Learning materials for your health  Learn

ጭርት (Ringworm)

  • March 13, 2023
  • የጤና እክሎች

ጭርት (Ringworm) 

ጭርት በፈንገስ (fungus) ምክንያት የሚመጣ በቆዳ ላይ የሚከሠት የኢንፌክሽን ዓይነት ነው። 

መገለጫውም ክብ የሆነ ዳር ዳሩ ቀይ እና መሐሉ የዳነ የሚመስል ሲሆን የማሳከክ ስሜት ሊኖረው ይችላል።

ጭርት ከአንዱ ሰው ወደ ሌላ ሰው በቆዳ ለቆዳ ንክኪ በቀላሉ ይተላለፋል።

 

 ምልክቶቹ 

 

ጭርት ቅርፊታማና ጠፍጣፋ ሲሆን አንዳንዴ ቀላ ያለ እና የሚያሳከክ ቁሰለት፣ ክብ ሆኖ ጠርዝ ጠርዙ ቀይ መልክ የሚኖረው እና ቀስ በቀስ የሚሰፋ የቆዳ ላይ ሕመም ነው።

 

የመተላለፊያ መንገዶች

 

  • ከሰው ወደ ሰው 

  • ከእንሰሳት ወደ ሰው፡- ለምሳሌ፣ ከድመት፣ ከውሻ አንዳንዴም ከላም ሊሆን ይችላል፡፡ 

  • ከዕቃ ወደ ሰው፡- የጭርት በሽታ ያለበት ሰው ወይንም እንስሳ  በጭርት በተጠቃ ቆዳው የነካቸውን ዕቃዎች መንካት። ለምሳሌ፤ ፎጣ፣ ልብስ፣ አንሶላ/ አልጋ ልብስ፣ ማበጠሪያ እና የመሳሰሉት፡፡ 

  • ከአፈር ወደ ሰው፡-  ብዙ ጊዜም ባይሆን አንዳንዴ ከተበከለ አፈር ወደ ሰው ሊተላለፍ ይችላል።



 

በጭርት በሽታ የመያዝ ዕድልን የሚጨምሩ ነገሮች

 

  • ከ15 ዓመት ዕድሜ በታች በአሉ ሕፃናት ላይ 

  • እርጥበታማ፣ ሙቀት ያለበት እና በተፋፈገ ቦታ የሚኖሩ ሰዎች

  • በጣም ጥብቅ ያለ እና አየር የማያስገባ ልብስ ማዘውተር

  • የጭርት በሸታ ከአለበት ሰው ጋር አልባሳት፣ አንሶላ እና ፎጣ በጋራ መጠቀም 

  • በጭርት ከተያዘ ሰው ወይንም እንስሳ ጋር ንክኪ መኖር

  • የሰውነት በሽታ የመከላከል ሥርዓትን የሚያዳክሙ ሕመሞች፤ ለምሳሌ የስኳር ሕመም፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ

  • በጣም ደረቅ ቆዳ (xerosis)

                                                                                  

 ወደ ሐኪም ቤት መሄድ የሚያስፈልገው መቼ ነው?               

በሽታው ከሁለት ሳምንት በላይ ከቆየና የማይድን ከሆነ፣ እንዲሁም እየተስፋፋ ከመጣ 


 

ጭርትን እንዴት መከላከል እንችላለን?

           

  • የግል እና የአካባቢን ንጽሕናን መጠበቅ

  • እርጥበትን ማስወገድ፣ ከታጠቡ በኋላ በንጹሕ ፎጣ መጥረግ እና ማድረቅ

  • በጣም ጠባብና ሰውነትን የሚያጣብቁ ልብሶችን አለማዘውተር

  • የግል መገልገያ ዕቃዎችን በጋራ አለመጠቀም 

  • የታመሙ እንስሳትን አለመቅረብ

        

ጭርት እንዴት ይታከማል?

 

  • የሚቀቡ ፀረ ፈንገስ (antifungals)  ክሬሞች፤  ለምሳሌ

 ኬቶኮናዞል (ketoconazole)

 ተርቢናፊን (Terbinafine) 

ሚኮናዞል (miconazole) እና የመሳሰሉት ናቸው። 

 

  • ፀረ ፈንገስ ክሬሞች ተጠቅሞ የመሻል ምልክት ከአልታየ በአፍ የሚወሰዱ ፀረ ፈንገስ መድኃኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ።

 

ጭርት የሚድን በሽታ ነው፡፡ ነገር ግን በድጋሜ እንዳይመጣ በሐኪም የታዘዘው መድኃኒት በሥርዓት መወሰድ አለበት።

         
           

 

Share the post

scroll top