገና ሕክምና የተደረገላቸው ሰዎች ከሕክምና በኋላ በጣም ትንሽ የእንቅርት ሆርሞን ሊቀራቸው ይችላል፡፡ በዚህም ምክንያት በቀሪው ሕይወታቸው የእንቅርት ሆርሞን ክኒኖች መውሰድ ሊኖርባቸው ይችላል።

የእንቅርት በሽታ ካልታከመስ ምን ያስከትላል?

  • የልብ ምት መዛባትን (atrial fibrillation) ብሎም አልፎ አልፎም የልብ ድካምን ሊያስከትል ይችላል።

የእንቅርት ሆርሞን ማነስ (Hypothyroidism)

መንሥኤው ምንድንነው?

ዋናው መንሥኤ  የአዮዲን እጥረት ሲሆን፤ ነገር ግን ሌሎች መንሥኤዎችም አሉ።

  • የራዲዮአክቲቭ አዮዲን ወይም የእንቅርት ቀዶ ጥገና 

  • መድኃኒቶች (antithyroid)

  • ሌሎች የእንቅርት በሽታዎች (thyroiditis)

የእንቅርት ሆርሞን ማነስ ምልክቶች ምንድናቸው?

  • የድካም ስሜት

  • ዐቅም ማነስ

  • ሰውነት መብረድ፣ ቆዳ መድረቅ

  • የምግብ ፍላጎት ሳይጨምር ክብደት መጨመር 

  • ሻካራ ቀጭን ፀጉር ማብቀል፣ ፀጉር መነቃቀል

  • የሆድ ድርቀት

  • የወር አበባ መዛባት እና ለመፀነስ መቸገር ናቸው።

አማራጭ ምርመራዎች

  • የደም ምርመራ (TSH, T3, T4) 

  • ከአስፈለገም ሌሎች  እንደ አልትራሳውንድ ያሉ ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ።

ሕክምና

ሕክምናው በየቀኑ የእንቅርት ሆርሞን ክኒኖችን መውሰድ ያካትታል፡፡ ክኒኖቹን ለተወሰኑ ሳምንታት ከተወሰዱ በኃላ ደም ይመረመርና የመድኃኒቱ መጠን እንዲስተካከል ይደረጋል፡፡ 

ካልታከመ ምን ሊያስከትል ይችላል?

  • ልብ ሊያዳክም እና ሊያዘገይ ይችላል፡፡

  • በአካል እንቅስቃሴ ወቅት  ትንፋሽ  ማጠር ሊያመጣ ይችላል።

  • ቁርጭምጭሚት  ላይ እብጠት (ፈሳሽ መያዝ) ሊኖር ይችላል።

  • የደም ግፊትና እና ኮሌስትሮልን ከፍ በማድረግ በልብ ድካም የመያዝ ዕድልን ይጨምራል፡፡

የታይሮይድ ሆርሞን እንክብል መድኃኒቶች መጠንን  ከሐኪሙ ትእዛዝ በስተቀር  መጨመርም ሆነ መቀነስ በጭራሽ አይገባም። ከመጠን በላይ የታይሮይድ ሆርሞን መውሰድ የልብ ምት ችግርን ያስከትላል፡፡ አልፎ ተርፎም አጥንቶችን ሊጎዳ ይችላል።

የእንቅርት ካንሰር

የእንቅርት ካንሰር እንዴት ይከሠታል? 

የእንቅርት ካንሰር የሚከሠተው በእንቅርት ውስጥ ያሉት መደበኛ ሕዋሳት ወደ ያልተለመዱ ሕዋሳት ሲቀየሩ እና ከቁጥጥር ውጭ ሲያድጉ ነው። በዓለማችን ላይ ከ 100,000 ሺሕ ሰዎች 3.7ቱ በዚህ ይጠቃሉ።

ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በሦስት እጥፍ የመያዝ ዕድላቸው ይጨምራል።

የሚያጋልጡ ሁኔታዎች

  • ለጨረር መጋለጥ

  • የአዮዲን እጥረት

  • የነበረ የእንቅርት ችግር 

  • ተመሳሳይ የቤተሰብ ሕመም ከአለ

  • ሴቶች ላይ ይበዛል

ምልክቶቹስ ምንድናቸው?

  •  ሕመም የሌለው የእንቅርት ዕጢ ዕድገት

  •  የድምፅ ለውጥ መኖር

  •  ምግብ ለመዋጥ መቸገር

  •  በአንገት አካባቢ ሌላ እባጭ ወይም ንፍፊት መውጣት

  •  ክብደት መቀነስ፣ ድካም

ምርመራዎቹ ምን ምን ያካትታሉ?

  • የደም ምርመራ (TFT)

  • አልትራሳውንድ

  • የአንገትና የደረት ሲቲ ስካን

  • በተጨማሪም ከእጢው ናሙና ይወሰድና ምርመራ ይደረጋል፡፡

የእንቅርት (ታይሮይድ) ካንሰር እንዴት ይታከማል?

የሕክምናው ዓይነት የሚወሰነው በካንሰሩ ዓይነት፣ በደረጃው እና በጤንነት ሁኔታ ሁኔታ  ላይ ነው።

  የሕክምና አማራጮች

  • ቀዶ ጥገና

  • ራዲዮ አክቲቭ አዮዲን

  • የጨረር ሕክምና እና

  • ኬሞቴራፒ ናቸው።

ከእንቅርት ካንሰር ሕክምናው በኋላ ምን መደረግ አለበት?

ከሕክምናው በኋላ መደበኛ የክትትል ጊዜ እንዲኖር ያስፈልጋል። በክትትሉም ጊዜ የደም  እና የእንቅርት ምስል ምርመራዎች ይደረጋሉ። በዚህም መሠረት የጤና ባለሙያው ካንሰሩ ተመልሶ ስለመምጣቱ ክትትል እንዲያደርግ ይረዳዋል። ስለአሚያጋጠሙ ማናቸውም የጎንዮሽ ጉዳቶች ወይም ችግሮች ከጤና ባለሙያው ጋር ለመነጋገርም ይረዳል።

የመድኃኒት ለውጦችና የደም ምርመራዎች መደረግ ስለአለባቸው ነፍሰ ጡር እናቶች በጊዜ ቅድመ ወሊድ ክትትልን ቢጀምሩ የተሻለ ይሆናል።

በተጨማሪ መደረግ የአለባቸው ነገሮች

  • የሕክምና ክትትልን በአግባቡ ማድረግ

  • ሕክምና በሚሰጥበት ጊዜ ጥያቄ ከአለ መጠየቅ

  • ያለጤና ባለሙያ ፍቃድ በራስ ተነሣሽነት መድኃኒት ለመቀየር አለመሞከር ናቸው።

  • በአጠቃላይ የእንቅርት ዕጢ  እንዳለብዎት ከተጠራጠሩ ወይም አንገትዎ ላይ እብጠት ከአለ የጤና ባለሙያን ማማከር አስፈላጊ እና ጠቃሚ ይሆናል።

ከእንቅርት ቀዶ ጥገና በኋላ ምን ሊያጋጥም ይችላል?

  • ታካሚው ከቀዶ ጥገናው በኋላ ሙሉ በሙሉ ንቁ ሲሆን ከማገገሚያ ክፍል  ወጥቶ ቀድሞ ወደ ነበረበት የሆስፒታል መኝታ ክፍል ይወሰዳል፡፡

  • ከቀዶ ጥገናው በኋላ አንዳንድ ጊዜ  በአንገት  ውስጥ በተሰፋው ቀዳዳ ሥር ቀጠን ያለ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ሊቀር ይችላል። ይህ የፍሳሽ ማስወገጃ አብዛኛውን ጊዜ ቀዶ ጥገናው ከተደረገ በነጋታው ይወገዳል፡፡

  • ከቀዶ ጥገናው በኋላ እንደተለመደው መብላት እና መጠጣት ይቻላል፡፡ 

  • በቀዶ ጥገናው ዓይነት ላይ በመመርኮዝ  የጤና ባለሙያው ታካሚው/ዋ መቼ ወደቤት መሔድ እንዳለባቸው ይወስናል።

  • ወደ ቤት ከሔዱ በኋላ ብዙውን ጊዜ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለስ ይችላሉ፡፡  ነገር ግን  ቢያንስ ለ10 - 15 ቀናት ድረስ ከባድ ዕቃዎችን ባያነሡ  ወይም ከባድ ስፖርቶችን ባይሠሩ ይመከራል። 

  • የቀዶ ጥገናው ጠባሳ ወይም ምልክቱ ለመደብዘዝ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ሊወስድ ይችላል ፡፡

ከእንቅርት ቀዶ ጥገና በኋላ ምን ዓይነት ችግር ሊያጋጥም ይችላል?

  • የጉሮሮ ነርቭ  ጉዳት እና የድምፅ ለውጥ (የድምፅ ኃይል መቀነስ) 

እነዚህ ምልክቶች ብዙውን ጊዜ ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ ናቸው፡፡ በቀዶ ጥገናው ወቅት ወይም የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ በሚገባበት ጊዜ  በአየር ቧንቧ አካባቢ የሚገኙ የጉሮሮ ነርቮች መቆጣት ምክንያት ሊከሠት ይችላል።  

  • የጉሮሮ ነርቭ ጉዳቶች

ችግሩ በኦፕሬሽኑ ወቅት ከሆነ የታወቀው የሕክምና ባለሙያዎች የነርቭ ሕክምና ያደርጋሉ። ብዙ ጊዜ የጉሮሮ ነርቭ ጉዳቱ ከቀዶ ጥገና አንድ ወር በኃላ 1.8% ከነበረ ከሦስት ወር በኋላ በመቀነስ 0.5% ይሆናል።

  • የእንቅርት የደም ቧንቧ ሊጎዳ እና የደም መፍሰስ  ሊያጋጥም ይችላል። የተጠራቀመው ደም ብዙ ከሆነ የአየር ቧንቧን በመጫን ትንፋሽ ሊያሳጥር ስለሚችል በ48 ሰዓታት ውስጥ ቁስሉ ተፈቶ ደሙ መወገድ አለበት።

  • የመተንፈሻ አካላት ላይ ጉዳት መድረስ (Tracheomalacia, Laryngeal edema)  - ጉዳቱ ከባድ ከሆነ በሳምባ የሚገባ ቱቦ (Endotracheal intubation) ሊደረግ ይችላል። የመተንፈሻ  አካላት እብጠትን ለመቀነስ መድኃኒቶች (Steroids) ሊታዘዙ ይችላሉ።

የሚከተሉት ችግሮች ምን ያህሉ የእንቅርት ዕጢ በቀዶ ጥገና ተወግዷል በሚለው ላይ ይወሰናሉ።

  • የእንቅርት ሆርሞን እጥረት (Hypothyroidism) - ይህም ከላይ እንደተጠቀሰው  ከቀዶ ጥገና በኋላ ሊያጋጥም ስለሚችል፤ የእንቅርት ሆርሞን እንክብሎችን በመውሰድ የሚስተካከል ነው።

  • የፓራታይሮይድ ሆርሞን እጥረት (Hypoparathyroidism) - የፓራታይሮይድ ዕጢ የሚገኘው በእንቅርት ዕጢ ጀርባ ላይ ሲሆን፤ የእንቅርት ቀዶ ጥገና በሚደረግበት ጊዜ ይህ ዕጢም አብሮ ሊወጣ ይችላል።

የፓራታይሮይድ ዕጢ ሥራው ምንድነው? 

ይህ ዕጢ የፓራታይሮይድ ሆርሞን በማመንጨት የሰውነታችንን ካልሲየም መጠን ይቆጣጠራል። ስለዚህ የዚህ  ሆርሞን እጥረት ከአለ የካልሲየም እጥረት ያጋጥማል ማለት ነው።

ለሕክምናውም የሰውነታችንን ካልሲየም የሚያስተካክል እንክብል ሊታዘዝልን ይችላል።  

የእንቅርት ሆርሞን ቀውስ (Thyrotoxicosis) 

የእንቅርት ሕመምተኛው ለማንኛውም ዓይነት ቀዶ ጥገና በቂ ዝግጅት ከአልተደረገለት የሚከሠት ነው፡፡ ይህ ማለት ከማንኛውም ቀዶ ጥገና አስቀድሞ የእንቅርት ሆርሞን መብዛትን በእንክብል መድኃኒቶች ለመቆጣጠር በአግባቡ አልተሠራም ወይም አልተቻለም ማለት ነው። ስለዚህ በቀዶ ጥገናው ወቅት በሕመምተኛው ላይ ለጤና አስጊ ቀውሶች ይከሠታሉ።

ሕክምናው

ለጤና አስጊ ቀውሶችን ለማከም በጤና ባለሙያዎች ድንገተኛ የሕክምና ርዳታ ይደረጋል።  ሌሎች የቁስል ኢንፌክሽን እና የቁስል ጠባሳ ከእንቅርት ቀዶ ጥገና በኋላ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ናቸው።

 

Share the post

scroll top