ዲ.ኤስ.ኤም.(DSM-5-TR) የተባለው የአእምሮ ሕመሞች መመርመሪያ እና ስታቲስቲካዊ መመሪያ 10 የተወሰኑ የባሕሪ መታወክ ዓይነቶችን ይዘረዝራል፣ እነሱም በተመሳሳይ ባህሪያት ላይ ተመስርተው በሦስት ቡድኖች (Clusters) ይከፈላሉ።
ቡድን ሀ (Cluster A)
ባልተለመዱ እና ለየት ባሉ አስተሳሰቦች እና ባህሪዎች የሚታወቁ የባሕሪ መታወክ ዓይነቶችን ያጠቃልላል። እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ፡
የፓራኖይድ ስብዕና መታወክ (Paranoid Personality Disorder): ምልክቶቹም
- ሌሎችን ያለ በቂ ምክንያት መጠርጠር እና አለመተማመን
- ለሌሎች ምስጢር ለመንገር መፍራት፣ ምክንያቱም መረጃው በኔ ላይ ሊውል ይችላል ብሎ በማሰብ
- ምንም ጉዳት የሌላቸውን ንግግሮች ወይም ሁኔታዎችን እንደ ግል ስድብ ወይም ጥቃት መውሰድ
- ቂም የመያዝ ልማድ መኖር
- ያለ በቂ ምክንያት የትዳር ጓደኛ ወይም የፍቅር አጋር ታማኝ እንዳልሆነ አብዝቶ መጠርጠር
የስኪዞይድ ስብዕና መታወክ (Schizoid Personality Disorder):ምልክቶቹም
- እራሱን ከማህበራዊ ግንኙነቶች ማግለል
- ሁልጊዜም ብቻውን መሆንን ይመርጣል
- ስሜቶችን የሚገልጹበት መንገድ ውስን ነው
- በተለምዶ ደስታ ከሚሰጡ እንቅስቃሴዎች ደስታ አለማግኘት
የስኪዞታይፓል ስብዕና መታወክ (Schizotypal Personality Disorder): ምልክቶቹም
- እንግዳ በሆኑ እምነቶች እና ለየት ባሉ ባህሪያት ይታወቃሉ
- ለየት ያሉ አባበሶች እና አነጋገሮች አሏቸው
- ሰዎች ከኋላቸው የሚያወሩት ስለነሱ እንደሆነ ያስባሉ
- እንደ ቴሌፓቲ (telepathy) እና አጉል እምነቶች (superstitions) ላይ ከሌሎች ሰዎች በበለጠ ያምናሉ እናም ባህሪያቸው በእነዚህ እምነቶች ይወሰናል
- ለሌሎች የማይሰሙ ነገሮችን ይሰማቸዋል ወይም ያስባሉ
ቡድን ለ (Cluster B)
ዋነኛ መገለጫዎቻቸው ድራማዊ እና የማይገመቱ ባህርያት፣ ያልተረጋጉ ስሜቶች እና ግድ የለሽ ድርጊቶችን ናቸው። እዚህ ውስጥ የሚካተቱት የበሽታ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው
አንቲ ሶሻል ስብዕና መታወክ (Antisocial Personality Disorder): ምልክቶቹም
- ለሌሎች ፍላጎትና ስሜት ደንታ የሌለው መሆን
- መዋሸት፣ መስረቅ እና ሌሎችን ለግል ጥቅም መጠቀም
- በተደጋጋሚ ሕግን መጣስ
- የሌሎችን መብት አለማክበርና መጣስ
- አመፀኛ እና ሁከት ፈጣሪ መሆን
- ለራሳቸው ወይም ለሌሎች ደህንነት ደንታ የሌለው መሆን
- ነገሮችን ባለማሰብ እና በግድየለሽነት መሥራት
- በድርጊታቸው ለሌሎች ስለሚደርሰው ጉዳት ጸጸት አለመሰማት
ቦርደርላይን ስብዕና መታወክ (Borderline Personality Disorder):ምልክቶቹም
- ስሜትን ለመቆጣጠር በጣም መቸገር
- ብቻ የመሆን ወይም የመተዉ ከፍተኛ ፍርሃት
- የማያቋርጥ የባዶነት ስሜት መኖር
- ራስን እንደ ደካማ ወይም ያልተረጋጋ አድርጎ ማየት
- ስለራሳቸው ያላቸው አመለካከት ብዙ ጊዜ አሉታዊ ነው
- ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ከፍቅር ወደ ጥላቻ በፍጥነት ሊለዋወጥ ይችላል
- ከሌሎች ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜ ስሜታቸው በድንገት ይለዋወጣል
- ራስን የመጉዳት ወይም ራስን የማጥፋት ዛቻ ያሳያሉ
- ብዙ ጊዜ ቁጡ መሆን
- ግድ የለሽ እና አደገኛ ድርጊቶች ያለማሰብ መፈጸም
ሂስትሪዮኒክ ስብዕና መታወክ (Histrionic Personality Disorder):
- በሁሉም ሁኔታዎች የትኩረት ማዕከል መሆን መፈለግ
- ከመጠን በላይ ስሜታዊ ወይም ድራማዊ መሆን
- ጠንካራ አስተያየት መኖር ግን የሚናገረውን ለመደገፍ በቂ መረጃ ሳይኖረው መናገር
- በሌሎች ሰዎች አስተያየት ወይም ሐሳብ በቀላሉ መመራት
- ስሜቶቹ ውጫዊ እና በፍጥነት የሚቀያየሩ ናቸው።
- ለአካላዊ ገጽታ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት
- ከሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ከትክክለኛው በጣም የጠበቀ እንደሆነ ማመን
ናርሲሲስቲክ ስብዕና መታወክ (Narcissistic Personality Disorder)
- የሌሎችን ስሜት አይረዱም
- ራስን እንደ ልዩ እና ከሌሎች የላቀ አድርጎ ማሰብ
- የኃይል፣ ስኬት እና ውበት ከፍተኛ ምኞቶች መኖር
- የሌሎችን ስሜትና ፍላጎት አለመረዳት
- ስኬቶቻቸውን እና ችሎታቸውን በማጋነን መናገር
- ያለማቋረት ውዳሴ መፈለግ
- ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ መሰማት
- ያለ በቂ ምክንያት ልዩ ሞገስ ወይም ጥቅም መፈለግ
- ሌሎችን ለግል ጥቅም መጠቀም
- በሌሎች ሰዎች ስኬት ይቀናሉ ወይም ሌሎች በእነሱ እንደሚቀኑ ያምናሉ
ቡድን ሓ (Cluster C)
በከፍተኛ ጭንቀትና ፍርሀትን የሚገለጹናቸው። እነዚህም የሚከተሉትን ያካትታሉ
የአቮይዳንት/ የተገለለ ስብዕና መታወክ (Avoidant Personality Disorder)
- ይህ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ዘላቂነት ያለው የበታችነት ስሜትና በሌሎች እንዳይፈረድባቸው ከፍተኛ ፍርሃት አለባቸው።
- ከሰዎች ጋር መገናኘት ቢፈልጉም እንኳ፣ ባለመቀበል ፍርሃት ምክንያት ራሳቸውን ከማኅበራዊ ግንኙነቶች ያገላሉ።
- ለትንሽ ትችት በጣም ስሜታዊ መጎዳት
- በቂ ወይም አስፈላጊ እንዳልሆኑ አድርገው ማሰብ
- ከሌሎች ጋር ግንኙነት የሚጠይቁ ሥራዎችን አለመሥራት
- ከማኅበራዊ ግንኙነት ራሳቸውን ማግለል
- አዲስ ነገር አለመሞከር እና አዲስ ሰዎችን አለመገናኘት
- በማኅበራዊ ሁኔታዎች ውስጥ በጣም ዓይን አፋር መሆን
የዲፔንዳንት/ ጥገኛ ስብዕና መታወክ (Dependent Personality Disorder)
- ከአንድ ሰው ጋር በጣም ይቀራረባሉ እና ያንን ሰው ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ።
- በሌሎች ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ መሆን እና እንክብካቤ መፈለግ
- ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ጋር ታዛዥ እና ተገዢ ይሆናሉ
- ከአንድ ሰው ጋር የመለያየት ፍርሃት አለባቸው
- ብቻውን ሲቀሩ ራሳቸውን መንከባከብ እንደማይችሉ መፍራት
- በራስ ችሎታ ላይ እምነት ማጣት
- ትናንሽ ውሳኔዎችን ለማድረግ እንኳን ከሌሎች ብዙ ምክርና ማጽናኛ መፈለግ
- በራስ መተማመን ማጣት ምክንያት ስራዎችን ለመጀመር ወይም ለማከናወን መቸገር
- ሰዎች አይቀበሉኝም ብሎ ስለሚፈሩ ከእነሱ ጋር ለመከራከር ወይም አለመስማማትን ለመግለጽ ይከብዳቸዋል
- አንድ የቅርብ ግንኙነት ሲያልቅ ወዲያው ሌላ መፈለግ
ኦብሴሲቭ ኮምፐልሲቭ ስብዕና መታወክ (Obsessive-Compulsive Personality Disorder - OCPD)
- ይህ መታወክ ያለባቸው ሰዎች ያለማቋረጥ ለሥርዓት፣ ለፍፁምነት እና ለቁጥጥር ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ይህም አንድን ተግባር ለማጠናቀቅ የሚያስችላቸውን ተለዋዋጭነት ስለሚቀንስ ሥራው እንዲዘገይ ወይም እንዳይጠናቀቅ ያደርጋል። ይህ ባህሪ በግንኙነታቸው ላይም ችግር ሊፈጥር ይችላል።
- በሥርዓት እና በሕጎች ላይ ከመጠን በላይ ማተኮር
- ማንኛውም ነገር እንከን የለሽ መሆን አለበት ብለው ያስባሉ እናም እንደዛ ሆኖ ካልተገኘ መበሳጨት፣ በዚህም ምክንያት ስራዎችን ቶሎ አያጠናቅቁም
- ሰዎችን እና ሁኔታዎችን መቆጣጠር መፈለግ
- ሥራዎችን ለሌሎች ማስተላለፍ አይችሉም፣ ምክንያቱም ሌሎች ጥሩ አድርገው ይሰራሉ ብለው ስለማያምኑ
- በሥራ ወይም በአንድ ፕሮጀክት ላይ ከመጠን በላይ ስለሚያተኩሩ ጓደኞቻቸውን እና ደስ የሚያሰኙ እንቅስቃሴዎችን ይረሳሉ
- የተሰበሩ ወይም ዋጋ የሌላቸውን ነገሮች መጣል አለመቻል
- በአስተሳሰብ እና በባህሪ ግትር ይሆናሉ እንዲሁም የማይለዋወጥ አቋም ያሳያሉ
- በበጀት እና በገንዘብ አጠቃቀም ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ


