Learning materials for your health  Learn

በጨቅላ ሕፃናት ላይ የሚከሠት የዐይን በሽታ (Ophthalmia neonatorum)

  • March 29, 2023
  • የጤና እክሎች

በጨቅላ ሕፃናት ላይ የሚከሠት የዐይን በሽታ  (Ophthalmia neonatorum)

በተወለዱ በመጀመሪያዎቹ 30 ቀናት ላይ የሚከሠት የጨቅላ ሕፃናት የዐይን ኢንፌክሽን ነው። አብዛኞቹ በጤና ተቋማት ውስጥ የሚወለዱ ሕፃናት ይህ የዐይን በሽታ እንዳያጋጥማቸው ሲባል በተወለዱ በሰዓታት ውስጥ የዐይን ጠብታ ይደረግላቸዋል። ይህ በሽታ በሥርዓት ከአልታከመ የዐይን ብርሃን እስከማጥፋት ይደርሳል። 

የበሽታው መንሥኤዎች

      የጨቅላ ሕፃናት የዐይን በሽታ መንሥኤዎች  

  • ባክቴሪያዎች  በአብዛኛው ጊዜ በጨቅላ ሕፃናት ላይ የዐይን በሽታ ያስከትላሉ፡፡   

  •  ቫይረስ 

  •  ኬሚካሎችም መንሥኤ ሊሆኑ ይችላሉ። 

 

ባክቴሪያዎች

  • ክላሚዲያ ትራኮማቲስ (Chlamydia trachomatis) ይህ ባክቴሪያ  የጨቅላ ሕፃናትን የዐይን በሽታ በማስከተል ቀዳሚ ነው፡፡ በዚህ ባክቴሪያ ከተያዘች እናት የተወለዱ ሕፃናት ከ 25 እስከ 50% የጨቅላ ሕፃናት የዐይን በሽታ የመያዝ ዕድላቸው ይጨምራል። በዚህ ባክቴሪያ የሚመጣው በሽታ ልጁ ከተወለደ ከ 5 ቀን እስከ 12 ቀናት ውስጥ ሊጀምር ይችላል። 

  •  ኒዜሪያ ጎኖሪያ ( Neisseria gonorrhoeae) ይህ ባክቴሪያ በጣም አደገኛ እና ከባድ የሆነ የጨቅላ ሕፃናት የዐይን በሽታ አምጭ ባክቴሪያ  ነው፡፡ በፍጥነት ካልታከመ እይታን እስከማሳጣት ሊደርስ ይችላል። በዚህ ባክቴሪያ የሚመጣው በሽታ ልጁ ከተወለደ በ 24 እስከ 48 ሰዓታት ውስጥ ሊጀምር ይችላል። 

  •  ሌሎች ግራም ፖዘቲቭ (gram-positive organism) እና ኔጌቲቭ ባቴሪያዎች ( gram-negative organisms)

            ቫይረስ 

  •   ኤች ኤስ ቪ (Herpes simplex virus HSV) ብዙ ጊዜ የጨቅላ ሕፃናት የዐይን በሽታ አያስከትልም፡፡ (<1%) ብዙ ጊዜ ይህ ቫይረስ በሽታውን ሲያስከትል የጠቅላላ የሰውነት የቫይረስ ኢንፌክሽን ያስከተላል። በዚህ ቫይረስ ምክንያት የሚመጣው በሽታ ልጁ ከተወለደ በ 2 ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ ሊከሠት ይችላል።  

በባክቴሪያ ወይም በቫይረስ የሚመጣው የዐይን በሽታ፣ ሕፃናቱ ሲወለዱ በእናታቸው ብልት በኩል በሚወጡበት ጊዜ (በወሊድ ጊዜ) ተሕዋሲያኑ (ባክቴሪያና ቫይረስ) ከእናታቸው ብልት አካባቢ ወደ ሕፃናቱ ፊት (ዐይን) ይሸጋገራሉ።

ለበሽታው የሚያጋልጡ ነገሮች ምንድን ናቸው?

  • እናትዮዋ ከእርግዝና በፊት ወይም በእርግዝና ጊዜ ተገቢ ሕክምና የአልተደረገለት የአባለዘር በሽታ የአለባት ከሆነ። 

  • ምጥ ከመጀመሩ በፊት የሽርት ውሃ መፍሰስ

  • ያለ ጊዜ የተወለዱ ሕፃናት

  • ከ ኤች አይ ቪ ቫይረስ (HIV) ጋር የሚኖሩ እናቶች

  • ልጆች ከተወለዱ በኋላ ቅድመ ሕመም መከላከያ መድኃኒቶችን በአግባቡ አለመስጠት

  • በወሊድ ወቅት በጨቅላ ሕፃናት ላይ የሚከሠት የዐይን ጉዳት

  • ጥንቃቄ የጎደለው የጨቅላ ሕፃናት ክብካቤ

በባክቴሪያና በቫይረስ የሚመጣው የዐይን በሽታ ሕፃኑ በተወለደ በ 5 ቀናት ውስጥ ምልክት ያሳያል፡፡ በኬሚካል (በአንዳንድ መዲኃኒቶች) ምክንያት ከሆነ ደግሞ በሰዓታት ውስጥ ምልክት ሊያሳይ ይችላል።

የበሽታው ምልክቶች

  • የዐይን ፈሳሽ

  • የሕፃኑ የዐይን ቆብ በዐይናር (የዐይን ፈሳሽ) መያያዝና ሕፃኑ ዐይኑን ለመግለጥ መቸገር

  • የዐይን ቆብ ማበጥ

  •  የዐይን ቆብ መቅላትና የመሳሰሉትን ሊያሳይ ይችላል። 

  • ሕክምናውና መከላከያ መንገዶቹ

  • በእርግዝና ጊዜ ወይም ከዚያ በፊት እናቲቱ ላይ የአባለዘር በሽታ ከአለ ተገቢ የሆነ ሕክምና ማድረግ አለባት።

  • ማንኛውም ሕፃን ወዲያው እንደተወለደ በጤና ባለሙያ አማካኝነት የዐይን ጠብታ መቀባት ይኖርበታል። ይህም ከላይ የተገለፀው የዐይን በሽታ በሕፃኑ ላይ እንዳይከሠት ይከላከላል፡፡ ይህን የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ሁሉም እናቶች ሲወልዱ ወደ ጤና ተቋም ሄደው መውለድ አለባቸው።

  • በሽታው በሕፃኑ/ኗ ላይ ከተከሠተ ሕፃኑ ወደ ጤና ተቋም ተወስዶ በጤና ባለሙያ በሚታዘዝ መድኃኒት ሕክምና እንዲያገኝ ማድረግ ያስፈልጋል።

  •  በኬሚካል (አለርጅክ) ምክንያት የሚከሠተው የዐይን ሕመም አብዛኛውን ጊዜ በራሱ ሊድን የሚችል ቢሆንም፤ ባለሙያ ማማከር ግን አስፈላጊ ነው።

 

ሕክምና 

           ሕክምናው በጠብታ መልክ ከሚሰጠው መድኃኒት በተጨማሪ በመርፌ መልክ የሚሰጥ ሲሆን፤ ለተወሰኑ ቀናት ወይ ሳምንታት መድኃኒቱን ወስዶ መጨረስ ይኖርበታል። 

 

Share the post

scroll top