ድንገተኛ የፍርሃት ችግር በተደጋጋሚ እና ያልተጠበቁ የድንጋጤ ክስተቶች የሚገለጽ ነው። ድንገተኛ የፍርሃት ችግር በየጊዜው እና በማንኛውም ሰዓት፣ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ወይም ምንም አደጋ ሳይኖር ፣በድንገት የሚመጣ የፍርሃት ስሜት ነው። የዚህ በሽታ ዋና መለያ ባህሪው ጥቃቶቹ ያለማስጠንቀቂያ መከሰታቸው ነው።
እነዚህ የድንጋጤ ጥቃቶች በማንኛውም ጊዜ ሊከሰቱ ይችላሉ፣ አንዳንዴም በእንቅልፍ ወቅት ሳይቀር። አብዛኛውን ጊዜም ከ5 እስከ 20 ደቂቃዎች ይቆያሉ። በቀን ውስጥም ብዙ ጊዜ ወይም በዓመት ውስጥ ጥቂት ጊዜያት ሊከሰቱ ይችላሉ። ድንገተኛ የፍርሃት ችግር ያለባቸው ብዙ ሰዎች ሌላ ጥቃት ሊያጋጥም ይችላል ብለው ስለሚጨነቁ፣ ሌላ ጥቃት እንዳይደርስባቸው ህይወታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ሊለውጡ ይችላሉ። የድንጋጤ የፍርሃት ችግር ብዙውን ጊዜ የሚጀምረው በጉርምስና ዕድሜ መጨረሻ ወይም በወጣትነት ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ነው። ሴቶች ከወንዶች በበለጠ የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው።
የድንገተኛ የፍርሃት ችግር መንስኤ ምን እንደሆነ ባይታወቅም፣ የሚከተሉት ምክንያቶች ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፦
- ዘረመል (Genetics)
- ከባድ ጭንቀት
- በአንጎል ክፍሎች አሰራር ላይ የሚከሰቱ አንዳንድ ለውጦች
- በቤተሰብ ውስጥ የድንጋጤ ጥቃቶች ወይም ድንገተኛ የፍርሃት ችግር ታሪክ መኖር
- የቅርብ ሰው ሞት ወይም ከባድ ህመም
- በሕይወት ውስጥ የሚከሰቱ ትልልቅ ለውጦች
- ማጨስ ወይም ከመጠን በላይ ካፌይን መጠጣት
- በልጅነት ጊዜ አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ታሪክ መኖር
ድንገተኛ የፍርሃት ችግር ምልክቶች
ድንገተኛ የፍርሃት ችግር ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፦
- የልብ ምት ፍጥነት መጨመር
- ማላብ
- መንቀጥቀጥ
- የትንፋሽ ማጠር ወይም የመታፈን ስሜት
- ማቅለሽለሽ ወይም የሆድ ህመም
- ማዞር ወይም የራስ ምታት
- ራስን መሳት
- ከራስ የመለያየት ስሜት
- የራስ ቁጥጥርን የማጣት ወይም የመሞት ፍርሃት
- ብርድ ብርድ ማለት ወይም ትኩስ ስሜት
- የደረት ህመም እና የልብ ድካምን የሚመስሉ ሌሎች ምልክቶች
- እጅ እና እግሮችን የመጠዝጠዝ ወይም የመደንዘዝ ስሜት
ድንገተኛ የፍርሃት ችግር እንዴት ይታወቃል?
የጤና ባለሙያዎ ስለ ምልክቶችዎ እና ስለ ህክምና ታሪክዎ ይጠይቃሉ። የድንጋጤ ጥቃቶችን የሚመስሉ ምልክቶችን ከሚያስከትሉ እንደ የልብ ህመም፣ የታይሮይድ በሽታ እና የመተንፈሻ አካላት ችግሮች ለመለየት ምርመራዎችን ሊያደርጉ ይችላሉ።
የአእምሮ ጤና ባለሙያ የሚከተሉትን የሚያካትት ሙሉ ግምገማ ያደርጋሉ፦
- በድንጋጤ ጥቃት ወቅት ስላሉዎት ሀሳቦች፣ ስሜቶች እና ምልክቶች ጥያቄዎችን መጠየቅ
- በጥቃቶቹ መካከል ስላሉዎት ሀሳቦች፣ ስሜቶች እና ባህሪያት መጠየቅ
- የሌሎች የስነ-አእምሮ ህመሞች ምልክቶችን ማረጋገጥ
አንድ ሰው ድንገተኛ የፍርሃት ችግር እንዳለበት ለመመርመር የስነ-አእምሮ ህክምና ማህበር ባወጣው DSM-5 ላይ የተዘረዘሩት መስፈርቶች የሚከተሉት ናቸው፦
- ተደጋጋሚ እና ያልተጠበቁ የድንጋጤ ክስተቶች መኖር
- ቢያንስ አንድ የድንጋጤ ጥቃት ከተከሰተ በኋላ፣ ለአንድ ወር ወይም ከዚያ በላይ ስለ ሌላ ጥቃት መምጣት ስጋት መኖር፣ ሁነታው የሚያስከትለው መዘዝ እንዳለ ማሰብ እና መፍራት ወይም የድንጋጤ ጥቃት ያስነሳሉ ብለው የሚያስቧቸውን ሁኔታዎች ማስወገድን የመሰሉ ባህሪያዊ ለውጦች መኖር
- የድንጋጤ ጥቃቶቹ በአደንዛዥ እጾች አጠቃቀም፣ በጤና ችግር ወይም እንደ ማህበራዊ ፍርሃት (social phobia) ወይም ኦብሰሲቭ-ኮምፐልሲቭ ዲስኦርደር (OCD) ባሉ ሌሎች የአእምሮ ጤና ችግሮች አለመከሰታቸው ማረጋገጥ
ህክምናው ምንድን ነው?
የስነ-ልቦና ህክምና (psychotherapy)፣ መድሃኒቶች ወይም የሁለቱም ጥምረት ድንገተኛ የፍርሃት ችግርን ለማከም በጣም ውጤታማ ናቸው። ለምን ያህል ጊዜ ህክምና እንደሚያስፈልግዎ የሚወሰነው የበሽታው ክብደት እና ህክምናው ምን ያህል ውጤት እንዳለው በማየት ነው። ይህንን በሽታ ለማከም የሚረዱ መድሃኒቶች ፀረ-ድብርት መድሃኒቶች (Antidepressants) እና ፀረ-ጭንቀት መድሃኒቶች (Anti-anxiety medications) ናቸው።
በትክክለኛ ህክምና፣ የድንጋጤ ጥቃቶች የሚያጋጥማቸው ወይም የድንጋጤ መታወክ ያለባቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች ይድናሉ። ያለ ህክምና ግን፣ ይህ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ራስን የማጥፋት ሃሳብ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም፣ በማህበራዊ ግንኙነታቸው ላይ በሚፈጠር ችግር ምክንያት የኑሮ ጥራታቸው ሊቀንስ ይችላል።
የድንጋጤ ጥቃቶችን እንዴት መከላከል ይቻላል?
የጤና ባለሙያዎ የድንጋጤ ጥቃቶችን የሚያስነሱ ነገሮችን ለይተው እንዲያውቁ ሊረዱዎት ይችላሉ። በስነ-ልቦና ህክምና (psychotherapy) ወቅት፣ እነዚህን የሚያስነሱ ክስተቶችን ለመቆጣጠር እና ጥቃቱን ለመከላከል የሚረዱ ስልቶችን ይማራሉ።
የድንጋጤ ጥቃት በሚያጋጥምዎት ጊዜ ማድረግ ያለብዎት ነገሮች፦
- በተቻለ መጠን ባለበት ቦታ ይቆዩ
- በቀስታ እና በጥልቀት ይተንፍሱ
- ጥቃቱ እንደሚያልፍ ለራስዎ ያስታውሱ
- አዎንታዊ፣ ሰላማዊ እና ዘና የሚያደርጉ ነገሮች ላይ ትኩረት ያድርጉ
- ለሕይወት አስጊ እንዳልሆነ ያስታውሱ
ተጨማሪ ጥቃት እንዳይከሰት መከላከል የሚከተሉት ነገሮች ሊረዱዎት ይችላሉ፦
- ስኳር የበዛባቸው ምግቦችን እና መጠጦችን፣ ካፊን፣ አልኮል እና ማጨስን ያስወግዱ
- መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ
- ጤናማ አመጋገብ ይመገቡ
- ጭንቀትን ጤናማ በሆኑ መንገዶች ይቆጣጠሩ
- ዮጋ እና ለጭንቀት የሚሆኑ የአተነፋፈስ ልምምዶችን ይለማመዱ
- በቂ እንቅልፍ ያግኙ
- የራስ አገዝ መጽሐፍ ያንብቡ




