የሳይነስ ኢንፌክሽን (sinusitis)

Melat Geatchew
Sep 1, 2025
undefined

የሳይነስ ኢንፌክሽን (sinusitis)

ሳይነሶች(ሽልቋ) በዓይንዎ መካከል ፣ በጉንጭዎ ጀርባ እና በግንባርዎ መካከል ባሉ አጥንቶች ውስጥ የሚገኙ ክፍት ቦታዎች ናቸው፡፡ የአፍንጫዎ ውስጠኛ ክፍል እርጥበት እንዲኖረው የሚያደርጉ ሲሆን ይህም ከአቧራ፣ከአለርጂ እና ከተለያዩ ብክለቶች ለመከላከል ይረዳል፡፡ እነዚህን ሳይነሶች ሸፍኖ የሚገኘው የህብረህዋስ መቆጣት ወይም ማበጥ የሳይነስ ኢንፌክሽን ይባላል።

 

ጤናማ ሳይነሶች በአየር የተሞሉ ናቸው፤  ነገር ግን እነዚህ ክፍት ቦታዎች በተለያየ ምክንያት በሚደፈኑበት ወቅት ፈሳሽ በማጠራቀም ለበሽታ አምጪ ተዋህሲያን መራቢያ ቦታ ይሆናሉ ይህም ኢንፌክሽን ያስከትላል።   

የሳይነስ መደፈንን ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ

  • ጉንፋን
  • በአለርጂ ምክንያት የሚመጣ የአፍንጫ ውስጠኛ ሽፋን እብጠት
  • በአፍንጫ ውስጥ የሚያድግ ትርፍ ስጋ(nasal polyp)
  • የተጣመመ አፍንጫ(deviated septum)

የሳይነስ ኢንፌክሽን ዓይነቶች

  • አጣዳፊ የሳይነስ ህመም(acute sinusitis) የሚጀምረው እንደ ንፍጥ ፣ የአፍንጫ መደፍን እና የፊት ህመም በመሳሰሉ የጉንፋን መሰል ምልክቶች ነው፡፡ በድንገት የሚጀምር በሽታ ሲሆን ከ2 እስከ 4 ሳምንታት ሊቆይ ይችላል፡፡
  • መለስተኛ የሳይነስ በሽታ (Subacute sinusitis) ከ 4 እስከ 12 ሳምንታት የሚቆይ የበሽታ አይነት ነው።
  • ሥር የሰደደ የሳይነስ በሽታ (chronic sinusitis) ምልክቶች ከ12 ሳምንታት ወይም ከዚያ በላይ የሚቆይ በሽታ።
  • ተደጋጋሚ የሳይነስ በሽታ (recurrent sinusitis) በዓመት ውስጥ አራት ወይም ከዚያ ጊዜ በላይ የሳይነስ ኢንፌክሽን ካጋጠመዎ እና በመካከል ጤነኛ ከሆኑ ተደጋጋሚ የሳይነስ በሽታ ይባላል ፡፡

ለሳይነስ ኢንፌክሽን አጋላጭ ሁኔታዎች

  • ከላይ የተጠቀሱት የሳይነስ መደፈን ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች
  • የሰውነት በሽታ መከላከያ ስርዓት መዳከም  
  • ሲጋራ ማጨስ ወይም የሚኖሩበት አካባቢ ጭስ የሚበዛ ከሆነ
  • ተመሳሳይ በሽታ ያለባቸው ልጆች በትምህርት ቤታቸው ውስጥ ካሉ እና በጀርባቸው ተኝተው ጡጦ የሚጠቀሙ ህፃናት ለሳይነስ በሽታ ተጋላጭ ናቸው 

የሳይነስ ኢንፌክሽን ምልክቶች  

አጣዳፊ የሳይነስ ኢንፌክሽን 

  • የፊት ህመም
  • የተደፈነ አፍንጫ
  • የንፍጥ መብዛት
  • የማሽተት ስሜት መቀነስ
  • ሳል
  • ትኩሳት
  • መጥፎ የአፍ ጠረን
  • የድካም ስሜት
  • የጥርስ ህመም

ሥር የሰደደ የሳይነስ ኢንፌክሽን 

እነዚህ ምልክቶች ለ12 ሳምንታት ወይም ከዚያ በላይ ሲቆዩ ስር የሰደደ የሳይነስ ኢንፌክሽን ይባላል

  • የአፍንጫ መታፈን ወይም ሙሉነት ስሜት
  • የአፍንጫ የውስጠኛው ክፍል መምገል
  • ትኩሳት
  • ወፍራም እና ቀለሙን የቀየረ የአፍንጫ ፍሳሽ
  • በተጨማሪም ራስ ምታት ፣የድካም ስሜት፣ መጥፎ የአፍ ጠረን እና የጥርስ ህመም ሊኖርብዎት ይችላል፡፡

እንደነዚህ ያሉት ምልክቶች በተለያዩ በሽታዎች ምክንያት ሊከሰቱ ስለሚችሉ መንኛውንም ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶችን ካስተዋሉ ሃኪምዎን ያነጋግሩ።    

የሳይነስ ኢንፌክሽን ሕክምና

የሳይነስ ኢንፌክሽን ቀለል ከሆነ የአፍንጫ መደፈንን የሚያቃልሉ መድሃኒቶችን መጠቀም ይቻላል። ሆኖም እነዚህን መድሃኒቶች ከ 3 ቀን በላይ ያለ ሃኪም ትዕዛዝ መጠቀም አይመከርም። 

ከባድ የሳይነስ ኢንፌክሽን ካለብዎ ሀኪምዎ ፀረ ባክቴሪያ መድሃኒት ያዝልዎታል፤ ህክምናውም በተገቢው ከተከታተሉ አብዛኛውን ጊዜ ምልክቶች በቀናት ውስጥ ያገግማሉ።

ስር የሰደደ የሳይነስ ኢንፌክሽን ካለብዎ ሃኪምዎ ፀረባክቴሪያ እና ስቴሮይድ መድሃኒት ሊያዝልዎት ይችላል። የሳይነስ ኢንፌክሽን የተፈጠረው በፍንገስ ምክንያት ከሆነ ፀረ ፈንገስ መድሃኒቶች ይታዘዛሉ። 

በተጨማሪ የሚከተሉትን ማድረግ ሊረዳዎት ይችላል

  • በሙቅ ውሃ መታጠን፤ አንፋሎቱ ሳይነሶችን ለመክፈት ይረዳል
  • ለብ ያለ ውሃ ውስጥ ጨርቅ በመንከር አፍንጫ እና ሳይነሶች አካባቢ መያዝ
  • አብዝቶ ውሃ መጠጣት የአፍንጫ ፈሳሽ መወፈርን ይከላከላል
  • የአፍንጫ መደፈንን የሚያቃልሉ መድሃኒቶችን ለተገቢው ጊዜ መጠቀም ሊረዳ ይችላል
  • የሳይነስ ኢንፌክሽን ቀስቃሾችን ማስወደግ

የሳይነስ ኢንፌክሽንን  መከላከል እችላለሁ?

  • ሲጋራ ከማጨስ ይቆጠቡ፤ የሌሎችንም ጭስ ያስወግዱ፡፡
  • እጅዎን በአግባቡ በተደጋጋሚ ይታጠቡ እና ፊትዎን ላለመንካት ይሞክሩ፡፡
  • አለርጂዎትን ከሚቀሰቅሱ ሁኔታዎች ይራቁ ፤ የአለርጂ መድሃኒት የሚያስፈልግዎት ከሆነ ሃኪምዎን ያነጋግሩ። 
  • የሳይነስ ኢንፌክሽን የሚደጋገምብዎት ከሆነ ሳይነሶችን ለማፅዳት የሚደረግ ቀዶ ጥገና ስላሉት ጥቅሞች እና ጉዳቶች ከሃኪም ጋር ይነጋገሩ።    

ሕክምና ያልተደረገለት የሳይነስ ኢንፌክሽን ምን ያስከትላል?

ሳይነሶችዎ መከፈት እስኪጀምሩ ድረስ ህመም እና ምቾት መንሳት ይኖርዎታል፡፡ አልፎ አልፎ  ያልታከመ የሳይነስ በሽታ ወደ ማጅራት ገትር በሽታ ፣ የአንጎል እጢ ወይም የአጥንት ኢንፌክሽን ያስከትላል፡፡

Comments (1)

kemal hasen
Sep 2, 2025

selam docter