የቀለም ዓይነ ስውርነት ምንድነው?
የቀለም ዓይነ ስውርነት በሌላ ስያሜው የቀለም እይታ ጉድለት በመባልም የሚታወቅ ሲሆን ተጠቂ የሆነ ሰው ቀለማትን የሚገነዘብበትን ስርአት የሚጎዳ ሁኔታ ነው። እንደ ዓይነቱ እና መንስኤው ሁኔታው ከቀላል እስከ ከባድ ሊሆን ሲችል የቀለም ዓይነ ስውር የሆኑ ሰዎች የሚከተሉትን ቀለሞች የመለየት ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል፡-
- ቀይ እና አረንጓዴ
- ሰማያዊ እና ቢጫ እና
- አልፎ አልፎ ሁሉንም ቀለሞች -> አክሮማቶፕሲያ ይባላል
ለምን ይከሰታል?
የቀለም እይታችን የሚወሰነው ቀይ፣ አረንጓዴ እና ሰማያዊ ብርሃንን እንድናይ በሚረዱን ሬቲና ውስጥ ባሉ ልዩ ሴሎች ላይ ሲሆን እነዚህ ሴሎች በትክክል ካልሰሩ የቀለም መታወር ይከሰታል። በዓለም ዙሪያ ከ12 ወንዶች መካከል 1ኛው እና ከ200 ሴቶች መካከል ደግሞ 1ዷ ከቀለም ዓይነ ስውርነት ጋር ይወለዳሉ ተብሎ ሲታሰብ አብዛኛዎቹ የቀለም ዓይነ ስውርነት አይነቶች X ከተሰኘው የዘረመል ጋር ስለሚገናኙ በወንዶች ላይ ይበልጥ የተለመደ ነው።
መንስኤዎች
1. በዘር የሚተላለፍ (ጄኔቲክ)
- በጣም የተለመደው መንስኤ ነው።
- ከወላጆች የሚተላለፍ ነው።
- ብዙውን ጊዜ ከሴቶች ይልቅ ወንዶችን ያጠቃል።
2. ከመወለድ በኋላ የሚመጣ
- የዓይን በሽታዎች (እንደ ግላኮማ ወይም ማኩላር መበስበስ)
- የተወሰኑ መድሃኒቶችን መጠቀም
- ለጎጂ ኬሚካሎች መጋለጥ
- እርጅና
- በአይን ወይም በአንጎል ላይ ጉዳት
ምርመራ
የቀለም ዓይነ ስውርነት ብዙውን ጊዜ የሚመረመረው የቀለም እይታ ፈተናዎችን በመጠቀም ሲሆን፣ እነርሱም፦
- የኢሺሃራ ፈተና፦ በባለቀለም ነጠብጣቦች የተሰሩ ስዕሎችን በመመልከት ቁጥሮችን ወይም ቅርጾችን ለመለየት በመሞከር ምርመራው ይካሄዳል።
- የአኖማሎስኮፕ ምርመራ፦ የበለጠ ዝርዝር የምርመራ አይነት ሲሆን በልዩ ባለሙያዎች ጥቅም ላይ ይውላል።
- የኦንላይን ምርመራዎች፦ በበይነ መረብ ላይ የሚገኙ መመርመሪያዎች ሀሳብ ሊሰጡ ቢችሉም በባለሙያ ለሚደረግ የዓይን ምርመራ ምትክ አይደሉም።
እርስዎ ወይም ልጅዎ ላይ የቀለም እይታ ላይ ችግር ሊኖር ይችላል ብለው ካሰቡ የዓይን ሐኪም ጋር ቀጠሮን በመያዝ ምርመራውን በቀላሉ ያድርጉ።
ከቀለም ዓይነ ስውርነት ጋር አብሮ መኖር
በአሁኑ ጊዜ በዘር ለሚተላለፍ የቀለም መታወር መድኃኒት ባይኖርም የዕለት ተዕለት ኑሮን ቀላል ለማድረግ የሚያገለግሉ መንገዶች አሉ፡-
- ቀለምን የሚያስተካክሉ መነጽሮች፡- እንደ ኢንክሮማ መነጽሮች ያሉ ልዩ ሌንሶች አንዳንድ ሰዎች ቀለሞችን በተሻለ ሁኔታ እንዲለዩ ሊረዳቸው ይችላሉ።
- የስልክ መተግበሪያዎች፡- ለተሻለ እይታ እና ቀለሞችን ለመለየት የስክሪን ቅንጅቶችን በማስተካከል ያግዛሉ።
- የትምህርት ድጋፍ፡- መምህራን በትምህርት ቤት የቀለም እይታ ጉድለት ያለባቸውን ልጆች ለመርዳት ቁሳቁሶችን ማላመድ ይችላሉ።
የቀለም ዓይነ ስውርነት ብዙውን ጊዜ የእይታ ቅልጥፍናን ስለማይጎዳ ሰዎች ከሁኔታው ጋር በቀላሉ በመላመድ መኖር ይችላሉ። እርስዎ ወይም የሚያውቁት ሰው የቀለም ዓይነ ስውርነት ካለበት፣ ይህ ከባድ በሽታ እንዳልሆነ ማስታወስ ጠቃሚ ሲሆን በጥቂት ማስተካከያዎች እና ትክክለኛ ድጋፍ ሙሉ እና ንቁ ህይወትን መምራት ይቻላል።


