የእከክ በሽታ
📌 የእከክ በሽታ (Scabies) ሳርኮፕተስ እስኬቢ (Sarcoptes scabiei) ተብሎ በሚጠራው ተባይ አማካኝነት የሚመጣ የቆዳ በሽታ ነው፡፡
ተባዩ ስምንት እግሮች እና ነጭ ቡናማ ቀለም ያለው ለዐይን የማይታይ ነፍሳት ነው።
ሴቷ ስኬቢስ ከቆዳ በታች ሰርስራ ገብታ ዕንቁላሎችን ትጥላለች፡፡ ዕንቁላሎቹ ከተፈለፈሉ በኋላ ወደ ቆዳው ገጽ ተመልሰው የመቦርቦር እና ዕንቁላሎችን የመጣል ዑደቱን ይቀጥላሉ፡፡ የእከክ በሽታ ከፍተኛ የማሳከክ ስሜት ስለሚፈጥር ቆዳን በመንካት ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ሊዛመት ይችላል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የበሽታው ስርጭት 14.5% ነው።
የእከክ በሽታ እንዴት ይተላልፋል?
አብዛኛውን ጊዜ በሽታው ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው የሚተላለፈው በቆዳ ንክኪ አማካኝነት ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የመተላለፍ ዕድሉ ከፍተኛ ነው።
📌 ብዙውን ጊዜ ልጆች ከወላጆች በንክኪ ሊያዙ ይችላሉ።
📌 ከዚህ በተጨማሪ ልብሶችን እና ፎጣዎችን በመጋራት፣ በአንድ ቤት ውስጥ ብዙ ሆኖ በመኖር፣ እንዲሁም በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ ሊተላለፍ ይችላል።
የበሽታው ምልክቶች ምን ምንድን ናቸው?
የእከክ በሽታ የተለያዩ ምልክቶች አሉት። በብዛት የሚታዩት ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው።
1 እከክ ፡- ከስሙ መረዳት እንደምንችለው የበሽታው ዋና ምልክት እከክ ነው። ብዙውን ጊዜ ምሽት ላይ ወይም ደግሞ ከሙቅ ሻወር በኋላ ይባባሳል፡፡
የሚከተሉት የሰውነት ክፍሎች ከሌሎቹ በበለጠ በበሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
📌 በጣቶች መካከል
📌 በክርን እና በጉልበቶች ዙሪያ መተጣጠፊያ ላይ
📌 በብብት ቆዳ
📌 በጡት ጫፍ ዙሪያ አካባቢ
📌 በወገብ ዙሪያ
📌 በመቀመጫ መሃል እና በላይኛው ጭኖች አካባቢ
- ብዙውን ጊዜ የጀርባ እና የጭንቅላት ቆዳን አያጠቃም።
2 ቆዳ ላይ የሚወጣ ሽፍታ (ቁስሎች)
3 በቆዳ ላይ የሚወጣ ቀጭን የመስመር ምልክት ፡- ይህ ምልክት ሴቷ ተባይ ቆዳን ሰርስራ ስትገባ የሚፈጠር ነው። ምንም እንኳን እከክ የአለባቸው ሰዎች ሁሉ የሚታይ መስመር ባይኖርባቸውም፤ ይህ ምልክት ከሌሎች ምልክቶች በተለየ ከበሽታው ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለው።
4 በሽታ የመከላከል ዐቅማቸው የተዳከመ ሰዎች (ኤች አይ ቪ በሽተኞች፣ ዕድሜያቸው የገፉ ሰዎች እና ሌሎች ሁኔታዎችን ጨምሮ) ከባድ ምልክት ሊኖራቸው ይችላል። ይህም “ክረስትድ እከክ” ተብሎም ይጠራል ፡፡
📌 የክረስትድ እከክ (crusted scabis) ከተለመደው እከክ በተለየ ሁኔታ በሙሉ ሰውነት ላይ የሚሰራጭ እና ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ የሚተላለፍ በሽታ ነው።
የእከክ በሽታ እንዴት ይታከማል?
1 በሽታውን የሚያመጣውን ነፍሳት ለማስወገድ፤ በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው መድኃኒት ፐርሜቲን (permethrin) ይባላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቤንዛይል ቤንዞኤት (Benzyl benzoate)፣ ሰልፈር ሎሽን (Sulfur lotion) እንዲሁም ክረስትድ እከክን ለማከም አቨርሜክቲንን (Ivermectin) እንጠቀማለን፡፡
- እንደማንኛውም መድኃኒት ሁሉ ስኬታማ እንዲሆን የታዘዘው መድኃኒት በትክክል መወሰድ አለበት፡፡ ከአንገት በታች በአለው የሰውነት ቆዳ ላይ ሙሉ በሙሉ መዳረስ አለበት። እንዲሁም በሐኪም በታዘዘው መሠረት ወቅቱን እና ጊዜውን ጠብቀው በአግባቡ መቀባትዎን አይርሱ።
2 የቤተሰብ አባላትን ማከም፤ ተደጋጋሚ የኢንፌክሽን ዑደትን ለማስቀረት ምንም ዓይነት የሚታዩ ምልክቶች ባይኖሩም እንኳን የቤተሰብ አባላት መድኃኒቱን መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
- ከዚህ በተጨማሪ የበሽተኛውን ልብሶች፣ ፎጣዎችን እና አልጋ ልብሶችን ማጠብ ወይም በሙቅ ውሃ መቀቀል ጥሩ ሐሳብ ነው። መቀቀል ባይቻል እንኳን ቢያንስ ለሦስት ቀናት በፕላስቲክ ከረጢቶች ውስጥ ማስቀመጥ ወይም ደግሞ ፀሐይ ላይ ማስጣት ይመከራል።
- ተባዮቹ ከተወገዱ በኋላ ማሳከኩ ለብዙ ሳምንታት ሊቀጥል ይችላል፡፡ ማሳከክ በጣም ከባድ ከሆነ የስቴሮይድ ክሬም ሊጀመር ይችላል፡፡
3 ኢንፌክሽንን ማከም፤ በሽታው ከታከመ በኋላ ቆዳ ብዙውን ጊዜ ያለምንም ችግር ይፈወሳል፡፡ ቆዳን በንጽሕና መጠበቅ፣ ማድረቅ እና አለመነካካት ሊከሰት የሚችለውን ተያያዥ ኢንፌክሽን ለመከላከል ይረዳል፡፡
- ሆኖም ተጨማሪ የቆዳ በሽታ ምልክቶች ከታዩ (ለምሳሌ መቅላት፣ እብጠት፣ መግል፣ ሕመም) ከሐኪም ትእዛዝ በኋላ በአፍ የሚወሰዱ የፀረ ባክቴሪያ መደኃኒቶችን ቢወስዱ ይመከራል፡፡




