የአጥንት መሳሳት በሽታ (Osteoporosis) ምንድን ነው?
•የአጥንት መሳሳት (ኦስቲዮፖሮሲስ/Osteoporosis) ምን ማለት ነው የሚለውን በቀጥታ እንተርጉም ብንል የተቦረቦረ አጥንት (porous bone ) እንደማለት ሲኾን ይህም በአጥንት ክብደት እና ውቅር ላይ የሚኖረውን ጥቅጥቅ በማሳሳት እስከ ስብራት የሚያደርስ የአጥንት በሽታ ነው።
ወደ ሦስት ምድብ ያክል የአጥንት መሳሳት ክፍፍል አይነቶች ያሉ ሲኾን
እነዚህም:-
አይነት 1
•ከማረጥ ዕድሜ በኋላ ባሉ ሴቶች ላይ የሚከሰት (post menopausal type) በመባል ይታወቃል።
አይነት 2
• ይህ አይነት ደግሞ በኹለቱም ፆታዎች ከዕድሜያቸው ገፋ ባሉ ወንዶችና ሴቶች ላይ በሚኖር የአራሚ የአጥንት ህዋሳት የበላይነት ምክንያትነት (bone resorption) ሳቢያ የሚመጣ (Involutional type) የአጥንት መሳሳት አይነት ነው።
አይነት 3
• በዚህ ክፍል ስር የሚጠቃለሉት ችግሮች የሚከሰቱት ደግሞ በሌላ ሥር ሰደድ የጤና እክል መንስኤነት የተነሳ ለአጥንት መሳሳት ሲጋለጡ ሲኾን የጋራ ስማቸውም ሁለተኛ ደረጃ የአጥንት መሳሳት (Secondary osteoporosis) በመባል ይመደባሉ።
ለአጥንት መሳሳት በሽታ በምክንያትነት የሚጠቀሱ አጋላጭመንስኤዎች የሚባሉት ምን ምን ናቸው?
●እርጅና (Older age)
●ማረጥ (menopause)
●ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት፣
●ከመጠን ያለፈ የአነቃቂ መጠጦችን (ካፌይን:- ለምሳሌ ቡና) መውሰድ፣
●ሲጋራ ማጨስ
●የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለመሥራት፣
●የምግብ እጥረት (malnutrition)
●ዝቅተኛ የሰውነት ክብደት/ቀጫጫ መኾን (low body weight)
● የቫይታሚን ዲ ወይም የካልሲየም ማዕድንን በዝቅተኛ መጠን መመገብ (low intake)
● የመውደቅና በቀላሉ መሰበር እንዲሁም በቅርብ ቤተሰብ አባላት ላይ የአጥንት መሳሳት ስብራት (family history) ታሪክ መኖር
●ሌሎችም ሥር ሰደድ ሕመሞች (Chronic illness):-
○ካንሰር
○ሥር ሰደድ የኩላሊት በሽታ
○የልዩ ልዩ ሆርሞኖች መዛባት በሽታዎች (ለምሳሌም:- የታይሮይድ ሆርሞን)
●ለረጅም ጊዜ ለሌላ አገልግሎት ሲባል የሚወሰዱ መድኃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት:-
ለምሳሌ:- # ለሥር ሰደድ ብግነት እና ራስ ሰር ሕመሞች ሲባል የሚታዘዙ አስተካካይ መድኃኒቶች (steroids)፣
#ለሚጥል በሽታዎች የሚወሰዱ መድኃኒቶ (anticonvulsants) ወዘተ
☆የአጥንት መሳሳት ሕክምና ምን ይመስላል፡መከላከያ መንገዶችስ?
•አስቀድሞ የአጥንት ተሰባሪነትን መከላከል
•ስብራት ከተከሰተ ደግሞ ከዚህ በኋላ የሚኖረውን ውስብስብነት መከላከልና መጠገን ናቸው።
የአጥንት መሳሳትን ለመከላከል እንዲህ ቢያደርጉስ
•የአልኮል መጠጥ አለመውሰድ
•ሲጋራን ማጤስ ማቆም
•በቂ ካሎሪ ያላቸውን በካልሲየምና በቫይታሚን ዲ የበለፀጉ ምግቦችን ማዘውተር ለምሳሌም ያክል:-
*ወተት እና የወተት ተዋፅዖ የኾኑ ምግቦች
*በካልሲየም የበለፀጉ አረንጓዴ የአትክልትና ፍራፍሬ ምግቦችን መመገብ ለምሳሌ:- ከአትክልቶች እንደ ቆስጣ ያሉት እንዲሁም
የስጋ ውጤቶች የመሳሰሉት
•የፀሐይ ብርሃንን(ከ4-10 ሰዓት)በቀጥታ መሞቅ ይህም ቫይታሚን ዲ እንዲመረት ያደርጋል።
•የሚወስዱትን የአነቃቂ መጠጦች (caffeine containing drinks) ለምሳሌ እንደ ኮካ ኮላና ቡና ያሉትን መጠን መቀነስ ምክንያቱ ደግሞ ለአጥንት ጥንካሬ ዋነኛ የሚባለውን የካልሲየም ማዕድንን በሰውነታችን በተገቢው አገልግሎት እንዳይሰጥ ስለሚያስተጓጉሉ ነው።
•ለሰውነት የጡንቻ ጥንካሬና ሚዛን ማስጠበቂያ ሲባል ቀለል ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ።
•የዕድሜ መግፋት በተለይም ከ65 ዓመት ዕድሜ በላይ ላሉ ሴቶች እንዲሁም ደግሞ የአጥንት መሳሳትን እንደጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትሉ መድኃኒቶች ናቸው ተብለው የሚታወቁትን የሚወስዱ ከኾነ ለአጥንት መሳሳት ችግር ተብሎ ምርመራዎችን ቢያደርጉና በሐኪም የሚታዘዙትን መድኃኒቶች እንዲወስዱ ይመከራል፤ይኸውም አጥንትን ከእንደገና እንዲደራጅና የስብራት ተጋላጭነትን አንዲቀንስ የሚያደርጉ መድኃኒቶችን በመስጠት የአጥንትን የማዕድን ክምችት ምንም እንኳ 100% ሙሉ በሙሉ መመለስ ባይቻልም አጥጋቢ በኾነ ኹኔታ ለማስጠበቅ ይችላል::
🦴በማረጥ ዕድሜ ክልል ውስጥ አሊያም ቀደሞውኑ የኢስትሮጂን ሆርሞን ምንጩ ዕንቁልጢ በልዩ ልዩ ምክንያት መሥራት ባቆመባቸው ሴቶች(premature ovarian failure) ላይ ደግሞ ለአጥንት ጥንካሬ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱትን ሆርሞኖችን የመተካት ህክምና (hormonal replacement therapy) በመድኃኒት መልክም ሊሰጥ ይችላል።
●በቀን ውስጥ ለእያንዳንዱ ሰው የሚመከረው የካልሲየም መጠን ግን ምን ያክል ነው?
• በየቀኑ እንድንወስድ የሚመመከረው የካልሲየም መጠን እንደ ፆታ፣ ዕድሜ፣ በእርግዝና ጊዜ እና ጡት ማጥባት በመሳሰሉ ጊዜዎች ኹሉ የሚለያይ ቢኾንም እንኳ፡
•ለአዋቂዎች 800-1000 mg
•እርግዝና እና በጡት ማጥባት ጊዜ 1200 mg
•ከ51 ዓመት በኋላ በተለይ ለሴቶች 1200 mg
•ሕፃናት 200-400 mg


