Learning materials for your health  Learn

አጠቃላይ የጭንቀት በሽታ

 • May 10, 2022
 • የጤና እክሎች

አጠቃላይ የጭንቀት በሽታ (Generalized anxiety disorder)

 • በሕይወት ስንኖር በአንዳንድ አጋጣሚዎች የተነሣ መጠነኛ የሆነ መጨነቅ ወይም መረበሽ ሊገጥመን ይችላል። ይህ የተለመደ እና ጤናማ ነው። ነገር ግን አጠቃላይ የጭንቀት በሽታ (GAD) የአለባቸው ሰዎች ከእውነታው በራቀ ወይም ከሚገጥማቸው ችግር ጋር በአልተመጣጠነ መልኩ ፍርሃት እና ጭንቀት ይታይባቸዋል።

 •  እነዚህ ሰዎች አብዝተው ስለ ጤና፣ ገንዘብ፣ ቤተሰብ፣ ሥራ ወይም ትምህርት ይጨነቃሉ። መረበሻቸውንም በቀላሉ ማቆም አይችሉም ፡፡

 • አብዛኛውን ጊዜ መካከለኛ ዕድሜ ላይ ያሉትን ሰዎች የሚያጠቃ ሲሆን፤ ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በዚህ በሽታ ይያዛሉ። በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ውስጥ ብቻ ወደ 2 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች የዚህ በሽታ ሰለባ ናቸው።

 • የበሽታው ምልክቶች በተፈጥሮ የመምጣትና የመሔድ ባሕርይ አላቸው። በተጨማሪም እንደ ድባቴ ካለ የአእምሮ ሕመም ጋር አብሮ የመከሠት ዕድሉ የሰፋ ነው።

 • ብዙ ጊዜ ታማሚዎች የዕለት ተዕለት የሕይወት እንቅስቃሴአቸው የጭንቀት እና የፍርሃት ምንጭ ስለሚሆንባቸው፤  ሥራቸውን፣ ትምህርታቸውን  እና ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን እንደወትሮው በአግባቡ ለመከወን ይቸገራሉ።

አንድ ሰው አጠቃላይ የጭንቀት በሽታ ታማሚ ነው የምንለው መቼ ነው?

    ቢያንስ ለ 6 ወራት ያህል አብዛኛዎቹን ምልክቶች ለአብዛኛዎቹ ቀናት የሚያሳይ ከሆነ እና ምልክቶቹ በዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ከሆነ የጭንቀት በሽታ አለ ማለት እንችላለን። 

አጠቃላይ የጭንቀት በሽታ ምልክቶች

- ከመጠን ያለፈ እና የማያቋርጥ ጭንቀት ወይም ውጥረት

- ችግሮችን ከእውነታው በጣም አግዝፎ መመልከት

- መረጋጋት አለመቻል፣  መበሳጨት

- የሰውነት መጨመት ወይም ጡንቻ ኩምትር ማለት (Muscle tension)

- የልብ ምት መጨመር እና የትንፋሽ መፍጠን

- ራስ ምታት፣ ላብ፣ ማቅለሽለሽ

  - ትኩረት የማድረግ ችግር

 • የድካም ስሜት፣ እንቅልፍ ለመተኛት መቸገር

 • በቀላሉ መደናገጥ፣ መንቀጥቀጥ

 • አብዛኛውን ጊዜ አጠቃላይ የጭንቀት በሽታ የአለባቸው ሰዎች ለሌሎች የሥነ ልቦና ሕመሞች የተጋለጡ ናቸው። ይህም በፍርሃት መታወክ (Panic disorder)፣ ፎቢያ፣ ድባቴ፣ ለአደንዛዥ ዕፅ ወይም ለአልኮሆል መጠጥ ችግሮች የተጋለጡ ሊሆኑ ይችላሉ።

አጠቃላይ የጭንቀት በሽታ መንሥኤዎቹ ምንድናቸው ?

 • ትክክለኛ መንሥኤው ባይታወቅም የዘረ መል መዋቅር፣ የአንጎል ኬሚካላዊ አሠራር እና አካባቢያዊ ተጽዕኖዎች ለበሽታው መከሠት የራሳቸውን አስተዋጽዖ ያደርጋሉ ተብሎ ይታመናል።

የዘረ መል መዋቅር (Genetic makeup)

 •  በአንዳንድ ጥናቶች መሠረት በቤተሰብ ተመሳሳይ ሕመም መኖር ሕመሙ በታማሚው ላይ እንዲከሠት ሚና ይኖረዋል ተብሎ ይገመታል።  

የአንጎል ኬሚካላዊ አሠራር (Brain chemistry)

 •   አንዳንድ ጊዜ ስሜትን እና ጭንቀትን የሚቆጣጠረው የአእምሮአችን ክፍል የአሠራር ችግር ከገጠመው ወይም የነርቭ ኬሚካል (neurotransmitters) ላይ ለውጦች ከተከሠቱ ለዚህ ሕመም ታጋላጭ ልንሆን እንችላለን።

አካባቢያዊ ተጽዕኖዎች

 •  ሰዎች ከዚህ በፊት ለጥቃት (Abuse) ተጋልጠው ከነበረ፣ የቤተሰብ አስተዳደጋችን ወይም አንዳንድ የሕይወት አጋጣሚዎች፤ ለምሳሌ ሞት፣ ፍቺ፣ ሥራ ወይም ትምህርት ቤትን መቀየር ያሉ  አስጨናቂ ሁኔታዎች ለዚህ በሽታ ሊያጋልጡን ይችላሉ።

 • በተጨማሪም ሱስ የሚያስይዙ ንጥረ ነገሮችን፤ (አልኮሆል መጠጥ፣ ካፌይን እና ኒኮቲን ጨምሮ) መጠቀም ወይም የእነዚህ ሱሰኛ ሆነው መጠቀሙን ሲያቆሙ በሽታውን ሊያባብሰው ይችላል፡፡

አጠቃላይ የጭንቀት በሽታ ምርመራ

 • የሥነ አእምሮ ሐኪሞች በሽታውን ለማግኘት ይረዳቸው ዘንድ ስለ አእምሮ ሕመም ምልክቶች፣ በሕይወት ላይ  ስለአመጡት ተጽዕኖ እና ስለሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በመጠየቅ ስለ ሕመሙ ለመረዳት ይሞክራሉ። እንዲሁም ምልክቶቹን ከሌላ በሽታ ለመለየት የደም ምርመራዎችን ሊያዝዙ ይችላሉ።  

 ሕክምናውስ ምንድነው?

ለአጠቃላይ የጭንቀት በሽታ  የሚደረግ ሕክምና ብዙውን ጊዜ  የሚከተሉትን ያካተተ ይሆናል።

 • መድኃኒቶች

 • የግንዛቤ ባሕርይ ሕክምና (Cognitive behavioral therapy) እና

 • የቤት ውስጥ ሕክምናዎች

የግንዛቤ ባሕርይ ሕክምና (Cognitive behavioral therapy)

 • በዚህ ሕክምና ወቅት ታማሚው ወደ ጭንቀት የሚመሩትን የአስተሳሰብ ዘይቤዎቹን እና ባሕርያቱን ለመገንዘብ እና ለመለወጥ እንዲችል ተደርጎ ይማራል። ይህ ዓይነቱ ሕክምና ለአልተገባ ጭንቀት የሚዳርገውን የተዛባ አስተሳሰብን ለመቀየር ይረዳል፡፡

 • በተጨማሪም ተመሳሳይ ችግር በአለባቸውን ሰዎች ላይ የሚሠሩ ድጋፍ ሰጪ ቡድኖች ውስጥ በመቀላቀል ልምድን መጋራትም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

  የመድኃኒት ሕክምና

የመድኃኒት ሕክምና በሽታውን መፈወስ አይችልም። ነገር ግን  ምልክቶቹን ለማስታገስ ይረዳል።

 • ቤንዞዲያዛፔን (Benzodiazepines)

 • እነዚህ መድኃኒቶች ለአጭር ጊዜ የሚሰጡ ሲሆን የጭንቀት ስሜትን  እና ምልክቶቹን ለማስታገስ  የሚረዱ ናቸው።

 • የጎንዮሽ ጉዳታቸው ምንድነው?  

 • ለረጅም ጊዜ ከተጠቀምናቸው ሱስ ሊያስይዙ ይችላሉ፡፡  

 • የማስታወስ ችሎታንና እና ትኩረትን ሊቀንሱ ይችላሉ፡፡

 • ከአልኮሆል መጠጥ እና ከአንዳንድ ተመሳሳይ ውጤት ከአላቸው መድኃኒቶች ጋር ሲቀላቀሉ አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ።

 • የፀረ ድባቴ መድኃኒቶች (Antidepressants)

 • እነዚህ መድኃኒቶች አጠቃላይ የጭንቀት በሽታን  ረዘም ላለ ጊዜ ለማከም ያገለግላሉ፡፡  ለረጅም ጊዜ ሕክምና የመድኃኒቶቹ ደኅንነት የተሻለ ቢሆንም ውጤት ለማሳየት ግን ጥቂት ሳምንታት ሊወስድባቸው ይችላል።

የመድኃኒቶቹ የተለመዱ የጎንዮሽ ጉዳቶች

 • እንቅልፍ መብዛት

 • ክብደትን መጨመር  

 • ማቅለሽለሽ እና የወሲብ ችግሮች ናቸው ፡፡

የቤት ውስጥ ሕክምናዎች

 • የአካል ብቃት እንቅስቃሴ

 • አየር በደንብ እያስገቡ በማስወጣት (Deep breathing) መተንፈስ

 • ጤናማ አመጋገብ

 • በቂ እንቅልፍ ማግኘት

 •  ካፊይን ማስወገድ (ቡና፣ ቼኮሌት፣)

 • አልኮሆል መጠጥና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆችን ማስወገድ

 • ተመስጦ ማድረግ (Meditation)

 • ታማሚዎ ከላይ የተጠቀሱትን ሕክምናዎች በአግባቡ ከወሰዱ አብዛኛውን ጊዜ ጥሩ የጤና መሻሻል ያሳያሉ።

አጠቃላይ የጭንቀት በሽታን እንዴት መከላከል ይቻላል?

 • እነዚህን ችግሮች ሙሉ ለሙሉ እንዳይከሠቱ ማድረግ ባይቻልም፤ የሚከተሉትን በማድረግ ግን ምልክቶቹን መቆጣጠር ወይም መቀነስ ይቻላል።

  • አሰቃቂ ወይም የሚረብሹ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ሁኔታውን ለመሸሽ ከመሞከር ይልቅ  ምክክርን (Counselling) እና ድጋፍን ማግኘት የተሻለ ነው፡፡

  • ጤናማ  እና ንቁ የአኗኗር ዘይቤን መምራት፡፡

  • ማኅበራዊ ሕይወትን ማጎልበት

  • ከወትሮ የተለየ የመጨነቅ ስሜት ሲኖር ዕረፍት ማድረግ፤ ከሌሎች ጋር መወያየት፡፡

  • ስለአለፈው ነገር አለመጨነቅ፤ ያለፈውን መተው

  • የሥነ አእምሮ ሕክምና ላይ ከሆኑ ሕክምናውን በአግባቡ መከታተል እና

  • መድኃኒቶችን ያለ ሐኪም ትእዛዝ አለመውሰድ ናቸው።   

 


 

Share the post

scroll top