Learning materials for your health  Learn

ለምፅ (vitiligo)

  • March 20, 2023
  • የጤና እክሎች

 ለምጽ (vitiligo)

ለምጽ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ የቆዳ ቀለም እንዲነጣ የሚያደርግ በሽታ ነው፡፡ በዚህ በሽታ የተጠቃው የአካል ክፍልም በጊዜ ሂደት ቀስ በቀስ ስፋቱን እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይህ እክል ከውጭኛው ቆዳ በተጨማሪም ፀጉር እና የአፍ የውስጥ ክፍልን ያጠቃል፡፡

በመደበኛነት የፀጉር እና የቆዳ ቀለም የሚወሰነው ሜላኒን (Melanin) በሚባል ንጥረ ነገር ነው፡፡ ለምጽ በአለባቸው ሰዎች ላይ ይህን ሜላኒን (Melanin) የሚባለውን ንጥረ ነገር የሚያመርቱ ሕዋሶች (melanocytes) በተገቢው እየሠሩ አይደለም ወይም ከእነ ጭራሹ የሉም ማለት ነው፡፡

 ለምጽ ሁሉንም የቆዳ ዓይነቶች ያጠቃል፡፡ ነገር ግን ጥቁር ቆዳ በአላቸው ሰዎች ላይ የበለጠ በግልፅ ይታያል፡፡ በሽታው ለሕይወት አስጊ ወይም ተላላፊ አይደለም፡፡ ለምጽ በማንኛውም ዕድሜ ክልል ውስጥ ሊጀምር ይችላል፡፡ ሆኖም ብዙውን ጊዜ  ከ30 ዓመት ዕድሜ በፊት ይከሠታል ፡፡

ለለምጽ የሚደረግ ሕክምና የተጎዳውን ቆዳ ቀለሙን እንዲመልስ ይረዳል፡፡ ነገር ግን የቆዳ ቀለም መንጣትን ወይም እንደገና መከሠትን አይከላከልም ፡፡

የለምጽ ምልክቶች

 

  • የቆዳ መንጣት ብዙውን ጊዜ በእጆች፣ በፊት፣ በአፍ ዙሪያ እና በብልት አካባቢ ይጀምራል

  • የጸጉር፣ የቅንድብ፣ የሽፋሽፍት ወይም የጺም መሸበት

  • በአፍ እና በአፍንጫ ውስጠኛው ክፍል ያሉ ሕብረ ሕዋሳት (mucus membrane) ቀለም መንጣት

  • ለምጽ ብዙ ጊዜ ሕመም የለውም፡፡  ነገር ግን በፀሐይ ቃጠሎ ጊዜ ሕመም ሊኖረው ይችላል ።

  • ማሳከክም የለውም፡፡ 

 

የለምጽ ዓይነቶች

ለምጽ በአጠቃው የሰውነት ክፍል ላይ በመመርኮዝ የተለያዩ የለምጽ ዓይነቶች ይጠቀሳሉ፡፡

  •  አጠቃላይ ለምጽ (generalized vitiligo) ይህ  በብዛት የተለመደው የለምጽ  ዓይነት ነው፡፡ ሁሉንም ባይባልም አብዛኛውን የቆዳ ክፍል ያጠቃል፡፡  በተጓዳኝ ያሉ የአካል ክፍሎች በተመሳሳይ ሁኔታ በዚህ እክል የቀለም መንጣት ያጋጥማቸዋል፡፡

  • ከፊል ለምጽ (segmental vitiligo) አንዱን  የሰውነት ጎን (ክፍል) ብቻ የሚያጠቃ የለምጽ ዓይነት ነው፡፡ በለጋ ዕድሜ ጀምሮ ለ 1 ወይም ለ 2 ዓመት ከቀጠለ በኋላ መስፋፋቱን ያቆማል።  

  • የ ሕብረ ሕዋሳት ለምጽ (mucosal) ይህ የ አፍ፣ አፍንጫ እና የመራቢያ የውስጠኛውን አካል ብቻ የሚያጠቃ  የለምጽ ዓይነት ነው።

  • ውስን ለምጽ (focal vitiligo) አንድ ወይም ጥቂት የሰውነት ክፍሎችን ብቻ  የሚያጠቃ የለምጽ ዓይነት ነው።

  • ፊት እና እጆች ብቻ የሚያጠቃ የለምጽ ዓይነት (acrofacial vitiligo) ይባላል።

  • ሁለንተናዊ ለምጽ (universal vitiligo) ከሞላ ጎደል በሁሉም የቆዳ ንጣፎች ላይ የቀለም መቀየር ያስከትላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ለምጽ ብዙ ጊዜ የተለመደ አይደለም።


 

ወደ ጤና ተቋም መሄድ የሚያስፈልገው መቼ ነው?

የቆዳ፣ የፀጉር ወይም የአፍ እና አፍንጫ ውስጠኛ ክፍል ቀለማቸውን እያጡ ከመጡ ወደ ጤና ተቋም ሄዶ መታየት አስፈላጊ ነው። ለምጽ ፈውስ ባይኖረውም፤ መባባስን እና መስፋፋትን የሚቀንሱ ወይም የቆዳ ቀለምን ወደነበረበት ለመመለስ የሚረዱ ሕክምናዎች አሉ።


 

የለምጽ መንሥኤዎች ምንድናቸው?

 

  • የሰውነታችን በሽታ የመከላከል ሥርዓት የራሳችንን ቆዳ ሜላኒን የሚያመርቱ ሕዋሶች (melanocytes) በሚያጠቃበት ወቅት (autoimmune disorder)

  • በዘር ሊከሠት ይችላል፡፡

 

  • እንደ ጭንቀት፣ ለከባድ ፀሐይ ጨረር መጋለጥ ወይም የቆዳ ቁስለት የመሳሰሉ ነገሮች የለምጽ ቀስቃሾች ናቸው።

 

  የለምጽ በሽታ በዘር ይተላለፋል?  

የለምጽ በሽታ በዘር አይተላለፍም፡፡ ነገር ግን ወደ 30% ተጠቂዎች ቢያንስ አንድ የቅርብ ዘመድ የለምጽ በሽታ አለበት።

  • የለምጽ መዘዞች

ለምጽ የአለባቸው ሰዎች ለሚከተሉት እክሎች የበለጠ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

  • ማኅበራዊ ወይም ሥነ ልቦናዊ ጭንቀት

  • በፀሐይ ጨረር የቆዳ መጎዳት

  • የዐይን ችግሮች፤ ሆኖም ግን እይታን አያሳጣም 

  • የመስማት ችግር

  • ሌሎች በሰውነታችን በሽታን የመከላከል ሥርዓት የተነሣ የራሳችንን አካል ሲያጠቁ የሚከሠቱ በሽታዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ የ ስኳር፣  የእንቅርት፣ የደም ማነስ እና የመሳሰሉት። 

 

ለለምጽ የሚደረግ ምርመራ

  • ሐኪም ስለ ሕክምና ታሪክ ይጠይቃል፤ ቆዳዎን ይመረምራል፡፡ 

  •  የቆዳ ሐኪሙ የጨረር ምርመራ (wood’s lamp) ሊያደርግም ይችላል፡፡

  •  አስፈላጊ ከሆነ የቆዳ ናሙና እና የደም ምርመራዎች ሊታዘዙ ይችላሉ።

 

የለምጽ ሕክምና

የሕክምናው አማራጭ፤ በዕድሜ፣ ቆዳ ምን ያህል እንደተጎዳ? እና የትኞቹን የሰውነት ክፍሎች እንደአካተተ? በሽታው በምን ያህል ፍጥነት እየተባባሰ እንደሆነ? እና በሕይወት ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሆነ? ከግምት በማስገባት ይወሰናል፡፡

ውጤቶቹ ቢለያዩም እና ሊተነበዩ የማይችሉ ቢሆኑም መድኃኒቶችን እና ብርሃንን መሠረት የአደረጉ ሕክምናዎች የቆዳ ቀለምን ለማደስ ይረዳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ሕክምናዎች ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶች አላቸው፡፡ ስለዚህ በመጀመሪያ የታካሚውን የቆዳ ቀለም ምርት ወይም መዋቢያ ሜካፕ በመጠቀም የቆዳውን መልክ ለመለወጥ ሙከራ እንዲደረግ ሐኪሙ ሊጠቁም  ይችላል፡፡

በመድኃኒት፣ በብርሃን ወይም በቀዶ ጥገና መታከም ከአስፈለገ ውጤቱ እስኪታይ ወራት ሊፈጅ ይችላል። በተጨማሪም ለታካሚው የሚስማማ የሕክምና ዘዴ ከማመገኘቱ በፊት ከአንድ በላይ ሕክምና መሞከር ግድ ሊሆን ይችላል።

ምንም እንኳን ሕክምናው ለተወሰነ ጊዜ ስኬታማ ቢሆንም ውጤቱ ላይቆይ ይችላል፤ ወይም አዳዲስ የቆዳ መንጣቶች ሊታዩ ይችላሉ። ማገርሸትን ለመከላከል የሚረዳ ቋሚ ሕክምና ማድረግ ሊያስፈልግም ይችላል።

መድኃኒቶች

የለምጽ ሂደትን ሊያስቆም የሚችል መድኃኒት የለም!

ግን አንዳንድ መድኃኒቶች በብቸኝነት ወይም ከብርሃን ሕክምና ጋር በጥምር ጥቅም ላይ ሲውሉ የቆዳ ቀለሞች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንዲመለሱ ይረዳሉ፡፡


 

  • ቆዳን መልሶ ማጥቆር  (Repigmentation therapy)  

    

  • የኮርቲኮስቴሮይድ ክሬም (corticosteroid creams) ውጤቱን ለማየት ወራት ቢፈጅም፤ የለምጽ በሽታ እንደተከሠተ ሳይዘገዩ ሕክምናውን መጀመር የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል። የቆዳ መሳሳት እና ሰንበሮችን ማውጣት እንደ ጎንዮሽ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በፍጥነት እየጨመረ ለሚገኝ የለምጽ በሽታ በአፍ ወይም በመርፌ መልክ የሚሰጥ ኮርቲኮስቴሮይድ መድኃኒት ሊታዘዝ ይችላል።

  • Calcineurin inhibitor ointments (tacrolimus  or pimecrolimus) ያሉ መድኃኒቶች የሰውነታችንን በሽታ የመከላከል ሥርዐት በማስተካከል ውስን ቦታ ላይ ሳይስፋፉ ላሉ ለምጽ ለአጠማቸው የቆዳ ክፍሎች በተለይም ለፊት እና አንገት ላይ ማሻሻልን ያሳያል። ሆኖም የአሜሪካው የምግብ እና መድኃኒት ቁጥጥር በዚህ መድኃኒት እና በቆዳ ካንሰር መካከል ግንኙነት እንዳለ አሳስቧል።

 

  • የብርሃን ሕክምና

 

  • በጠባብ ሞገድ አልትራቫዮሌት ቢ (narrow band UVB) ብርሃን የለምጽ መባባስን ያስቆማል። ይህን ሕክምና በሳምንት ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ ማድረግ ይገባል፡፡ ውጤቱም ከአንድ እስከ ሦስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ መታየት ይጀምራል። የሕክምናው የጎንዮስ ጉዳቶች የቆዳ መቅላት፣ ማሳከክ እና ማቃጠልን ያካትታሉ።

 

  • የቀረውን የቆዳ ቀለም ማንጣት (depigmentation therapy)

 

  • ይህ ሕክምና የተስፋፋ ለምጽ ከአለ እና ሌሎች የሕክምና አማራጮች ውጤታማ ከአልሆኑ በለምጽ የአልተጠቃውን የቆዳ ክፍል በማንጣት የቆዳ ቀለም ወጥ እንዲሆን የሚያደርግ የሕክምና ዓይነት ነው። ሕክምናው በቀን አንድ ወይም ሁለት ጊዜ የአለማቋረጥ ለዘጠኝ ወር ወይም ከዚያ በላይ ይደረጋል። የጎንዮሽ ጉዳቶቹ የቆዳ መቅላት፣ ማበጥ፣ ማሳከክ እና መድረቅን ሊያካትቱ ይችላሉ፡፡

 

  • ቀዶ ጥገና (surgery) 

በብርሃን ሕክምና እና በመድኃኒቶች ለአላገገሙ ወይም የተሻለ ለውጥ ለአላመጡ   የለምጽ በሽተኞች የተለያዩ የቀዶ ሕክምና አማራጮች አሉ።

  • ስኪን ግራፍት (skin graft) የተባለ የ ቀዶ ጥገና ዓይነት ሲሆን፤ ከአልተጎዳው የሰውነት ቆዳ ወስዶ የተጎዳው ቦታ ጋር በማድረግ መሸፈን ማለት ነው።  

  • ማይክሮ ፒግመንቴሽን (Micropigmentation) የከንፈር አካባቢ ንቅሳት ሲሆን በ ሕክምና አልድን ለአለ ለምጽ ይሰጣል።

 

የአኗኗር ዘይቤ ለውጦች

  • ቆዳን ከፀሐይ ጨረር መከላከል። ቢያንስ ከ 30 በላይ SPF የአላቸውን፣ ሁለቱንም የፀሐይ ጨረሮች (UVA,UVB) የሚያግድ የፀሐይ ጨረር መከላከያ ቅባቶች መጠቀም። ከፍተኛ ፀሐይ ባለበት ስፍራ ጃንጥላ ወይም ኮፍያ መጠቀም።

  • የተጎዳውን የቆዳ ክፍል ለመሸፈን ከተፈለገ ሜክአፕ መጠቀም ይቻላል። ለታካሚው የሚስማማውን የውበት መጠበቂያ ምርት ለማረጋገጥ ባለሙያ ማማከር ተገቢ ነው። 

 

Share the post

scroll top