ስኮፖላሚን (የዲያብሎስ እስትንፋስ)

Eyasu Yebeltal
Sep 3, 2025
undefined

ስኮፖላሚን (የዲያብሎስ እስትንፋስ)

ስኮፖላሚን በእንቅስቃሴ የሚመጣ ማቅለሽለሽን ከማከም ጀምሮ እስከ ከቀዶ ጥገና በኋላ የሚኖር የማቅለሽለሽ ስሜትን ለማስታገስ የሚያገለግል ጠቃሚ መድሃኒት ነው። ይህ መድሃኒት በጤና አገልግሎት ውስጥ በጣም ጠቃሚ ቢሆንም መጥፎ ጎንም አለው። አደገኛነቱ አንድ ታዋቂ ቅጽል ስም ያስገኘለት ሲሆን የዲያብሎስ እስትንፋስ በመባል ይታወቃል። በዚህ ጽሁፍ ስኮፖላሚን ምን እንደሆነ፣ ህጋዊ የህክምና አጠቃቀሞቹ እና ለምን አደገኛ የሚለውን ዝና እንዳተረፈ እናያለን።

ስኮፖላሚን ምንድን ነው?

ስኮፖላሚን በሶላናሲኤ የዕፅዋት ቤተሰብ ውስጥ ካሉ ዕፅዋት የሚገኝ ትሮፔን አልካሎይድ ኬሚካል ሲሆን እንደ ናይትሼድ ተክል ያሉ ዝርያዎችን ያካትታል። አብዛኛውን ጊዜ ማቅለሽለሽ እና ማስታወክን ለመከላከል እንደ መድሃኒት አገልግሎት ላይ ሲውል በተለይም ለእንቅስቃሴ ማቅለሽለሽ ህክምና፣ ከቀዶ ጥገና በኋላ ለማቅለሽለሽ ህክምና እና አንዳንድ የፓርኪንሰን በሽታ ሕክምናዎች አካል ነው። መድሃኒቱ በጡንቻ እንቅስቃሴ እና በነርቭ ምልክቶች ላይ ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን የአሲታይል ኮሊን የነርቭ አስተላላፊ በመከልከል ሲሰራ የዚህን ኬሚካል መቀበያዎች በመዝጋት ስኮፖላሚን በአንጎል እና በሰውነት ውስጥ የሚፈጠሩ የማይፈለጉ ምልክቶችን (ማቅለሽለሽ እና ማዞር) ይቀንሳል።

የሕክምና አጠቃቀም

አደገኛ የሚል ዝና ቢኖረውም ስኮፖላሚን በሕክምና ልምምድ ውስጥም ጠቃሚ መድሃኒት ነው። ከተለመዱ የህክምና ጥቅሞቹ መካከል አንዳንዶቹ የሚከተሉትን ያካትታሉ፡-

  • የእንቅስቃሴ ህመም፡- ስኮፖላሚን እንደ መኪና፣ ጀልባ እና አውሮፕላን ያሉ መጓጓዣዎችን ስንጠቀም በጉዞ ምክንያት የሚመጣን ማቅለሽለሽ እና ማስታወክን ለመከላከል ጥቅም ላይ ይውላል።
  • ከቀዶ-ጥገና በኋላ ማቅለሽለሽ፡- ስኮፖላሚን ከቀዶ ጥገና በኋላ ከማደንዘዣ ጋር ተያይዞ የሚመጣን ማቅለሽለሽ እና ማስታወክን ይከላከላል።
  • የፓርኪንሰን በሽታ፡- በአንዳንድ ሁኔታዎች ስኮፖላሚን የተወሰኑ የፓርኪንሰን በሽታ ምልክቶችን ለመቆጣጠር ይጠቅማል (ለምሳሌ የጡንቻ ጥንካሬን እና መንቀጥቀጥን)።
  • የአንጀት መቆጣት፡- አንዳንድ ጊዜ በአንጀት መቆጣት(IBS) ምክንያት የሚፈጠር የሆድ ቁርጠትን ለማስታገስ ይጠቅማል።

ስኮፖላሚን እንደዚህ አይነት ጥቅሞች ቢኖሩትም አላግባብ ጥቅም ላይ ከዋለ ከባድ የጎንዮሽ ጉዳቶች አሉት።

ስኮፖላሚን እንደ የዲያብሎስ እስትንፋስ

መድሃኒቱ አላግባብ ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ ሊያመጣ የሚችለውን አስከፊ ውጤት ምክንያት በማድረግ “የዲያብሎስ ትንፋሽ” የሚለውን አስፈሪ ስያሜ አግኝቷል። ስሙ በዋነኝነት የመነጨው በኮሎምቢያ ውስጥ ካሉ ሪፖርቶች ሲሆን ስኮፖላሚን እንደ ዝርፊያ እና አልፎ ተርፎም አፈና ላሉ ወንጀሎች ዋነኛ መሳሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። በከፍተኛ መጠን ወይም ያለ የሕክምና ክትትል ሲወሰድ ስኮፖላሚን ከባድ ግራ መጋባት፣ የማስታወስ ችሎታ መቀነስ፣ ቅዠት እና አጠቃላይ የአቅም ማነስ ሁኔታን ሊያስከትል ይችላል። በአንዳንድ ሁኔታዎች በስኮፖላሚን ተጽእኖ ስር ያሉ ግለሰቦች በከፍተኛ ግራ በመጋባት ውስጥ ሆነው ሳያውቁ ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ ወይንም የግል መረጃቸውን ለወንጀለኞች አሳልፈው እንዲሰጡ ተደርገዋል።

ስኮፖላሚን ለምን በጣም አደገኛ ሆነ?

መድሃኒቱ በህክምና ቁጥጥር ስር አገልግሎት ላይ ሲውል ጠቃሚ ቢሆንም የስኮፖላሚን የወንጀል አጠቃቀም የግለሰቦችን ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል።

  • የማስታወስ ችሎታን ማጣት፡- ስኮፖላሚን ከሚያስከትላቸው አስጨናቂ ተጽእኖዎች  አንዱ የመርሳት ችግር ነው። በተጽእኖው ስር ያሉ ሰዎች በሰከሩበት ወቅት የሆነውን ላያስታውሱ ስለሚችሉ ለብዝበዛ ይጋለጣሉ።
  • ግራ መጋባት፡- ከፍተኛ መጠን ያለው ስኮፖላሚን ከፍተኛ ግራ መጋባት እና ውዥንብርን ያስከትላል። በተጽእኖው ስር ያሉ ግለሰቦች አካባቢያቸውን እንዳያስተውሉ እና አልፎ ተርፎም በእነሱ ላይ ምን እየደረሰባቸው እንዳለ ለመረዳት እንዲያስቸግራቸው ያደርጋል።
  • ንቃተ-ህሊና ማጣት እና ታዛዥነት፡- እጅግ በጣም በከፋ መልኩ፣ ስኮፖላሚን ግለሰቦች የሚያደርጉትን ሳያውቁ ትእዛዞችን እንዲታዘዙ ሊያደርጋቸው ይችላል። ሰዎች በተጽእኖው ስር ሆነው ሳያውቁ የግል መረጃቸውን አሳልፈው እንደሰጡ እና አልፎ ተርፎም ውድ ዕቃዎችን እንዳስረከቡ ሪፖርት አድርገዋል።

ስኮፖላሚንን ከመጠን በላይ መውሰድ ወይም አላግባብ መጠቀም ምልክቶች

ስኮፖላሚን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ወይም ከመጠን በላይ ከተወሰደ ወደ አደገኛ ውጤቶች ሊመራ ይችላል። እነዚህ ምልክቶች የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ፡-

  • ደረቅ አፍ እና ጉሮሮ
  • የደበዘዘ እይታ
  • የአይን ብሌን መስፋት
  • የመሽናት ችግር
  • ፈጣን የልብ ምት
  • የሰውነት ሙቀት መጨመር
  • ከባድ ጭንቀት ወይም ግራ መጋባት እና
  • ቅዠቶች 

እርስዎ ወይም የሚያውቁት ሰው ስኮፖላሚን ከወሰዱ በኋላ እነዚህን ምልክቶች ካጋጠመዎት ወዲያውኑ የሕክምና ዕርዳታ ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው።

ስኮፖላሚንን እንዴት በትክክል መጠቀም ይቻላል?

ሕጋዊ ለሆነ የጤና ሁኔታ ስኮፖላሚን እንዲወስዱ ከታዘዙ ደህንነቱ የተጠበቀ አጠቃቀምን ለማረጋገጥ ሊወስዷቸው የሚችሏቸው እርምጃዎች አሉ። እነሱም፡- 

  • የሕክምና ምክሮችን ይከተሉ፡- ሁል ጊዜ ስኮፖላሚንን ዶክተርዎ እንዳዘዘው ይውሰዱ። የስኮፖላሚን ፕላስተርን እየተጠቀሙ ከሆነ በትክክለኛው ቦታ ላይ ማስቀመጥዎን በማረጋገጥ እንደ መመሪያው ይቀይሩት።
  • ከሌሎች መድሃኒቶች ጋር አይቀላቅሉት፡- ሌሎች መድሃኒቶችን በተለይም የነርቭ ስርዓትዎ ላይ ተጽእኖ የሚያደርጉ መድሃኒቶችን ሚወስዱ ከሆነ ሃኪምዎን ያማክሩ። ስኮፖላሚንን ከአልኮሆል ወይም ከሌሎች ማስታገሻዎች ጋር መቀላቀል የጎንዮሽ ጉዳቶችን ይጨምራል።
  • የጎንዮሽ ጉዳቶችን ይከታተሉ፡- እንደ ግራ መጋባት፣ የዓይን ብዥታ፣ ወይም የመሽናት ችግር ያሉ ያልተለመዱ የጎንዮሽ ጉዳቶች ካጋጠሙዎት ወዲያውኑ ዶክተርዎን ያነጋግሩ።
  • ሌሎች እንዳይደርሱበት ያድርጉት፡- ስኮፖላሚን በተሳሳተ እጅ አደገኛ ሊሆን ስለሚችል ከልጆች ወይም አላግባብ ሊጠቀምበት ከሚችል ማንኛውም ሰው ርቆ በጥንቃቄ መቀመጡን ያረጋግጡ።

እንደ ማንኛውም መድሃኒት ስኮፖላሚንን በታዘዘው መሰረት ብቻ መጠቀም እና ሊያስከትል የሚችለውን የጎንዮሽ ጉዳት ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ስኮፖላሚን በሕክምናው ዓለም ውስጥ ጠቃሚ መድሃኒት ቢሆንም አላግባብ ጥቅም ላይ ሲውል አደገኛ የመሆን አቅም አለው። እንደ ኮሎምቢያ ባሉ ቦታዎች መድኃኒቱን ለወንጀል አጠቃቀምም ላይ ስለሚውል ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

Comments (0)