ስርቅታ (Hiccups)
- April 3, 2023
- የጤና እክሎች
ስርቅታ (Hiccups)
ስርቅታ ደረትን ከሆድ የሚለየው ዋና የመተንፈሻ ጡንቻ (Diaphragm) በድንገት ሲኮማተር ይከሠታል፡፡ ይህ የጡንቻ መኮማተር አየር ወደ ውስጥ እንድናስገባ እና የድምፅ ሳጥን እንዲዘጋ ያደርጋል።
በዚህን ጊዜም ”ስርቅ” የሚለው ድምፅ ወይም ስርቅታ ይፈጠራል።
የስርቅታ መንሥኤዎቹ ምንድናቸው?
-
በ 48 ሰዓታት ውስጥ የሚጠፋ ስርቅታን የሚያመጡ መንሥኤዎች የሚከተሉትን ያጠቃልላሉ።
-
በአንድ ጊዜ ከመጠን በላይ ምግብ መመገብ
-
የአልኮሆል መጠጦች ወይም እንደ ኮካ ያሉ ጋዝ ያላቸው ለስላሳ መጠጦች
-
ብዙ አየርን በአፍ በኩል ማስገባት፤ ለምሳሌ ማስቲካ በማኘክ ወይም ከረሜላ በመምጠጥ
-
ድንገተኛ ደስታ ወይም ጭንቀት በሚፈጠርበት ጊዜም ሊመጣ ይችላል፡፡
-
ድንገተኛ የሰውነት ሙቀት መቀየር
በእነዚህ ምክንያት የሚመጣው ስርቅታ አብዛኛውን ጊዜ የሚቆየው ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነው።
ከ 48 ሰዓታት በላይ የሚቆይ ስርቅታን (persistent hiccups) የሚያስከትሉ መንሥኤዎች ምንድናቸው?
አንዳንድ ጊዜ ግን ስርቅታ መሠረታዊ የጤና ችግር ምልክት ሊሆን ይችላል። ይህ ስርቅታ ከሴቶች ይልቅ በወንዶች ላይ የበለጠ የሚከሠት ሲሆን፤ ምክንያቶቹ እንደሚከተሉት ተጠቅሰዋል።
-
የነርቭ ጉዳት ወይም መቆጣት (Phrenic nerve injury)
የመተንፈሻ ጡንቻ እንዲኮማተር በሚያደርጉ ነርቮች ላይ ጉዳትን የሚያደርስ ማንኛውም ዓይነት ሕመም ስርቅታን ሊያመጣ ይችላል።
-
በነርቩ ላይ ቀጥተኛ ጉዳት የሚያደርሱ እና ነርቩ የሚገኝበት አካባቢ ያሉ ሕመሞች
- የአንገት ወይም የሆድ ውስጥ ዕጢ
- የጆሮ ታምቡርን የሚነካ ሕመም
- አንዳንድ የጨጓራ ሕመም (GERD)
- የጉሮሮ ኢንፌክሽን
-
ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓት ችግሮች (Central nervous system disease)
በማዕከላዊው የነርቭ ሥርዓት ውስጥ ዕጢ፣ ኢንፌክሽን ወይም ጉዳት ከደረሰ የሰውነትን መደበኛ የነርቭ ቁጥጥርን ሊያስተጓጉል ይችላል። ስለዚህ የመተንፈሻ ጡንቻ ነርቭ የጡንቻ መኮማተር እና ስርቅታን ሊያመጣ ይችላል።
ለምሳሌ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።
-
የጭንቅላት ኢንፌክሽን (Encephalitis)
-
ማጅራት ገትር ( meningitis)
-
ስትሮክ (stroke) :- የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ ወይም መርጋት የአንጎል ላይ ጉዳት ማድረስ
-
የጭንቅላት ዕጢዎች
-
አንዳንድ ሥር የሰደዱ በሽታዎች ስርቅታን ሊያመጡ ይችላሉ።
- የስኳር በሽታ፣ የኩላሊት በሽታ፣ የሰውነት ንጥረ ነገር መዛባት (Electrolyte imbalance)
-
መድኃኒቶች (Barbiturates,Anesthetics)
ከቀዶ ጥገና ሕክምና በኋላ ስርቅታ ሊከሠት ይችላል?
አንዳንድ ሰዎች ለቀዶ ጥገና ማደንዘዣ ከወሰዱ በኋላ ወይም የሆድ ዕቃ አካላትን የሚያካትቱ ቀዶ ጥገናዎችን ከአደረጉ በኋላ ስርቅታ ሊይዛቸው ይችላል።
ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ስርቅታ የሚከተሉትን ችግሮች ሊያመጣ ይችላሉ፡፡
-
የአመጋገብ መዛባት
-
ለመተኛት መቸገር
-
በንግግር ጊዜ መቸገር
-
ክብደት መቀነስ እና ድካም ሊያስከትል ይችላል፡፡
-
ከቀዶ ጥገና በኋላ ቁስል ቶሎ እንዳይድን ሊያደርግ ይችላል።
የ ስርቅታ ምርመራዎች ምንድናቸው?
የጤና ባለሙያ ስርቅታ ያመጣውን መንሥኤ ለማወቅ የተለያዩ ምርመራዎችን ሊያደርግ ይችላል። ከእነሱም ፦
-
የነርቭ ምርመራ
-
የላቦራቶሪ ደም ምርመራዎች
-
የምስል ምርመራዎች
-
የደረት ራጅ ( chest x ray )
-
ሲቲ ስካን (CT scan )
-
ኤም አር አይ ( MRI)
ስርቅታ ሕክምና አለው?
አብዛኛውን ጊዜ ስርቅታ ያለሕክምና ርዳታ በራሱ ጊዜ ይጠል። ነገር ግን መንሥኤው መሠረታዊ የጤና ችግር ከሆነ እና ስርቅታው ከ 48 ሰዓት በላይ ከቆየ ፤ ወይንም ሕመሙ እንቅልፍን፣ ምግብ መብላትን እና አተነፋፈሳችንን የሚጎዳ ከሆነ ወደ ጤና ባለሙያ ዘንድ መሄድ ያስፈልጋል።
ለሕመሙ የሚደረግ ሕክምና ስርቅታውን ሊያስወግድ ይችላል ፡፡
-
ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ስርቅታ ከአለብዎ የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ ማድረግ ሊረዳዎ ይችላል።
-
ጋዝነት የአላቸውን መጠጦች እና ምግቦችን ማስወገድ
-
በአንድ ጊዜ ትንሽ የምግብ መጠን መመገብ
ከሁለት ቀናት በላይ ለቆየ ስርቅታ የማስታገሻ መድኃኒቶች በጤና ባለሙያዎች ሊታዘዙ ይችላሉ፡፡ እነሱም፤
-
ጋባፔንቲን (Gabapentin)
-
ባክሎፌን (Baclofen)
-
ክሎፕሮማዚን (Chlorpromazine)
ስርቅታን ለማስታገስ የሚከተሉትን የቤት ውስጥ መፍትሔዎች መጠቀም ይችላሉ።
-
በወረቀት ከረጢት መተንፈስ
-
በቀዝቃዛ ውሃ መጉመጥመጥ
-
ትንፋሽን ለጥቂት ሰከንዶች መያዝ
-
ቀዝቃዛ ውሃ ፉት ማለት ናቸው።
-
ስኳር መቃም
-
ደረቅ ዳቦ መብላት
የሕፃናት ስርቅታ
-
በሕፃናት ላይ ስርቅታ እንዴት ሊከሠት ይችላል?
-
ቶሎ ቶሎ እና ብዙ ምግብ መመገብ
-
ቶሎ ቶሎ ብዙ ጡት ወይም ጡጦ መጥባት
-
ሕፃናት የሚያስደስታቸውን ወይም ለየት ያለ ነገር ሲያገኙ
-
የሕፃናት ሙቀት በተለይ ሆድ አካባቢ ያለ ሙቀት በድንገት መቀነስ
-
በሕፃናት ላይ የሚከሠት ስርቅታን በምን ማስቆም እንችላለን?
-
ማስገሳት (burping)
-
የእንጀራ እናት ጡጦ መጠቀም (using pacifier)
-
ዋናው መፍትሔ ግን ወላጆች ስርቅታ ቀላል እንደ ሆነ ልጁ ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ማወቅ፣ ከ 5 - 10 ደቂቃ ዉስጥ እንደሚቆም ማወቅ እና በመረጋጋት ልጃቸውን ማጫወትና ማዝናናት አለባቸው።
በሕፃናት ላይ የሚከሠት ስርቅታን እንዴት መከላከል ይቻላል?
-
ከ ምግብ በኋላ ልጅዎን አስተካክለው በማቀፍ (upright position) ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ማቆየት
-
ሕፃናት ከተመገቡ በኋላ ከበድ ያለ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ መጠንቀቅ። ምግብ ከበሉ በኋላ መጫወት ወይንም መላፋት አይመከርም።
-
ልጅዎን ለማብላት ወይንም ለማጥባት እስኪራብ እና እስኪያለቅስ ድረስ አለመጠበቅ።